1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም. የስፖርት ጥንቅር

ሰኞ፣ ግንቦት 26 2016

ሳምንታዊው የስፖርት ጥንቅር ኢትዮጵያውያን የተሳተፉባቸው የአትሌቲክስ ውድድሮችን፤ እንዲሁም የሻምፒዮንስ ሊግን አካቷል።

https://p.dw.com/p/4gbBV
ዶር ሙንድ
በሪያል ማድሪድ የተሸነፈው የቦሪሲያ ዶርትሙንድ ተጫዋች ምስል Hirnschal/osnapix/picture alliance

የግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ስፖርት

ትናንት በስቶኮልም ስዊዲን በተደረገ የዳይመንድ ሊግ የ3000 ሜትር የሩጫ ውድድር ለሜቻ ግርማ  8 ደቂቃ ከ01 ነጥብ ከ63 ሰከንድ በመግባት ቀዳሚ ሆነ። እሱን ተከትሎ  ሳሙኤል ፍሪው  8 ደቂቃ ከ05 ነጥብ ከ78 ሰከንድ በመግባት ሁለተኛ ሲሆን የቱኒዝያው አትሌት ሙሀመድ  አሚን  8 ደቂቃ ከ10 ነጥብ ከ41 ሰከንድ በመግባት ሦስተኛ ሆኖ ውድድሩን አጠናቅዋል። በተመሳሳይ ዓርብ ዕለት በኦስሎ ኖርዊይ በተካሄደው  ድይመንድ ሊግ  የሩጫ ውድድር የ 5000 ሜትር ርቀት ሀጎስ ገብረ ህይወት እና ዮሚፍ ቀጀልቻ  ጃኮብ ኪፕሎሞን አስከትለው አንደኛ እና ሁለተኛ ሆነው አሽንፈዋል። በዚህ ውድድር አትሌት ሀጎስ በ5ሺህ ሜትር ርቀት የኢትዮጵያ ከብረወሰን ከማሻሻሉም ባሻገር ሁለተኛውን የዓለም ፈጣን ሰአትን አስመዝግቧዋል።

የ30 ዓመቱ ኢትዮጵያውያዊአትሌት ሀጎስ ገብረ ሕይወት በኦስሎ የተደረገውን የዳይመንድ ሊግ 5000 ሜትር ውድድር  ፈጣን ሰአት ያስመዘገበው  12 ደቂቃ 36 ነጥብ ከ73 ሰከንድ በመግባት ዮሚፍ ቀጀልቻ ርቀት  12 ደቂቃ 38 ነጥብ ከ 95 ሰከንድ  በመግባት ሁለተኛ ሆንዋል። ዩጋንዳዊው አትሊት ጃኮፕ ኪፕሊሞ 12 ደቂቃ ከ40 ነጥብ ከ96 ሰከንድ በመግባት ሦስተኛ በመሆን አጠናቋል። በኢትዮጵያ የ5ሺህ ሜትር ርቀት ፈጣኑ ሰአት አትሌት ሀጎስ ገብረ ሕይወት እስካሻሻለበት እስካለፈው ሳምንት ድረስ በአትሌት ቀነኒሳ በቀለ ተይዞ የነበረ ሲሆን ሰአቱም 12 ደቂቃ 37 ነጥብ ከ 35 ሰከንድ ነበር። በሴቶች የ3000 ሜትር ርቀት ውድድር ሊክና አንባው ሁለተኛ ስትወጣ ወብርስት አስካለ 9ነኛ ሆና ውድድርዋን ጨርሳለች። 32 የተለያዩ ውድድሮች የሚካሄዱበት የዳይመንድ ሊግ ውድድር 14 በከተሞች የሚካሄድ ሲሆን በያዝነው ሳምንት መጫረሻ እሑድ በፓሪስ በቀጣይ ዓርብ በሞናኮ ከዛም በሎንዶን የሚካሄድ ይሆናል።

አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ
አትሌት ጥሩነሽ ዲባባምስል DW/Y. Gebreegziabher

