1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፋጣኝ መፍትሄ ለወባ ወረርሽን

ቅዳሜ፣ መስከረም 19 2016

"በዞን ደረጃ በወር እስከ 20ሺ በወባ የሚያዙ ሰዎችም ይመዘገባሉ፡፡ እንደ ቆንዳላና ቤጊ ወረዳ ደግሞ በሳምንት ከ1,000 እስከ 3,000 ሰዎች ላይ ወባ እየታየ ነው፡፡ በቤጊ ሆሲፒታል ለምሳሌ ወባን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያት ሞት ይመዘገባል፡፡ በዚህን ሳምንት 2 ሰዎች በወባ በሆስፒታሉ ህይወት ማለፉን ሪፖርት ደርሶናል፡፡"

https://p.dw.com/p/4WzuE
Asiatische Tigermücke
ምስል H. Schmidbauer/blickwinkel/picture alliance

በምዕራብ ወለጋ በወር እስከ 20 ሺህ ሰዎች በወባ እየተጠቁ ነው

ከምዕራብ ወለጋ ዞን ባለፉት 2 ወራት የወባ በሽታ በስፋት ከታየባቸው ስፍራዎች አንዱ  የቆንዳላ ወረዳ ሲሆን በወረዳው ስር  በ10 በቀሌዎች ውስጥ ታይተዋል፡፡ በወረዳው በአሁኑ ወቅት ወባ በሽታ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ያነጋገርናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ በዚህ አካባቢ ከዚህ ቀደም ለረጅም ጊዜ የጸጥታ ችግር የነበረበት ቦታ በመሆኑም የጤና ተቋማት በሙሉ አቅማቸው አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነም ተገልጸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ባለፈው ዓመት አርሶ አደሩ በግብርና ስራ ላይ ባለመሰማራቱ ህጻናት በምግብ እጥረትም ሳቢያ ጉዳት እየደረሰባቸው እንደሚገኝ ነዋሪዎቹ አመልክተዋል፡፡ 
"ወባ በጣም ተስፋፍተዋል፡፡ በዚህ አካባቢ ወባ ስርጭት ከፍተኛ ነው፡፡ በወረርሽኝ ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ በትንሹ በቀን 20 እና 30 ህጻናት ወደ ህክምና ተቋማት ይሄዳሉ፡፡  ህጻናት ከምግብ እጥረት ምክንያት ወባን መቋቋም አይችሉም፡፡ ከኑሮ ወድነት ጋር ተያይዞ የምግብ እጥረትም አለ፡፡ ባለፈው ዓመት ባለመታረሱ ምርት የለም፡፡ የምግብ እጥረትም በስፋት ይስተዋላል፡፡ አስቸኳይ ምላሽ ይፈልጋል፡፡"
በቆንዳላ ከሳምንት በፊት በቀይ መስቀል በኩል የጸረ ወባ ኬሚካል ለከተማው መሰጡት  ሌላው የወረዳ ነዋሪ ለዲዳቢሊው ተናግረዋል፡፡ ከህክምና ተቋማት በርቀት ላይ በሚገኙ ስፍራዎች አሁንም ወረርሽኝ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል፡፡ 
" በጊሚ ጋባ፣ሹራ ማራሞና ባምሶ የተባሉ ቦታዎች ላይ በሰው ላይ ጉዳት አድርሰዋል፡፡ በገሚ ጋባ ከትናንት በስቲያየ2 ህጻናት ህይወት አልፈዋል፡፡ የምግብ እጥረትም በመኖሩ ህጻናት ላይ  በብዛት ጉዳት አድርሰዋል፡፡ ቀይ መስቀል የተወሰኑ መድሀኒት ካመጡ በኃላ ሰዎች ህክምና ማግኘት  ጀምረዋል"
