1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በግራዎች ጥምረት አሸናፊነት የተደመደው የፈረንሳይ ምክር ቤታዊው ምርጫ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 2 2016

ባለፈው እሁድ የተካሄደው የፈረንሳይ ሁለተኛ ዙር ምክር ቤታዊ ምርጫ በግራዎች ጥምረት አሸናፊነት መጠናቀቅ የቀኝ ጽንፈኞችን ተጠናክሮ የመውጣት ስጋት አስቀርቷል። ይሁንና ከተወዳዳሪዎቹ አንዳቸውም ከ50 በመቶ በላይ ድምጽ አለማሸነፋቸው ግን የወደፊቱን የሀገሪቱን አቅጣጫ በእርግጠኛነት ለማወቅ አስቸግሯል።

https://p.dw.com/p/4i4f0
የፈረንሳይ ግራ አክራሪ ፓርቲ LFI መሪዎች ከድሉ በኋላ
የፈረንሳይ ግራ አክራሪ ፓርቲ LFI መሪዎች ከድሉ በኋላ ምስል Thomas Padilla/AP Photo/picture alliance

በግራዎች ጥምረት አሸናፊነት የተደመደው የፈረንሳይ ምክር ቤታዊው ምርጫና የፈረንሳይ መጻኤ እድል

በስተመጨረሻ ፈረንሳይ እፎይ አለች፤ የአውሮጳ ወዳጆችዋም የፈረንሳይን እፎይታ ተጋርተዋል። ከአንድ ሳምንት በፊት አስፈርቶ የነበረው የፈረንሳይ ቀኝ ጽንፈኞች ወደ ስልጣን መጠጋት አሁን ስጋት መሆኑ ቀርቷል። የፈረንሳይ ህዝብ በሁለተኛ ዙር የምክር ቤት ምርጫ  ቀኝ ጽንፈኞችን ሳይሆን የግራ ፓርቲዎች ቅንጅትን መርጧል። ምርጫው ቀኝ ጽንፈኞች ወደ ስልጣን እንዳይጠጉ አድርጓል። የመሀል አቋም ያለው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮ ጎራ 164 መቀመጫዎችን በማግኘት በምርጫው ሁለተኛ ደረጃን ሲይዝ በመጀመሪያው ዙር ምርጫ ብዙ ድምጽ በማግኘት የመጀመሪያውን ቦታ ይዘው የነበሩት ቀኝ ጽንፈኞች ግን  ከጨዋታ ውጭ ሆነዋል።  ያም ሆኖ በምርጫው ሦስተኛ ደረጃ ያገኘው በማሪን ለፐን የሚመራው ቀኝ ጽንፈኛው ናሽናል ራሊ በምህጻሩ RN  ያሸነፈው የምክር ቤት መቀመጫ ከቀድሞው በእጅጉ ጨምሯል።  ምንም እንኳን ምርጫው ቀኝ ጽንፈኞችን ከስልጣን ማራቁ ለብዙሀኑ ፈረንሳውያን  እፎይታን ቢያስገኝም ከተወዳደሩት ፓርቲዎች አንዳቸውም ከ50 በመቶ በላይ ድምጽ አለማሸነፋቸው ፈረንሳይን ባልተረጋገጠ መጻኤ እድል ውስጥ እንድትወድቅ አድርጎል። እስካሁን ማን የወደፊቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሆን ግልጽ አይደለም። ግራዎቹ ጠቅላይ ሚኒስት ከነርሱ እንዲሆን ግፊት እያደረጉ ነው።
የግራው ፓርቲ የፍራንስ አንቦውድ መሪ ዦን ሉክ ሜሎንሾን ከድሉ በኋላ መጀመሪያ እፎይታ ማግኘታቸውን ተናግረው ለማክሮ  ጥሪ አስተላልፈዋል።የቀኝ ጽንፈኞች በፈረንሳይ የመጀመሪያ ዙር ምርጫ ማሸነፍ አንድምታ