በሌላ የአትሌቲክስ ዜና በማድሪድ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር ጥሩነሽ ዲባባ 3ኛ ስትወጣ ዳዊት ወልዴ በቀዳሚነት አጠናቀቀ። እሔድ ግንቦት 25  በስፔን ማድሪድ በተካሄደው የሴቶች  የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ 3ኛ በመሆን አጠናቃለች። የሶስት ጊዜ የኦሎምፒክ እና የአምስት ጊዜ የዓለም ሻምፒዮና  የሆነችው የርቀቱ ንግሥት  አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ 39ኛ ዓመት ልደቷን ባከበረች ማግስት ባደረገቸው በዚህ ውድድር ከዓመት የውድድር ዕረፍት በኋላ ያሳየችው  የውድድር ብቃት አድናቆትን አስችሮዋታል። አውስትራላዊቷ አትሌት አዚ ቤት ዶየል  31 ደቂቃ ከ 23 ስትገባ ዩጋንዳዊቷ  አትሌት  አኔት  30 ደቂቃ ከ38 ሰከንድ በመግባት ሁለተኛ ስትሆን አትሌት ጥሩነሽ 31 ከ04 በሆነ ግዜ ጨርሳለች። በወንዶች የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር ደግሞ ዳዊት ወልዴ 26 ደቂቃ ከ55 ሴኮንድ በመግባት ሲያሸንፍ ኬንያዊው አትሌት ቪንሴንት ኪማዮ 2ኛ ዩጋንዳዊው ማርቲን ኪፕሮቲች ደግሞ 3ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።

እግርኳስ

2026 ለሚደረገው የዓለም ዋንጫ ለማለፊያ የማጣሪያ ጨዋታዎች በተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት ከተሞች በመከናወን ላይ ይገኛሉ። የምድብ ሦስተኛ እና አራተኛ ጨዋታዎችም በዚህ ሳምንት በተለያዩ ሃገራት ይደረጋሉ። በምድብ አንድ የምትገኛው ኢትዮጵያ  ከጊኒ ቢሳዋ ጋር ላለባት የማጣሪያ ጨዋታ ወደ ስፍራው አቅንታለች። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከጊኒ ቢሳው ጋር ለሚያደርገው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ወደ መዲናዋ  ቢሳው  ባለፈው ሳምንት መጭረሻ ነው የተጓዘው። ብሔራዊ ቡድኑ ለዓለም ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታ ወደ ጊኒ ቢሳው ከማምራቱ አስቀድሞ የሀገር ቤት ልምምዱን በአዲስ አበባ ስታዲየም ሲያደርግ ቆይቷል።

ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የትግራይ ክልል ክለቦች ለመጭው ዓመት ውድድር ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበሩበት ሊግ እንዲመለሱ መወሰኑ ይታወቃል። በሰሜን ኢትዮጵያ መንግሥት እና ትግራይ ሀይሎች መካከል ለሁለት ዓመታት የዘለቀው ጦርነት በክልሉ የነበረው የሊግ ውድድር አስቀርቷል። በሁለቱ ተፋላሚ ሀይሎች መካከል የነበረው ልዩነት በሰላም ስምምነት ከረገበ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የገቡት ከሽሬ እንዳሥላሴ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ሲሆኑ የተቀሩት ቡድኖች ተጫዋቾችቸውን  ወደ ልምምድ መመለስ የሁሉም ድርሽ  ነው ተብሏል። የክልሉ ሊጎች በመጫው ዓመት ጀምሮ የሀገሪቱን የሊግ ውድድር ይቀልቀላሉ ተብሎ ይጣበቃል።

የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ያነሳው ሪያል ማድሪድ
የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ያነሳው ሪያል ማድሪድ ተጫዋቾች ፈንጠዝያምስል Carl Recine/REUTERS

ሻንፒዮንስ ሊግ

በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የአውሮፓ እግር ኳስ ክለቦች ድግስ ቻምፒየንስ ሊግ በሪያል ማድሪድ አሸናፊነት ተጠናቋል። ክውድድሩ አስቀድሞ በብዙ ገማቾች ሪያል ማድሪድ በቀላሉ እንደሚያሽነፍ የተጠበቀ ቢሆንም የመጀመርያ አጋማሽ ሙሉ በሙሉ የጨዋታ የበላይነቱ የቦርሲያ ዶርትሙንድ ነበር።

ከጉዳት ተመልሶ የመጀመርያ የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታዉን ያደረገዉ ቤልጅየማዊ የግብ ጠባቂ ባሳየዉ ድንቅ ብቃት የቡድኑ መረብ ሳይደፈር ወደ ሁለተኛዉ አጋማሽ እንዲገቡ ትልቁን አስተዋጾ አድርጓል። ከእረፍት መልስ ቀስ በቀስ ኳሷን በመቆጣጠር ጨዋታዉ ላይ ተጽዕኖአቸዉን ማሳረፍ የቻሉት ማድሪዶች በቻምፒየንስ ሊግ ፍጻሜ ታሪክ የመጀመርያ ጎል ያስገባ ተከላካይ የሆነባትን ግብ በ74ኛዉ ደቂቃ ዳኒ ካርቫሃል አስቆጥሮ ጨዋታዉን መምራት ጀመረ። 

ጎሉ ከተቆጠረ በኋላ የጨዋታው መልክ ተቀየረ። ከቦሩሲያ ዶርቱመድ የበላይነቱ ውደ ሪያል አዘነበለ። በጨዋታው ሙሉ በሙሉ የበላይነት የወሰዱት ማድሪዶች ዓመቱን ሙሉ የአዉሮፓ እና የክለቡ ኮከብ የነበሩት ቪኒሽየስ ጁኒየር እና ጁድ ቤሊንግሃም የበለጠ ተጣምረዉ ታዩበት። በ83ኛ ደቂቃ ቪኒሽየስ ጁኒየር ባስቆጠራት ግብ ሁለት ለባዶ መርተዉ ለክለባቸዉ 15ኛ የሆነዉን የቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫ አንስተዋል። ሪያል ማድሪድ ወጣት ኮከቦችን አሰባስቦ ወደ አዲስ ምዕራፍ እየገባ ያለዉ ይህ ታሪካዊዉ ክለብ በዕድሜ የገፉትን እነ ቶኒ ክሮስ እና ሉካ ሞድሪችን በክለብ ወድድር ከፍተኛ ክብር የሆነዉን ዋንጫ አንስቶ የሚሰናበት ይሆናል። ይህ ድል ለክለብ አሰልጣኙ 7ኛ እና ሪከርድ ሲሆን ቶኒ ክሩስ ፣ ሉካ ሞድሪች ፣ ናቾ ፣ እና ግብ አስቆጣሪው ዳኒ ካርቫሃል ለተጫዋቾች ሪከርድ የሆነዉን ስድስተኛ ዋንጫቸዉን አሸነፈዋል። በቀጣይ ሳምንታት የኪሊያን ኢምባፔን መምጣት የሚጠባበቀው ሪያል ማድሪድ ከታሪክ ላይ ታሪክ እየጨመረ መጪዉን ግዜም እንደሚቆጣጠር ለተፎካካሪዎቸ አስታዉቆ ምሽቱን በድል አሳልፏል።

በተያያዘ ዜና በሪያል ማድሪድ አሸናፊነት የተጠናቀቀው የ2023/24 የውድድር ዓመት የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የዓመቱ ምርጥ ተጨዋች ዝርዝር ይፋ ተደርጓል። በዚህም መሰረት ብራዚላዊው የሪያል ማድሪድ የፊት መስመር ተጨዋች ቪንሰስ ጁኒየር የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የዓመቱ ምርጥ ተጨዋች ተብሎ ተመርጧል። ቪንሰስ ጁኒየር በውድድር ዓመቱ ስድስት የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ግብ ማስቆጠር ችሏል።  የ2023/24 የውድድር ዓመት የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የዓመቱ ምርጥ ወጣት ተጨዋች ይፋ ሆኗል። በዚህም መሰረት በእንግሊዛዊው የሪያል ማድሪድ የመሐል ሜዳ ተጨዋች ጁድ ቤሊንግሀም የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የዓመቱ ምርጥ ወጣት ተጨዋች ተብሎ መመረጥ ችሏል። ጁድ ቤሊንግሀም በውድድር ዓመቱ ለሪያል ማድሪድ አራት የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ግብ አስቆጥሮ አምስት ለግብ የሆኑ ኳሶች አመቻች ማቀበል ችሏል።

