1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአየር ንብረት ለውጥ ያባባሰው የወባ ወረርሽኝ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 4 2015

በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል በዓመት ውስጥ ከሁለት የዝናብ ወቅቶች በኋላ የወባ ወረርሽኝ እንደሚቀሰቀስ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። የዩናይትድ ስቴትስ የረድኤት ድርጅት USAID መረጃ 70 በመቶ በሚሆነው የኢትዮጵያ ግዛት የወባ በሽታ ይከሰታል። በዚህ ምክንያትም ከጠቅላላው ሕዝብ 52 በመቶው ለወባ በሽታ የተጋለጠ ነው።

https://p.dw.com/p/4TiVc
Mücke
ምስል El Mundo/IMAGO

የአየር ንብረት ለውጥ ያባባሰው የወባ ወረርሽኝ

የወባ ትንኝ ለመራባት ሞቃት አካባቢ እና እርጥበት እንደሚያስፈልጋት ነው የሚነገረው። ለዚህም ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ከዝናብ ወቅቶች ማለቂያ ላይ ብዙ ሰዎች በወባ የሚያዙት። የኅብረተሰብ ጤና ሳይንስ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር መኮንን አይችሉህም ኢትዮጵያ ውስጥ የወባ በሽታ በዋነኛነት በሁለት ዓበይት ወቅቶች ማለትም የበልግ ዝናብ እና ክረምት ዝናብ ማብቂያ ላይ መሆኑን ያመለክታሉ። ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ ታቁሮ የከረመው ውኃ እስከ ጥር ወር ድረስ ሳይደርቅ የሚቆይባቸው አካባቢዎች በመኖራቸው እንደሆነ ነው የተናገሩት። የወባ በሽታ ኢትዮጵያ ውስጥ ወቅቶችን ጠብቆ የሚከሰት መሆኑ እንዳለ ሆኖ ዓመቱን ሙሉ ወባ የማይጠፋባቸው አካባቢዎች መኖራቸውን ዶክተር ወንድወሰን አሞኘ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ሳይንስ ኮሌጅ የውስጥ ደዌ እና ተላላፊ በሽታዎች ተመራማሪ እና ተባባሪ ፕሮፌሰር በበኩላቸው ያስረዳሉ።

Moskitoschutz in Togo
የወባ ትንኝን ለመከላከል አንዱ መንገድ፤ አጎበርምስል picture alliance/Photononstop

በአሁኑ ጊዜ ለሚታየው የወባ መስፋፋትም የበልግ ዝናብ ቀደም ብሎ ጀምሮ በመካከሉ የመቋረጥ ነገር ስለነበር ውኃ በያዙ አካባቢዎች ትንኟ የመፈልፈል ዕድል እንድታገኝ ማድረጉንም አመልክተዋል። በተለይ የወባ አስተላላፊ ትንኝን በተመለከተም ዶክተር ወንድወሰን እንዲህ ይላሉ፤ «ትንኟን አኑፉሊስ ነው የምንላት፤ አኑፉሊስ አረቢያንሲስ የምትባል ነች በዋነኛነት ወባን አስተላላፊ። ይቺ ደግሞ ከቤት ውጪም ከቤት ውስጥም ሰውንም እንስሳትንም የመንከስ ባህሪ ስላላት በሽታውን በቀላሉ ማስተላለፍ ትችላለች።»

በዓለም አቀፍ ደረጃ በተጨባጭ መታየት የጀመረው የአየር ንብረት ለውጥ ውጤት የወባ በሽታ ወትሮ ባልነበረባቸው አካባቢዎች ሳይቀር እንዲከስት እያደረገው እንደሆነ መረጃዎች እየወጡ ነው። ዶክተር ወንድወሰንም ፤ ይኽንኑ ነው ያረጋገጡት። ዶክተር መኮንንም እንዲሁ ከዚህ በፊት ወባ ይከሰትባቸው ባልነበሩ አካባቢዎችም በሽታው መገኘት መጀመሩ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር እንደሚያያዝ ተናግረዋል።

Äthiopien Adama | USAID Programm gegen Malaria
ወባን ስለማጥፋት ከሚካሄዱ ዘመቻዎች አንዱምስል Seyoum Getu/DW

ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ወቅት ወባን ስለማጥፋት ይነገር እንዳልነበር አሁን ወረርሽኙ መስፋፋቱ ነው የሚገለጸው። በቅርቡ የወጡ መረጃዎች በተለይ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች እንደ ምዕራብ እና ምሥራቅ ወለጋ፤ ቄለም እና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች ከ270 ሺህ ሰዎች በላይ በወባ በሽታ መጎዳታቸው ተገልጿል። የወባ ስርጭት እንዳይስፋፋና በሽታው የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ሊደረጉ የሚገቡ ጥንቃቄዎችን በተመለከተ ዶክተር መኮንን፤ ስለጤናው ችግር ማኅበረሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረጉ ወሳኝ ነው ባይ ናቸው።

ዶክተር ወንድወሰን በተለይ የወባ ህመም ነፍሰጡር እናቶች እና ሕጻናትን ይበልጥ ሊጎዳ እንደሚል ያመለክታሉ። ዓመቱን ሙሉ የወባ በሽታ የሚከስትባቸው እንደ ጋምቤላ፤፣ መተከል፣ መተማ፣ ሁመራ፤ የጅቡቲ ድንበር አካባቢዎችን የመሳሰሉ ቆላማ ቦታዎች የሚኖሩ እና ለወባ የተጋለጡ ወገኖች ሰውነታቸው በሽታውን የመቋቋም አቅም እንዳዳበረ ነው ዶክተር ወንድወሰን የሚገልጹት። እንዲያem ሆኖ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረጉ ለሁሉም ይመከራል።

የወባ በሽታ ከመላው አውሮጳ በ20ኛው ክፍለ ዘመን እንደተወገደ ይነገራል። ሆኖም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ወባ ካለባቸው ሃገራት ከመጡ ሰዎች ላይ ብቻ ሳይሆን እዚህ አውሮጳ ፈረንሳይ እና ግሪክ ውስጥ ከአምስት ሰዎች በላይ መያዛቸውን የአውሮጳ የበሽታ መከላከል እና መቆጣጠሪያ ማዕከል ይፋ አድርጓል። ለዚህ ደግሞ በምክንያትነት የአየር ንብረት ለውጥ ይጠቀሳል። ለሰጡን ማብራሪያ ባለሙያዎቹን እናመሰግናለን።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