 

«በመጀመሪያ ደረጃ ከፍተኛ እፎይታ አግኝተናል። በመጀመሪያ ፕሬዝዳንቱ ስልጣን መልቀቅ ወይም በኛ ደረጃ ካሉት ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትር መምረጥ አለባቸው።ቀድሞ እንደዚህ ተደርጓል። »
እርሳቸው ይህን ሲሉ ደጋፊዎቻቸው ደግሞ  ማክሮ ስልጣን ይልቀቁ እያሉ ነበር። 
በዚህ ሳምንት ለኔቶ ጉባኤ ዋሽንግተን ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙት ፕሬዝዳንት ማክሮ የሚቀጥሉትን እርምጃዎቻቸውን ለመወሰን መጠበቃቸው እንደይቀር ተናግረዋል።   
በዚህ ምርጫ «ኒው ፖፑላር ፍሮንት» በምህጻሩ NFP የተባለው የግራዎቹ ጥምረት ያገኘው አጠቃላይ ድምጽ በፈረንሳይ ፓርላማ ጠንካራው ቡድን ለመሆን አብቅቶታል። ጥምረቱ የግራ ክንፉን ፓርቲ «ፍራንስ አንቦውድ» በምህጻሩ LFIን የመሀል ግራውን የሶሻሊስቶች ፓርቲ አረንጓዴዎቹንና የፈረንሳይ ኮምኒስቶች ፓርቲን በዋናነት እንዲሁም ሌሎች ትናንሽ ፓርቲዎችን ያቀፈ ነው። ጥምረቱ የቀኝ ጽንፈኞችን ድል የማጨናገፍ ዓላማ ይዞ የተመሰረተው ከጥቂት ሳምንታት በፊት ነበር። 

ለግራ ክንፎች ጥምረት ድጋፍና ቀኝ ጽንፈኞችን በመቃወም በፕላስ ደላ ሪፐብሊክ የተካሄደው ሰልፍ
ለግራ ክንፎች ጥምረት ድጋፍና ቀኝ ጽንፈኞችን በመቃወም በፕላስ ደላ ሪፐብሊክ የተካሄደው ሰልፍ ምስል Fabrizio Bensch/REUTERS


በርካታ  የአውሮጳ ሀገራት ከምርጫው ውጤት በኋላ እፎይታ አግኝተዋል። በውጤቱ መደሰታቸውን ቀድመው የገለጹት የፖላንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ቱስክ ነበሩ። ቱስክ በቀድሞው ትዊተር በአሁኑ መጠሪያው ኤክስ በጻፉት መልዕክት በፓሪስ መነሳሳት በሞስኮ ቅሬታ በኬቭ እፎይታ ካሉ በኋላ በዋርሶ ደግሞ ለደስታ በቂ የሆነ ብለውታል። ከ8 ዓመታት የወግ አጥባቂዎች አመራር በኋላ ባለፈው ዓመት ስልጣን የያዙት ቱስክ ፈረንሳይ ከሩስያ ጋር ጦርነት የምታካሂደውን ዩክሬንን እንድትደግፍ ይፈልጋሉ። በጀርመንና በስፓኝ የሶሻል ዴሞክራት ፓርቲዎች የፈረንሳይ ቀኝ ጽንፈኞች ፓርቲ RN ከጨዋታ ውጭ ከሆነ በኋላ እፎይታቸውን ገልጸዋል። ፓርቲዎቹ ባለፈው ሳምንቱ የብሪታንያ ምርጫ የሌበር ፓርቲ በፈረንሳይ ደግሞ የNFP ማሸነፍ ቀኝ ጽንፈኞችን በማራቁ ተጽናንተዋል። የስፓኝ ሶሻሊስቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ ከፈረንሳይ ግራዎች ድል በኋላ  በዚህ ሳምንት ሁለት ትላልቅ የአውሮጳ ሀገራት ብሪታንያንና ፈረንሳይን ማለታቸው ነው የስፓኝ ያለፈውን ዓመት ተመሳሳይ መንገድ መርጠዋል፤ቀኝ ጽንፈኞችን ባለመቀበል የህዝቦችን ችግሮች ለመፍታት ይታገላሉ ላሏቸው የግራ ሶሻሊስቶች ግልጽ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል ሲሉ አድንቀዋል። ጀርመንም የምርጫው ውጤት እፎይታ እንደሆናት ነው የተናገረችው። የጀርመን ሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ የSPD ው የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ በግላቸውም ሆነ በመንግሥታቸው ደረጃ ውጤቱ እፎይታ ማስገኘቱን ነው የተናገሩት።የአውሮጳ ምክር ቤት የምርጫ ውጤት እየፈጠረ ያለው ቀውስ


