1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ፍጥጫ፦ ሪያል ማድሪድ ከቦሩሲያ ዶርትሙንድ

ቅዳሜ፣ ግንቦት 24 2016

ዛሬ ማታ በለንደን ዌምብሌይ ስታዲየም ሪያል ማድሪድ እና ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ለአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ የፍጻሜውን ግብግብ ያደርጋሉ። ሁለቱ ቡድኖች በውድድሩ ያላቸው ታሪክ የተራራቀ ነው። የአሰልጣኞቻቸውም ስኬት ከፍተኛ ልዩነት ይታይበታል። ሁለቱም ከፍጻሜው በኋላ ጀርመናውያን ተጫዋቾች መሰናበታቸው ግን ያመሳስላቸዋል።

https://p.dw.com/p/4gWkn
የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ
ሪያል ማድሪድ 14 ጊዜ ቦሩሲያ ዶርትሙንድ አንድ ጊዜ የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ አሸንፈዋል። ምስል Matthias Schrader/AP/picture alliance

የቻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ፍጥጫ፦ ሪያል ማድሪድ ከቦሩሲያ ዶርትሙንድ

የአውሮፓ የቻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ በመላው ዓለም እጅግ ከፍተኛ ተመልካቾች የሚያገኝ ስፖርታዊ ውድድር ነው። ዛሬ ምሽት ሪያል ማድሪድ እና ቦሩስያ ዶርትሙንድ የሚያደርጉት የፍጻሜ ጨዋታ በዓለም ዙሪያ 450 ሚሊዮን የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ይመለከቱታል ተብሎ ይጠበቃል። 

የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ለ14 ጊዜ ያሸነፈው ሪያል ማድሪድ እና ድሉን ከ27 ዓመታት ገደማ በፊት አንድ ጊዜ ያጣጣመው ቦሩሲያ ዶርትሙንድ የተራራቀ ልምድ ባላቸው አሰልጣኞች የሚመሩ ናቸው። 

ማድሪድን የሚመሩት የ64 ዓመቱ ካርሎ አንቺሎቲ ሁለት ጊዜ በተጫዋችነት አራት ጊዜ በአሰልጣኝነት ዋንጫውን ማንሳት ችለዋል። ባየር ሙንሽን፣ ኤሲ ሚላን፣ ቼልሲ፣ ጁቬንቱስ እና ፓሪ ሴንት ዠርሜን የመሳሰሉ ታላላቅ የእግር ኳስ ቡድኖችን ጭምር ያሰለጠኑ ናቸው። 

የቦሩሲያ ዶርትሙንድ አሰልጣኝ ኤዲን ቴርዚክ ትልቁ ውጤት ከሦስት ዓመታት ገደማ በፊት ያሸነፉት የጀርመን ዋንጫ ነው። የ41 ዓመቱ አሰልጣኝ በጀርመን የታችኛው ሊጎች ተጫውተዋል። 

በልምድ ረገድ አንቺሎቲ ቴርዚክን ይበልጧቸዋል። እንዲያም ቢሆን ሐሳብ ይገባቸዋል።

የግንቦት 19 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

“ቀዝቃዛው ላብ እና ፍርሀት ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ይፈጠራል። ይኸ የተለመደ ነው። በእንዲህ አይነት ጨዋታዎች ሁልጊዜም እንደዚያ ነው” ሲሉ አንቺሎቲ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

አንኖኒዮ ሩዲገር፣ ካርሎ አንቺሎቲ እና ቪኒሺየስ ጁኒየር
የሪያል ማድሪድ አሰልጣኝ ካርሎ አንቺሎቲ ዛሬ ምሽት የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ካሸነፉ አምስተኛቸው ይሆናል። ምስል Susana Vera/REUTERS

“ነገር ግን እኔ ብዙ ልምድ አለኝ። ቡድኔ ከፍ ያለ በራስ መተማመን ይሰጠኛል። ምክንያቱም ለጨዋታው ትኩረት ሰጥተው ተመልክቺያቸዋለሁ። በቻምፒዮንስ ሊግ ስሜት ውስጥ ይገኛሉ” ብለዋል። 

ማድሪድ ለመጨረሻ ጊዜ የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ባለቤት የሆነው ቪኒሺየስ ጁኒየር ባስቆጠራት ግብ ከሁለት ዓመታት በፊት ሊቨርፑልን 1-0 አሸንፎ ነበር። ብራዚላዊው አጥቂ በዛሬው ምሽት ጨዋታ የስፔን ሻምፒዮን ለሆነው ሪያል ማድሪድ ቁልፍ ተጫዋች ይሆናል። 

ካሪም ቤንዜማ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ከተዘዋወረ በኋላ ማድሪድ በዚህ ዓመት የክንፍ ተጫዋቾች የሆኑት ቪኒሺየስ ጁኒየር እና ሮድሪጎን እንደ ዋንኛ አጥቂ ተጠቅሟል። በውሰት ለማድሪድ የሚጫወተው ጆሴሉ ለአጥቂው ክፍል ቁመት እና ጡንቻ ጨምሯል። 

ስፔናዊው ጆሴሉ ማድሪድ የጀርመኑ ባየር ሙንሽንን ሲያሸንፍ ሁለት ግቦች አስቆጥሯል። በዛሬው የፍጻሜ ጨዋታ ይጀምር እንደሆነ የሚታይ ነው። 

ዶርትሙንድ በአንጻሩ በዘጠኝ ቁጥር አጥቂ የሚጫወት ነው። የጀርመኑ ኒክላስ ፉልክሩግ በቡንደስ ሊጋው አምስተኛ ደረጃ ይዞ ላጠናቀቀው ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ሲጫወት የመጀመሪያው ዓመት ሲሆን ያን ያህል ስኬታማ አልሆነም። ይሁንና በግማሽ ፍጻሜው ከፒኤስጂ በተደረገው ጨዋታ ጨምሮ በአውሮፓ ቁልፍ ግቦች ከመረብ አሳርፏል። 

የቦሩሲያ ዶርትሙንድ አሰልጣኝ ኤዲን ቴርዚክ “በአንድ ግጥሚያ ማናቸውም ነገር ይቻላል የሚል ጽኑ ዕምነት አለኝ። ማንም ቢሆን በአንድ ጨዋታ ብዙ ነገር ማሳካት እንደሚችል በተለይ በዚህ ዓመት፣ በተለይ በዚህ ውድድር ያሳየ ቢኖር እኛ ነን” ሲሉ ተናግረዋል።

የቦሩሲያ ዶርትሙንድ አሰልጣኝ ኤዲን ቴርዚክ
የቦሩሲያ ዶርትሙንድ አሰልጣኝ ኤዲን ቴርዚክ ባለፈው ዓመት የጀርመን ቡንደስ ሊጋ ዋንጫን በመጨረሻው ጨዋታ ቢያጡም በተያዘው ዓመት በቻምፒዮንስ ሊግ ለፍጻሜ ለመድረስ በቅተዋል። ምስል Alex Grimm/Getty Images

“ማድሪድ ስምንት ጊዜ ከቻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ የደረሰ ይመስለኛል። አንድ ጊዜም አልተሸነፉም። ዋናው ነገር ባለፉት ስምንት የፍጻሜ ጨዋታዎች የተፈጠረው አይደለም። በሚቀጥለው የሚፈጠረው ነው” ያሉት አሰልጣኝ ኤዲን ቴርዚክ “ለዚያ ደግሞ ኃላፊነቱ የእኛ ነው” የሚል ዕምነት አላቸው።

 የግንቦት 5 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሁለቱም ቡድኖች ከዛሬው የፍጻሜ ጨዋታ በኋላ የሚያመሳስላቸው አንድ ነገር አለ። ሁለቱም በቡድኖቻቸው ቁልፍ ሚና የነበራቸው ጀርመናውያን ተጨዋቾችን ከፍጻሜው በኋላ ይሰናበታሉ። 

የሪያል ማድሪድ አማካይ ተጨዋች የሆነው ቶኒ ክሮስ ከአውሮፓ ዋንጫ በኋላ ከፕሮፌሽናል እግር ኳስ ጡረታ ይወጣል። የዛሬው የፍጻሜ ጨዋታ ቶኒ ክሮስ ለማድሪድ የሚሰለፍበት የመጨረሻ ነው።  ክሮስ ከዚህ ቀደም አምስት ጊዜ የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን አሸንፏል።

የዶርትሙንድ የአጥቂ አማካይ ተጫዋች የሆነው ማርኮ ሬውስ ለትውልድ ከተማው ቡድን ለአስራ ሁለት ዓመታት ተጫውቶ ከዛሬው ፍጻሜ በኋላ ይሰናበታል። ጨዋታውን ከሚጀምሩ አስራ አንድ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ለመሆኑ ማረጋገጫ የለውም። ነገር ግን ሁለተኛውን የቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ቢያሸንፍ ታላቅ የመሰናበቻ ስጦታ ይሆንለታል። 

ሬውስ በግሪጎሪያኑ 2013 የዛሬው ፍጻሜ በሚደረግበት የለንደኑ ዌምብሌይ ስታዲየም ዶርትሙንድ በባየር ሙንሽን በተሸነፈበት የቻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ተጫውቷል። 

ማርክ ሜዶውስ/ይልማ ኃይለሚካኤል

እሸቴ በቀለ