1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በእሥር ላይ የቆዩ ከያንያን ተፈቱ፣ ጦርነት ይቁም የሚል ሰልፍ ያስተባበሩ ሰው ተሰደዱ

ሰኞ፣ ሰኔ 17 2016

የኢሕአፓ ፕሬዝዳንትን ጨምሮ በገንዘብ ዋስትና እንዲለቀቁ ፍ/ቤት የወሰነላቸው ዘጠኝ ሰዎች፤ በፖሊስ የተጠየቀባቸው ይግባኝን ውድቅ አድርጎ የዋስትና መብታቸው እንዲከበር የፌ/ ጠ/ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ወሰነ። የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት የሰጠውን ብይን በማጽናትፖሊስ የጠየቀውን ይግባኝ ውድቅ አድርጓል።

https://p.dw.com/p/4hR91
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምስል Seyoum Hailu/DW

በእሥር ላይ የቆዩ ከያንያን ተፈቱ፣ ጦርነት ይቁም የሚል ሰልፍ ያስተባበሩ ሰው ተሰደዱ

ለወራት በእሥር ላይ የቆዩ ከያንያን ተፈቱ፣ ጦርነት ይቁም የሚል ሰልፍ ያስተባበሩ ሰው ተሰደዱ

የኢሕአፓ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ዝናቡ አበራን ጨምሮ በገንዘብ ዋስትና ከእሥር እንዲለቀቁ የሥር ፍርድ ቤት የወሰነላቸው ዘጠኝ ሰዎች፤ በፖሊስ የተጠየቀባቸውን ይግባኝ ውድቅ በማድረግ የዋስትና መብታቸው እንዲከበር የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ወሰነ። ሰበር ሰሚ ችሎቱ፣ የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት የሰጠውን ብይን በማጽናት ነው ፖሊስ የጠየቀውን ይግባኝ ውድቅ ያደረገው። 

በተመሳሳይ ማህበራዊ ጉዳዮችን የሚዳስሰው "እብደት በሕብረት" የተባለው የመድረክ ተውኔት ተዋናይ አመኑኤል ሀብታሙ ከ ሁለት ወራት እሥር በኋላ እንዲሁም አዘጋጁ ዳግማዊ ፈይሳ እና ሌሎችም ዛሬ ከእሥር መለቀቃቸውን ጠበቃቸው ለዶቼ ቬለ አረጋግጠዋል። 

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት፣ የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት በእነ ፕሮፌሰር ዝናቡ አበራ እና ሌሎች ዘጠኝ ሰዎች ላይ የሰጠውን ብይን በማጽናት ፖሊስ የጠየቀውን ይግባኝ ውድቅ አድርጎ ግለሰቦቹ ከእሥር እንዲለቀቁ የሥር ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ አጽንቶታል ሲሉ ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ ተናግረዋል። 

የኢሕአፓ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ዝናቡ አበራን ጨምሮ በአዋሽ አርባ ታሥረው ከነበሩ 17 ሰዎች መካከል፣ ግንቦት 30 ቀን 2016 ዓ. ም ወደ አዲስ አበባ ተዛውረው የቆዩት ዘጠኝ ግለሰቦች የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ያለፈው ሰኞ በገንዘብ ዋስትና እንዲወጡ ወስኖላቸው፣ ለአምስቱ ተጠርጣሪዎች ሰላሳ ሺህ ብር፣ ለአራቱ ደግሞ የሃያ ሺህ ብር ዋስትና ተከፍሎ ሳይፈቱ ለአንድ ሳምንት እስከ ዛሬ በእሥር ቆይተዋል። 

የዋስትና አፈፃፀም ከተከናወነ በኋላ ፖሊስ ይግባኝ መጠየቁን ተከትሎ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አርብ እለት በነበረው ቀጠሮ "መዝገብ ጠፍቶ መወሰን አልቻልኩም" በሚል ምክንያት ጉዳዩን አሳድሮት ብይን ለመስጠት ነበር ለዛሬ ሰኞ ቀጥሮ የሰጠው። 
 

ጦርነት ይቁም የሚል ሰልፍ ያስተባበሩ ሰው ተሰደዱ
 

አቶ ዳንኤል ሽበሺ
አቶ ዳንኤል ሽበሺምስል DW/G. Tedla

እነዚህን ግለሰቦች ጨምሮ ከዚህ በፊት ታሥረው የተፈቱት አቶ የሺዋስ አሰፋ፣ መጋቢ ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት፣ ለእሥር የተዳረጉት ሕዳር 30 ቀን 2016 ዓ. ም "ጦርነት ይቁም ሰላም ይስፈን፣ ሁሉን አቀፍ ውይይት እና ድርድር ከታጣቂ ኃይሎች ጋር ይካሄድ" የሚሉ እና ሌሎች መፈክሮችን የሚያስተጋባ ሰላማ ሰልፍ ለማድረግ በመንቀሳቀሳቸው ነው። ይህንን በመንግሥት የተከለከለውን ሰላማዊ ሰልፍ ካስተባበሩት 13 ፖለቲከኞች አንዱ የነበሩት አቶ ዳንኤል ሺበሺ በተደጋጋሚ ደረሰብኝ ባሉት ወከባ እና እንግልት ብሎም ለሕይወታቸው በመሥጋት ሀገር ጥለው መሰደዳቸውን ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። "ለመውጣቴ ምክንያት የሆነው ጦርነት ይቁም ሰላም ይስፈን ከሚለው ጥያቄ ጋር  በተያያዘ ነው"  

 

የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች መፈታት

ማህበራዊ ጉዳዮችን የሚዳስሰው "እብደት በሕብረት" የተባለው የመድረክ ተውኔት ተዋናይ አመኑኤል ሀብታሙ፣ አዘጋጁ ዳግማዊ ፈይሳ እና የሌሎችም ተጠርጣሪ ከያንያን ያለፈው ሐሙስ የዋስትና መብታቸው ቢከበርም ከቀናት ቆይታ በኋላ ዛሬ መለቀቃቸውን ጠበቃቸው አያሌው ቢታኔ ገልፀዋል። "ሕገ መንግሥታዊ የሆነውን የዋስትና መብት ፍርድ ቤት ክፍለ ደ በኋላ በዘፈቀደ መልኩ ላለፉት ሦስት አራት ቀናት በላይ ያለ አግባብ ተይዘው የተቀመጡበት አግባብ" መታረም አለበት ብለዋል።
 

ዕብደት በሕብረት
ዕብደት በሕብረት ምስል privat

የመብት ድርጅቶች ውትወታ
 

ሰብዓዊ መብት ላይ የሚሠሩ የሲቪክ ድርጅቶች አሁንም ጋዜጠኞች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ አርቲስቶች እና ፖለቲከኞች በዘፈቀደ እንደሚታሰሩ በመግለጽ ይህን መሰሉ አካሄድ እንዲታረም፣ የታሰሩትም በሙሉ እንዲፈቱ ውትወታ ከማድረግ አልቦዘኑም።

 

ሰለሞን ሙጬ

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