«እኔም ሆንኩ መላው የፌደራል መንግሥት እፎይታ አግኝተናል። የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ከቀኝ ክንፍ ፓርቲ ጋር መጣመርን መቀበል ቢኖርባቸው በጣም ትልቅ ተግዳሮት ይሆን ነበር። ግን ያ አልሆነም። እናም አሁን ፕሬዝዳንቱ ብቻ ሳይሆኑ የተመረጡት የፓርላማ አባላት አበረታች የመንግሥት ምስረታ ይሳካላቸዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።ያም ሆነ እጅግ ጠቃሚ  በሆነው በፈረንሳይና ጀርመን ወዳጅነት ተደስቻለሁ። ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ጋር ባለኝ ጥሩ የግል ግንኙነት ምክንያትም ተደስቻለሁ»
ይሁንና የጀርመን መንግሥት ቃል አቀባይ ሽቴፋን ሄበሽትራይት በፈረንሳይ ፓርላማ አብላጫ ድምጽ ያለው የፖለቲካ ፓርቲ አለመኖር ስጋት ሆኖ መቀጠሉ እንደማይቀር አስጠንቅቀዋል። በዚሁ ጉዳይ ላይም መራኄ መንግስት ሾልዝ ከኢማኑኤል ማክሮ ጋር መነጋገራቸው እንደማይቀርም ጠቁመዋል። በዚህ አጋጣሚም የፈረንሳይና የጀርመን ወዳጅነትም የሁለቱ ሀገራት ይበልጥ መቀራረብ መሠረት መሆኑንም ገልጸዋል። 

ቀኝ ጽንፈኛው የRN ፓርቲ በምርጫው ከተሸነፈ በኋላ የደነገጡት ደጋፊዎቹ
ቀኝ ጽንፈኛው የRN ፓርቲ በምርጫው ከተሸነፈ በኋላ የደነገጡት ደጋፊዎቹምስል Lafargue Raphael/ABACA/IMAGO


«በዚህ ታሪካዊ ሁኔታ ውስጥ እንዴት መንግሥት መመስረት እንደሚቻል ማንሳታችን አይቀርም። መራኄ መንግሥቱ ከወዳጃቸው ከ(ማክሮ) ጋር በእርግጠኝነት ዋሽንግተን ውስጥ ስለሁኔታው በትንሹም ቢሆን የመነጋገር እድል ይኖራቸዋል። ለአሁኑ ግን እንደሚመስለኝ እውን እንዳይሆኑ ስንፈራቸው የነበሩት ባለመሆናቸው በተወሰነ ደረጃ እፎይታ አለ። በዚህ የምርጫ ውጤት ምን ይሆናል።ጊዜ የሚነግረን ይሆናል፤ፈረንሳይም ትወስናለች። ባለፈው ሳምንት እንደተነጋገርነው የጀርመንና የፈረንሳይን ግንኙነት በጣም ልዩ ነው። ግንኙነቱ የጀርመንና ፈረንሳይ እርቀ ሰላም መሠረት ፣በሰላምና በነጻነት የምንኖርባት አውሮጳን የምናረጋግጥበት ከምንጊዜውም በላይ ርስበርስ የምንቀራረብበት  አንኳር ጉዳይ ነው።  » 
ብሪስ ታይንቱረር ኢፕሶስ በተባለው የፖለቲካ ጥናት ተቋም የፖለቲካ ጉዳይ ተንታኝ ናቸው።በርሳቸው አስተያየት በአሁኑ ምርጫ አብልጫ ድምጽ ያገኘ የፖለቲካ ጎራ አለመኖሩ ችግሮችን ማስከተሉ አይቀርም። ምንም እንኳን ግራዎች ቢደሰቱም ወደፊት አጀንዳዎቻቸውን ማስፈጸም መቻላቸው ጥያቄ ውስጥ ነው። አሸናፊ ያልተለየበት የፈረንሳዩ የምክር ቤት ምርጫ እና አንድምታዉ


