1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአቶ ጌታቸው ረዳ ቅሬታ በምርጫ ቦርድ ውሳኔ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 4 2016

የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳ፥ ህወሓት የአመራሮቹ ስምና ፌርማ የያዘ ሰነድ ለቦርድ መቅረቡ በምርጫ ቦርድ መጠቀሱ በማንሳት፤ ይሁንና ይህ ትክክል አለመሆኑ፤ ለፓርቲው ምዝገባ ተብሎ በአመራሮች የተፈረመ ሰነድ እንደሌ፣ የገባው ሰነድ የተጭበረበረ መሆኑ ጠቅሰው ቦርዱ መልሶ እንዲመረምር ጥያቄ አቅርበዋል።

https://p.dw.com/p/4jKDN
የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ፕረዚደንትና የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳ
የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ፕረዚደንትና የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳምስል DW/Y. Geberegeziabeher

የአቶ ጌታቸው ረዳ ቅሬታ በምርጫ ቦርድ ውሳኔ

ህወሓት ክፍፍል ውስጥ ባለበት በዚህ ወቅት የጋራ የአቋም መግለጫ ያወጡት የትግራይ ወታደራዊ አዛዦች ከየትኛውም የፖለቲካ አሰላለፍ ነፃ እንደሚሆኑ አስታወቁ።  እነዚህ ወታደራዊ አዛዦች በትግራይ ፖለቲካ ውስጥ የውጭ ጣልቃ ገብነት ተቀባይነት የለውም ብለዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር እና የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ ሊደረግ ከታቀደው የህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ ራሳቸው ማግለላቸው አስታውቀዋል።

የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር እና የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ለህወሓት ሊቀመንር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል እና ለህወሓት ቁጥጥር ኮምሽን ሰብሳቢ ብለው የፃፉት እና ትላንት ለህዝብ የተሰራጨው ደብዳቤ እንደሚያሳየው፥ ይካሄዳል ተብሎ ከታቀድው የህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ ራሳቸው ማግለላቸው አስታውቀዋል። አቶ ጌታቸው ረዳ ከታቀደው የህወሓት ጉባኤ ራሳቸው ያገለሉት ሂደቱ ዴሞክራሲያዊ እና ሕጋዊ ባለመሆኑ ነው ብለዋል።  አያይዘውም የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ የማያውቀው የፓርቲው ምዝገባ ሂደት መኖሩም ጠቁመዋል። ይህ ደግሞ ተራ ስህተት ሳይሆን ህወሓት ለማፍረስ እና የትግራይ ህዝብ ትግል ከንቱ ለማድረግ ህውሓት ውስጥ ያለ ሕገወጥ ቡድን እየፈፀመው ያለ ተግባር ነው ሲሉ አቶ ጌታቸው ረዳ በደብዳቤያቸው ከሰዋል። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቅርቡ በተሻሻለው የምርጫ አዋጅ መሰረት 'በልዩ ሁኔታ' ለህወሓት ሕጋዊ እውቅና መስጠቱን ይታወቃል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቅርቡ በተሻሻለው የምርጫ አዋጅ መሰረት 'በልዩ ሁኔታ' ለህወሓት ሕጋዊ እውቅና መስጠቱን ይታወቃልምስል Ethiopian National Election Board

ትላንት ማምሻው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቅርቡ በተሻሻለውየምርጫ አዋጅ መሰረት 'በልዩ ሁኔታ' ለህወሓት ሕጋዊ እውቅና መስጠቱ ማስታወቁን ተከትሎ ዛሬ ለቦርድ በደብዳቤ ቅሬታ ያቀረቡት የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳ፥ ህወሓት የአመራሮቹ ስምና ፌርማ የያዘ ሰነድ ለቦርድ መቅረቡ በምርጫ ቦርድ መጠቀሱ በማንሳት፤ ይሁንና ይህ ትክክል አለመሆኑ፤ ለፓርቲው ምዝገባ ተብሎ በአመራሮች የተፈረመ ሰነድ እንደሌ፣ የገባው ሰነድ የተጭበረበረ መሆኑ ጠቅሰው ቦርዱ መልሶ እንዲመረምር ጥያቄ አቅርበዋል። ከዚህ በተጨማሪ አቶ ጌታቸው ለመላው የህወሓት አባላት በማለት ባሰራጩት ፅሑፍ ግለሰቦች በህወሓት ስም ሕገወጥ እንቅስቃሴ ላይ ተጠምደዋል ያሉ ሲሆን፥ ይህ እንዲቆም መላው አባል፣ አመራር እና የህወሓት ደጋፊ ሊንቀሳቀስ ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። 


 የህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ በአፋጣኝ እንዲደረግ በሚጠይቁ እና ህወሐት አሁን ባለው ቁመና ጉባኤ ማካሄድ አይችልም በሚሉት የፓርቲው አመራሮች መካከል ከነበረው ልዩነት በተጨማሪ አሁን ደግሞ በፓርቲው እውቅና ዙርያ አመራሩ ሌላ ውዝግብ ውስጥ ገብሏል። በመቐለ በተደረገ አንድ መድረክ የተናገሩት የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳ የህወሓት አመራር የሚያደርጋቸው ስብሰባዎች ፍሬ አልባ እና የመጠቃቃት መድረኮች ሆነዋል ሲሉ ገልፀዋል። 

አቶ ጌታቸው "ስብሰባዎቻችን፣ ሽምግልናዎቻችን ምንም ዓይነት ትርጉም እንደሌላቸው አረጋግጠናል። ስብሰባ በሐሳብ ላይ የተመሰረተ ሲሆን ነው ትርጉም የሚኖረው። ሓሳብ ከሌለህ የህዝብ ችግር አትፈታም ብቻ ሳይሆን ሁሉም ነገር መጠቋቆር ብቻ ነው እየሆነ ያለው። አንዱ በሌላው ላይ ነጥብ ሊያስቆጥር ካልሆነ ለህዝብ የሚያመጣው ትርጉም የለም" ብለዋል።

በትግራይ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ የሚመክር የውይይት መድረክ
በትግራይ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ የሚመክር የውይይት መድረክምስል Million Haileslasse/DW

በሌላ በኩል  የህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ በአፋጣኝ እንዲካሄድ  ከሚወተውቱት መካከል የሆኑት የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ አባል አቶ ተኽላይ ገብረመድህን "የህዝብ ችግር ሊፈታ ከሆነ አመራር ሊስተካከል ይገባል። ባለንበት እንቀጥል ከሆነ የህዝብ ስቃይ ነው እየጨመርን ያለነው። በተግባር እያየነው ያለነውም ይህንኑ ነው። በተለይም ይህ አሁን ያለው አመራር ህወሓት እጁ ላይ እያጠፋች ነው። ይህ ተገቢ አይደለም። የትግራይ ጥቅም ለማረጋገጥ የግድ አመራር ሊስተካከል ይገባል። የግድ ህወሓት ሊስተካከል ይገባል" ብለዋል። 

የህወሓት ክፍፍል በሰፋበት በዚህ ወቅት ትላንት ማታ የጋራ መግለጫ ያወጡት የትግራይ ወታደራዊ አዛዦች በትግራይ የሚደረግ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ሰላማዊ እንዲሆኑ ጠይቀዋል። ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በነበረ ጦርነት ጦርነቱ የመሩት እነዚህ አሁን ላይ የትግራይ የፀጥታ ሐይሎች ተብለው የሚታወቁ ከፍተኛ ወታደራዊ መሪዎች በትግራይ ፖለቲካ ውስጥ የውጭ ጣልቃ ገብነት ተቀባይነት እንደሌለውም አስታውቀዋል። በኮነሬል ገብረ ገብረፃድቅ ከቀረበው የወታደራዊ አመራሮቹ የአቋም መግለጫ፥ "በትግራይ የሚካሄድ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በሰለጠነ እና በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲፈፀም፣ ሁሉም ዓይነት አስተሳሰብ ዕድል እንዲያገኝ ማድረግ ፅኑ እምነታችን ነው። ከዚህ አልፎ የትግራይ ሰላም፣ ድህንነት እና አንድነት የሚነካ እንደማንቀበል እየገለፅን የትግራይ የፀጥታ ሐይሎች ከሆነ ይሁን የፖለቲካ አሰላለፍ ነፃ ሆነን፣ የትግራይ ጥቅምና ድህንነት ለድርድር እንደማናቀርብ፣ የትግራይ ፖለቲካ በትግራይ ልጆች እንጂ ከውጭ የሚጫን እንደማንቀበል እየገለፅን፣ በዚህ በኩል የሚፈጠር ጉድለት እንደምንታገለው እናረጋግጣለን" ብለዋል።
ወታደራዊ አዛዦቹ አሁን ይህን ይበሉ እንጂ ከዚህ ቀደም ህወሓት ያካሂዳቸው በነበሩ ስብሰባዎች በቀጥታ ሲሳተፉ እንደነበር ይታወቃል። ይህ የአሁኑ መግለጫቸው የከዚህ ቀደሙ ተሳትፎአቸው ትክክል መሆን አለመሆኑን በግልጽ አልጠቆመም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር በክልሉ የተለያዩ መስርያቤቶች እና የተለያዩ ዞኖች ከፍተኛ አመራርነት ሆነው የቆዩ ባለስልጣናት በጡረታ እያሰናበተ መሆኑ ተገልጿል። ይህ እርምጃ ከወቅታዊ የህወሓት የውስጠ ፓርቲ መካረር ጋር ግንኙነት ይኑረው አይኑረው የታወቀ ነገር የለም።
ሚልዮን ሃይለስላሴ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር