1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሀረ ሀር-ሰዴ የኢሬቻ በዓል በቢሾፍቱ ተከበረ

እሑድ፣ መስከረም 27 2016

ዛሬ ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ቢሾፍቱ ውስጥ በሚገኘው የሆራ ሀርሰዲ ሀይቅ ላይ በህብረት የተገኙት የኦሮሞ አባገዳዎች የኢሬቻውን ስነስርዓት በምርቃት የከፈተቱት ስለ ሰላም በተጣራና ሰላምን በሚናፍቅ ደምጸት ነው፡፡

https://p.dw.com/p/4XGVM
ኢሬቻ በቢሾፍቱ
ኢሬቻ በቢሾፍቱ ከተማ ሲከበርምስል Seyoum Getu/DW

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የታደሙበት የኢሬቻ በዓል ዛሬ በቢሾፍቱ በድምቀት ተከብሮ ውሏል።

ዛሬ ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ቢሾፍቱ ውስጥ በሚገኘው የሆራ ሀርሰዲ ሀይቅ ላይ በህብረት የተገኙት የኦሮሞ አባገዳዎች የኢሬቻውን ስነስርዓት በምርቃት የከፈተቱት ስለ ሰላም በተጣራና ሰላምን በሚናፍቅ ደምጸት ነው፡፡ የቱላማ አባገዳ ጎበና ሆላ ስርዓቱን በምርቃት በከፈቱበት ወቅት ስለ ሰላም አብዝተው በመጣራት ዓመቱ ወደ ሰላም የምንሸጋገርበት ይሁን ሲሉ ለአባገዳዎቹ ምኞት አጽእኖት ሰጥተዋል፡፡

ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብም እርጥብ ሳር ይዘው በየቡድን እየሆኑ በኢሬቻው ህብረዜማ ስርዓቱ ወደሚከወንበት ሆራ ሀርሰዲ ሲተሙ ነበር፡፡ ታዳሚያኑ “ሆ..ያ..ማሬዎ…” እያሉም ከፍ ባለ ዜማ አከባቢውን አድመቀውትም ውለዋል፡፡

በኦሮሞ ባህላዊ አልባሳት ያጌጡ ወጣቶች በኢሬቻ በዓል ላይ ተሳታፊ ሆነዋል።
የዘንድሮ ሆራ ሀርሰዲ ኢሬቻ ተሳትፎ የመጀመሪያዋ የሆነላት የአርሲ አሰላ ነዋሪዋ ወጣት ሰሚራ መሃመድም የመጀመሪያዋ የኢሬቻ ተሳትፎዋ በመልካም ትዝታዎች የሚታወሱ እንደሆነላት ታስረዳለች፡፡ምስል Seyoum Getu/DW

በርግጥ የበዓሉ ታዳሚያኑ ከትናንት ከሰኣት ጀምሮም የቱሪስት መዳረሻ የምትባለውን ቢሾፍቱ ከተማን አጨናንቀዋት ውለው አድረዋል፡፡ ከኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ለገጣፎ ክፍለ ከተማ መጥቶ በስርዓቱ ላይ የታደመው ወጣት ታሪኩ በዳሳ ከነዚህ በሚሊየን ከሚቆጠሩ ተሳታፊዎች ነው፡፡ ታሪኩ ለዶይቼ ቬለ በሰጠው አስተያየት የዘንድሮ ኢሬቻ ከወቀትሮም በተለየ ደማቅ እና የተረጋጋ ሰላመዊ ነው ብሏል፡፡የኦሮሞ ባህላዊ አልባሳት ቅድ ባለሙያዎቹ እንስቶች “እንደሚታየው ህዝብ ወደዚህ ሆራ ስፍራ እየተመመ ነው እንጂ ብዛት ያለው እንደውም ገና እዚህ አልደረሰም፡፡ የህዝቡ ብዛትም ከአምና ራሱ እጥፍ ይሆናል፡፡ እኔ ከትናት ማታ ጀምሮ እዚህ ነበበርኩ፡፡ ቢሾፍቱ ከማታ ጀምሮ እንዳየሄው ደማቅ ብላለች፡፡”

የኦሮሞ አባ ገዳ በሆረ አርሰዴ ኢሬቻ በዓል ላይ ምርቃት ሲያቀርቡ
ዛሬ ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ቢሾፍቱ ውስጥ በሚገኘው የሆራ ሀርሰዲ ሀይቅ ላይ በህብረት የተገኙት የኦሮሞ አባገዳዎች የኢሬቻውን ስነስርዓት በምርቃት የከፈተቱት ስለ ሰላም በተጣራና ሰላምን በሚናፍቅ ደምጸት ነው፡፡ ምስል Seyoum Getu/DW

የዘንድሮ ሆራ ሀርሰዲ ኢሬቻ ተሳትፎ የመጀመሪያዋ የሆነላት የአርሲ አሰላ ነዋሪዋ ወጣት ሰሚራ መሃመድም የመጀመሪያዋ የኢሬቻ ተሳትፎዋ በመልካም ትዝታዎች የሚታወሱ እንደሆነላት ታስረዳለች፡፡ “የዘንድሮ ኢሬቻ እንዳየሁት በጣም ደስ ይላል፡፡ እንደ የመጀመሪያ ተሳትፎዬ ደስ የሚል አንድነት አይቻለሁና ሰላምና መተባበርን ያመጣል ብዬ አስባለሁ፡፡”የኢሬቻ ሆራ-ፊንፊኔ በደማቅ ሁኔታ ተከበረ

በኢሬቻ ሆራ አርሰዲ ተሳትፎያቸው ዘንድሮ ለተከታታይ 9ኛ ጊዜ ከሚኖሩበት አዲስ አበባ እየተመላለሱ መከወናቸውን የሚያስረዱት አቶ ዳኒኤል በቀለ ደግሞ በነዚህ ጊዜያት እንደታዳሚ በኢሬቻ በበጎና ፈተና የታጀቡ ጊዜያትን ማሳለፋቸውን ያወሳሉ፡፡ በኢሬቻ የመሰባሰቡን ጥቅም ሲያስረዱም፤ “ከተለያዩ አከባቢዎች የምንመጣ እንደመሆናችን በዓመት አንዴ ስንገኛን ይበልጥ እየተዋወቅን አንድነታችን እያጠናከርን እንሄዳለን፡፡ ኢሬቻ ከመሰረቱም ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የእርቅ፣ የሰላምና የምስጋና በዓል ነው፡፡ ከጠቀሜታ ውጪ ጉዳትም የለውም፡፡”

የኦሮሞ አባ ገዳዎች የሆረ አርሰዴ የኢሬቻ በዓልን ሲያስጀምሩ
ዛሬ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ እርጥብ ሳር ይዘው በየቡድን እየሆኑ በኢሬቻው ህብረዜማ ስርዓቱ ወደሚከወንበት ሆራ ሀርሰዲ ሲተሙ ነበር፡፡ ታዳሚያኑ “ሆ..ያ..ማሬዎ…” እያሉም ከፍ ባለ ዜማ አከባቢውን አድመቀውትም ውለዋል፡፡ምስል Seyoum Getu/DW

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኛው የአዲስ አበባ ነዋሪ አቶ ኤርሚያስ አበራ ቡልቻ ደግሞ የሰላምና የወንድማማችነት በዓል ነው ያሉት ኢሬቻ ላለፉት ዓመታት እያደገ በሁሉ ስርዓቱ እየዳበረ መምጣቱን ያስገነዝባሉ፡፡ “ላለፉት 19 ዓመታት ተሳትፌያለሁ፡፡ በዓሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል፡፡ በዓሉ እጅግ ባማረ ሁኔታ እየተከበረ የብሔር ብሔረሰቦች እንዲሁም የአፍሪካ ትኩረት ወደ መሳብ ደርሷል፡፡ ወደ ፊት ደግሞ ይበት የዓለም ህዝብ ትኩረትም እንደሚስብ አምናለሁ፡፡”የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ስለ ኢሬቻ በዓል ዝግጅት ምን ይላሉ?

ከባሌ ሮቤ በመምጣት በኢሬቻ ላይ የታደመችው ወጣት ሃያት አረባም እንደ በርካቶቹ ሁሉ በዘንድሮ ኢሬቻ የአከባበር ስርዓቱ ተደምማለች፡፡ “የዘንድሮ ኢሬቻ እጅግ በጣም ደስ ይላል፡፡ ወታቱ በባህል ልብስ አምሮበት በሰላማዊ ሁኔታ እያከበርን ነው ያለነው፡፡ ሰላምን በመስበክ ተምሳለት በሆነ መንገድ ነው ማክበር ያለብን በሚል ነው በወንድማማችነት ስሜት ያከበርነው፡፡ የተለያየ ብሔርም ተሳትፎውን ብያጠናክር እላለሁ፡፡”

የሆረ አርሰዴ ኢሬቻ በዓል ታዳሚያን በከፊል
ኢሬቻ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት ተቃውሞዎች የሚሰማበት መድረክ ሆኖ እንደቆየ ከዓመታት ታሪኩ ብታወስም በዚህ ኣመት የጎላ የተቃርኖ ደምጾች ሲሰማ አልተስተዋለም፡፡ምስል Seyoum Getu/DW

ኢሬቻ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት ተቃውሞዎች የሚሰማበት መድረክ ሆኖ እንደቆየ ከዓመታት ታሪኩ ብታወስም በዚህ ኣመት የጎላ የተቃርኖ ደምጾች ሲሰማ አልተስተዋለም፡፡

ስዩም ጌቱ

ታምራት ዲንሳ