« በቀኝ ጽንፈኛው በRN በኩል ግልጽ ነው ተናደዋል፤ በግራዎቹ በኩል ደግሞ የመጀመሪያውን ቦታ በመያዛቸው ተደስተዋል። ይሁሉ ሆኖ ግን ያገኑት ድምጽ አንጻራዊ አብላጫ ነው። ፍጹም አብላጫ ድምጽ ያገኘ የለም። ስለዚህ ግራዎቹ የመታመኛ ድምጽ ማግኘቱ ይቸግራቸዋል፤አ,ጠቃላዩን መርሀ ግብራቸውን ማስፈጸምም እንዲሁ ስለዚህ የአሁኑ ደስታ መበሳጨትን ሊኢስከትል ይችላል። ለNR ያም ሆነ ይህ ብዙም ጥሩ ነገር የለውም። መሸነፉ በተወሰነ ደረጃ እፎይታ አስገኝቷል። ሽንፈቱም በጣም ትልቅ ሽንፈት ነው።» 
የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋብርኤል አታል ከምርጫው ውጤት በኋላ ከሃላፊነታቸውe እንደሚነሱ ቢያሳውቁም በማክሮን ተማጽኖ ለተወሰነ ጊዜ ስልጣናቸው ላይ እንደሚቆዩ ተናግረዋል። የጀርመንና የፈረንሳይ ግንኙነት አጥኚ ሮንያ ኬምፒን እንደሚሉት የእሁዱ ምርጫ ውጤት ለጀርመንና ለፈረንሳይ  ወዳጅነት በጣም ጥሩ ዜና ነው። እናም በርሳቸው አባባል የጀርመንና የፈረንሳይ ግንኙነት በእርግጠኝነት ይቀጥላል ማለት ነው። 

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮ
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮ ምስል Ludovic Marin/AFP/Getty Images


«እንደሚመስለኝ በጣም በጎ የሆነ የጀርመን-ፈረንሳይን ግንኙነት ማየት እንችላለን። ምንም እንኳን በፈረንሳይ የመንግሥት ምስረታ አስቸጋሪ ቢሆንም የፈረንሳይ ፓርላማ መጠናከሩ ፤በፓርላማ ምርጫ ውጤት መሠረት መንግሥት የመመስረት ጠንካራ ባህል  ያላት ጀርመን ከፈረንሳይ ጋር መወያየትን ያቀልላታል። የግንኙነታቸው መሠረትም አሁን በጣም ሰፊ ነው ብዬ አምናለሁ»
ማክሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምርጫው ውጤት ሊያሳድርባቸው የሚችለው ተጽእኖ ደግሞ ዛሬ በሚጀመረው የኔቶ አባል ሀገራት ጉባኤ ላይ ማረጋጋጫ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል። 
በሁለተኛ ዙር የፈረንሳይ ምክር ቤታዊ ምርጫ ውጤትና በተሰጡ አስተያየቶች ላይ ያተኮረው የዛሬው አውሮጳና ጀርመን ዝግጅታችን በዚሁ ያበቃል ደኅና ቆዩን

ኂሩት መለሰ 
ፀሐይ ጫኔ