አሰልጣኝ ጆዜ ሞሪኖ
አሰልጣኝ ጆዜ ሞሪኖ ምስል picture-alliance/dpa/M. Rickett

የዝውውር መረጃ

በውድድር ዓመቱ መጨረሻ ከአስራ ሁለት ዓመታት ቆይታ በኋላ ቦርስያ ዶርትሙንድ ጋር የተለያየው ማርኮ ሪዮስ በቀጣይ ወደ አሜሪካ ሜጀር ሊግ ለማምራት ንግግር ላይ መሆኑ ተሰምቷል። የመሐል ሜዳ ተጨዋቹን ማርኮ ሪዮስን ለማስፈረም የአሜሪካው ሎስአንጀለስ ጋላክሲ ክለብ ንግግር መጀመር ብቻ ሳይሆን  ለስምምነት ተቃርቧል ነው የተባለው።

የምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ ጣልያናዊውን የሌስተር ሲቲ አሰልጣኝ ኢንዞ ማሬስካን በሀላፊነት መሾሙን ያሳውቃሉ ተብሎ ይጠበቃል። አሰልጣኝ ኢንዞ ማሬስካ በሰማንያዎቹ ቤት ለአንድ ተጨማሪ ዓመት የማራዘም አማራጭ ያካተተ የአምስት አመት ኮንትራት መፈረማቸው ተገልጿል።

ሪያል ማድሪድ ፈረንሳዊውን የፊት መስመር ተጨዋች ኪሊያን ምባፔን ከፒኤስጂ በነፃ ዝውውር ማስፈረማቸውን በሚቀጥሉት ቀናት በይፋ እንደሚያሳውቁ ተሰምቷል።

ታዋቂዉ አሰልጣኝ ጆዜ ሞውሪኖ የቱርኩ የፊነርባቼ አዲሱ አሰልጣኝ ሆነው ተሹመዋል። መከላከል በሚባዛበት አጨዋወታቸው እና አወዛጋቢ ንግግሮቻቸው ብዙ አድናቂወች እና ጠላቶች ያፈሩት ጆዜ ከማንችስተር ዩናይትድ ከተሰናበቱ በኋላ አይቀሬ የሚመስለዉን የወደታች ጎዞ ቀጥለዋል። ከ2000 ዓ/ም አጋማሽ ጀመሮ በአዉሮፓ ዉስጥ እጅግ  ተፈላጊ ከሚባሉት ጥቂት አሰልጣኞች መሃከል አንዱ የነበሩት ጆዜ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ከነዚያ ጊዜወች ጋር ሲነጻጸሩ መካከለኛ እና ታናሽ ሊባሉ የሚችሉ ክለቦችን እያሰለጥኑ ይገኛሉ።

ለሁለተኛ ጊዜ እንግሊዝ ተመልሰው በቸልሲ እና ከዛም በማችስተር ድል እና ውድቀት የተቀላቀለባቸዉ ጊዜዎችን ያሳለፉት ጆዜ ቶተንሃምንም ይዘው ያልተሳካ ቆይታ አድርገው ነበር። ወደ ጣሊያን ክለብ ሮማ ሄዶ ላለፉት ሦስት ዓመታት የሊግ ዉድድር ላይ በጣም ደካማ የሚባል ዉጤት  አስመዝግበዋል።

በየሄዱበት ሁሉ አሸናፊነትን እና ዉዝግብን ይዘው የሚንቀሳቀሱት ጆዜ ቀጣይ ማረፊያቸዉን ወደ ቱርኩ ክለብ ፊነርባቼ አድርገዋል። «በተለምዶ አሰልጣኝ የሚወደደዉ ካሸነፈ በኋላ ነዉ እኔ ግን እዚህ ከመጀመርያዉ እንደተወደድኩ ይሰማኛል» ያሉት የ61 ዓመቱ አሰልጣኝ እንደልማዳቸዉ ትንሽ ማጥቃት ያለበት ጨዋታ ፣ ትንሽ ድል እና ብዙ ድራማዎች በጉጉት ለሚጠብቋቸዉ የፊነርባቼ ክለብ ደጋፊዎች ለማቅርብ ኢስታንቡል በሚገኘው ኡልክር ስታዲየም ትውውቃቸውን አድርገዋል።

ሃና ደምሴ

ሸዋዬ ለገሠ