በቆንዳላ ወረዳ አጎራባች በሆነው ወረዳ ውስጥ የሚገኘው ቤጊ ሆስፒታል በቅርበት ለሚገኙ ወረዳዎችም ጭምር አገልግሎት ይሰጣል፡፡ የቤጊ ወረዳ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይረክተር የሆኑት  ዶ/ር ብርመዱ መኮነን ወደ ሆስፒታላቸው ከሚመጡት ሰዎች  90 ከመቶው  በወባ በሽታ ታመው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የወባ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር የሚረዱ የተወሰኑ ድጋፎች ለሆስፒታሉ መደረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ ሆኖም በቂ አለመሆኑንና የወባ ስርጭት መጠን አሁንም መጨመሩን ተናግረዋል፡፡ 
"የወባ ስርጭትን ለመቆጣጠር በተወሰኑ መልኩ ተሞክረዋል፡፡ ነገር ግን በወባ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ግን አልቀነሰም አሁንም ጨምረዋል፡፡ በተጨማሪም ሰዎች የተመጣጠነ ምግብ እጥረም እያጋጠማቸው ስለሆነ ነው  በወባ የሚያዙ ሰዎችን በቀላሉ ይጎዳሉ፡፡  ድጋፍም ያስፈልጋቸዋል፡፡ ወደ ሆስፒታል የሚመጡ ሰዎች በጣም ከተዳከሙ በኃላ በመሆኑ ለከፍተኛ ጉዳት ሊዳርጋቸው ይችላል፡፡ ስለዚህ ሰዎች በቶሎ  ወደ ህክምና ተቃማት መምጣት እንዳለባቸወ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡  በቀን በሆስፒታሉ ከ50 እከ 59 ሰዎች ላይ ወባ እየታየ ነው ዝቅተኛ አንድ አንዴ በቀን 49 ሰው ላይ የሚታይበት ጊዜ አለ፡፡ "
የምዕራብ ወለጋ ዞን ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሰለሞን ጫላ በበኩላቸው ወባን ለመከላከል ብዙ ጥረት መደረጉን ገልጸው በተለያዩ ጊዜ ወባን ለመከላከል የሚሰሩ ስራዎች በጸጥታ ችግርና በልዩ ልዩ ምክንያቶች በሚፈለገው መልኩ አለመሆን  የበወባ በሽታ ስርጭት እንዲጨምር ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ የወባ በሽታ ስርጭት በተለይም በሁለቱ ወረዳዎች (ቤጊና ቆንዳላ) ከፍተኛ ነው፡፡ 
"በዞን ደረጃ በሳምንት ከ7,000 እስከ 8,000 ሰዎች በወባ እንደሚያዙ እየተረጋገጠ ነው፡፡ በወር ደግሞ እስከ 20ሺ በወባ የሚያዙ ሰዎችም ይመዘገባሉ፡፡ እንደ ቆንዳላና ቤጊ ወረዳ ደግሞ  በሳምንት ከ1,000 እስ 3,000 ሰዎች ላይ ወባ እየታየ ነው፡፡ በቤጊ ሆሲፒታል ለምሳለ ወባን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያት ሞት ይመዘገባል፡፡ በዚህን ሳምንት 2 ሰዎች በወባ በሆስፒታሉ ህይወት ማለፉን ሪፖርት ደርሶናል፡፡"
በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ዞኖች ውስጥ ወባ በወረርሽኝ መልክ መከሰቱን ከዚህ ቀደም የክልሉ ጤና ቢሮ ገልጸዋል፡፡ የቢሮው መረጃ እንደሚያሳየው በክልሉ በ6 ዞኖች፣በ7 ከተሞችና በ117 ወረዳዎች ወባ በወረርሽኝ መልክ ታይቷል፡፡ 
ነጋሳ ደሳለኝ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

የወባ ትንኝ
በወባ ትንኝ ንክሻ የሚተላለፈውን ይህን በሽታ ለመከላከል አካባቢን ከአቆሩ ውሃና ረግረጋማ ቦታዎች ማጽዳት ያስፈልጋል።ምስል Tom Ervin/Getty Images
የወባ ትንኝ ንክሻ መከላከያ
የወባ ትንኝ ንክሻን ለመላከል ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች አልጋዎን በዚህ መልኩ መሸፈን እንደሚገባ ባለሙያዎች ይመክራሉ።ምስል Jonathan Nackstrand/AFP