1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢትዮጵያ የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች እንዲከፈቱ መፈቀዱ

ሰኞ፣ ነሐሴ 6 2016

ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መመሪያ መሠረት የውጭ ምንዛሪ ቢሮ ለመክፈት ዝቅተኛ 15 ሚሊዮን ብር ካፒታል መቅረብ የሚያስፈልግ ሲሆን በተጨማሪም በዝግ የባንክ ሒሳብ ተቀማጭ የሆነ 30 ሚሊዮን ብር አብሮ መኖር አለበት።

https://p.dw.com/p/4jOAd
Äthiopien I National Bank in Addis Abeba
ምስል Seyoum Getu/DW

የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች እንዲከፈቱ መፈቀዱ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎችን ለመክፈት የሥራ ፈቃድ ማመልከቻዎችን መቀበል ጀመሩን አስታውቋል።

ይህንን ሥራ ለማከናወን 15 ሚሊዮን ብር ካፒታል እና በባንክ በዝግ ተቀማጭ የተደረገ 30 ሚሊዮን ብር ያስፈልጋል ተብሏል።

በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ አንድ የኢኮኖሚ ባለሙያ ፈቃድ ወስደው የሚሠሩት እነዚህ የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች "የገንዘብ እጥበትን ለመቀነስ ይረዳሉ፣ የትይዩ ገበያውን እንቅስቃሴ ያዳክማሉ፣ የውጭ ምንዛሪ ግብይቱን ተወዳዳሩ ያደርጋሉ" ብለዋል። ይህም በሀገር እድገት ላይ ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዲይዙ ያደርጋል በማለት ገልፀዋል።

እርምጃው ምን ፋይዳ ይዞ ይመጣል?

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የኢትዮጵያ ዜግነት ያላቸው በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ የሚኖሩ እንዲሁም የሌላ ሀገር ዜግነት ያላቸው ግን ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሆኑ ሰዎች መስፈርቶችን አሟልተው ሲቀርቡ የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች መክፈት የሚያስችላቸውን ፍቃድ እንደሚያገኙ ገልጿል። ባንኩ ከሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ. ም ጀምሮ ሥራ ላይ ባዋለው የውጭ ምንዛሪ መመሪያ ቁ.01/2016 መሠረት ይህንኑ ሥራ መሥራት የሚፈልጉ ሁሉ የሥራ ፈቃድ ማመልከቻ እንዲያቀርቡ ጥሪ አቅርቧል። ይህ እርምጃ ምን ፋይዳ ይዞ ይመጣ ይሆን? በሚል የጠየቅናቸው የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ኢድሪስ ሰዒድ፤ ብሔራዊ ባንክ ጥብቅ ቁጥጥር እያደረገ እስከተንቀሳቀሱ ድረስ በውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም ረገድ ጠብቆ የነበረውን ቁጥጥር ያላላሉ፤ የንግድ ሥራን በማሳለጥ ረገድም "ትልቅ ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽዖ ይኖራቸዋል" ብለዋል። 

የውጭ ምንዛሪ ቢሮ ለመክፈት ዝቅተኛ 15 ሚሊዮን ብር ካፒታል ያስፈልጋል
የውጭ ምንዛሪ ቢሮ ለመክፈት ዝቅተኛ 15 ሚሊዮን ብር ካፒታል ያስፈልጋልምስል Gregor Macak Martin/dpa/CTK/picture alliance

የባንኮች የወቅቱ የውጭ ምንዛሪ ተመን ግብይት 

ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ግብይት በገበያው እንዲመራ መወስኗን ተከትሎ ላለፉት ሁለት ሳምንታት ይሄው ግብይት በባንኮች የመግዣ እና መሸጫ ተመን እየተመራ ነው። እስካሁን የአንድ የአሜሪካ ዶላር ከግል ባንኮች ከፍተኛው የመግዣ ዋጋ 107 ብር ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አንዱን ዶላር በ101.8 ብር ገዝቶ በ111.9 ብር እየሸጠ መሆኑን አስታውቋል።

በሌላ በኩል የልማት እና የሥራ ፈጠራዎች ላይ ላተኮሩ ፕሮጀክቶች የገንዘብ እና የቴክኒክ ድጋፍ የሚያደርገው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ይህንኑ ሥራ በይፋ የተቀላቀለ ሲሆን አንዱን የአሜሪካ ዶላርበ108.2 ብር ገዝቶ በ 116 ብር በመሸጥ በሀገሪቱ ከፍተኛውን የምንዛሪ ዋጋ የሰጡ መሆኑን ዛሬን ጨምሮ ሰሞኑን ያወጣቸው የምንዛሪ ተመን መረጃዎች ያመለክታሉ። የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ኢድሪስ እንደሚሉት የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ሲከፈቱ አሁን በባንኮች በብቸኝነት እየተዘወረ ያለው የውጭ ምንዛሪ ግብይት ለቀቅ ብሎ ተወዳዳሪ እንዲሆን ያግዛሉ።

የዚህ ውሳኔ ተገቢነትና ለሥራው የሚያስፈልገው መነሻ ሀብት

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ ውሳኔው የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ ለውጭ ኢንቨስትመንት ለመከፈት ተብሎ የተከናወነ እና ዘርፉን ተወዳዳሪ ለማድረግ ባንኩ ጀምሮታል ላሉት ለውጥ ቁርጠኛ የመሆኑ ማሳያ አድርገውታል። የኢኮኖሚ ባለሙያው ደግሞ ይህ እርምጃ ሕገ ወጥ የገንዘብ እጥበትን ጭምር ለመግታት ይበጃል ባይ ናቸው።

ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መመሪያ መሠረት የውጭ ምንዛሪ ቢሮ ለመክፈት ዝቅተኛ 15 ሚሊዮን ብር ካፒታል መቅረብ የሚያስፈልግ ሲሆን በተጨማሪም በዝግ የባንክ ሒሳብ ተቀማጭ የሆነ 30 ሚሊዮን ብር አብሮ መኖር አለበት።
ሰሎሞን ሙጬ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ኂሩት መለሰ