1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስጋትና ተስፋ ያንዣበበት የጀርመን ምርጫ

ማክሰኞ፣ የካቲት 11 2017

«ሐገሮች የውስጥ ጉዳያቸው በተገቢው መንገድ ካልሄደ የስደተኞችን ጉዳይ ዋና ርዕስ ያደርጉታል። ለችግሩ ሐላፊነት የሚወስድ ሌላ ሦስተኛ ወገን ነው የሚፈልጉት። በሁሉም ሃገሮች በኔ ሐገር በአይቮሪኮስት ጭምር አንድ ችግር ሲፈጠር፤ የሥራ እጥነት ሲያጋጥም፤ ሰዎች ድሃ ሲሆኑ ለዚህ የመጀመሪያ ተጠያቂው ስደተኞች እንደሆኑ አድርገው ያስባሉ።»

https://p.dw.com/p/4qcTT
 የSPD እጩ ተወዳዳሪ የሆኑት ካሜሩናዊ  ጀርመናዊ አርማንድ ዞርን
የSPD እጩ ተወዳዳሪ የሆኑት ካሜሩናዊ ጀርመናዊ አርማንድ ዞርንምስል Christian Murk/DW

ስጋትና ተስፋ ያንዣበበት የጀርመን ምርጫ


የቀኝ ጽንፈኞች ድጋፍ መጨመር
በአደጉ አገሮች ከምርጫ በፊት የቅድመ ምርጫ ትንበያ ለማካሄድ የሚያስችሉ የመራጭ ሕዝብ አስተያየት መመዘኛ ጥናቶች ይካሄዳሉ። በጀርመን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር የፊታችን የካቲት 23 ቀን 2025 ምርጫ ከመካሄዱ በፊት በተሰበሰቡ የመራጭ ሕዝብ አስተያየት መመዘኛዎች አማራጭ ለጀርመን ወይም «AFD» እየተባለ የሚጠራው «መጤ ጠል» እየተባለ የሚወቀሰውቀኝ ፅንፈኛ ፓርቲ ከ1,297 መራጮች 21 በመቶ ድጋፍ በማግኘት ቀዳሚነቱን ይዟል። የመራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልስ ፓርቲ የሆነው SPD 17 በመቶ፤ ይህም በአለፈው የምርጫ ወቅት በተካሄደው የሕዝብ መመዘኛ አስተያየት ከነበረው 25 ነጥብ 7  በመቶ የቀነሰ መሆኑን ያሳያል። FDP እየተባለ የሚጠራው የነጻ ዴሞክራቶች ፓርቲ በአለፈው ምርጫ ካገኘው 11 ነጥብ 5 በመቶ ተንሸራቶ 7 በመቶ ማግኘቱን ታውቋል።
በአለፈው የጎርጎሮሳውያኑ 2024 በጀርመን በተካሄደ አካባቢያዊ ምርጫ በምስራቅ ጀርመን ግዛት በዛክሰን፣አንሃልተንና ቱሪንገን ፌደራላዊ ግዛቶች ቀኝ ጽንፈኛው አማራጭ ለጀርመን ፓርቲ የጀርመን ጥምር መንግስት የመሰረቱትን 3 አጣማሪ ፓርቲዎችን በሦስት ዕጥፍ በመብለጥ አሸንፏል። 
በማግድቡርግ ከተማ አንድ ሳውዲ አረቢያዊ የአዕምሮ ሐኪም በከተማዋ የገና ገበያ ውስጥ በነበሩ ሰዎች ላይ በፈጸመው የመኪና አደጋ 6 ሰዎች ሲሞቱ ከ200 በላይ መቁሰላቸውን ይታወሳል። ሰሞኑን ደግሞ በሙዩኒክ ከተማ አንድ አፍጋኒስታናዊ በፈጸመው ተመሳሳይ ጥቃት በ28 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት አድርሷል። እንደዚህ ዓይነት ጥቃቶች በነዋሪዎች ላይ የደህንነት ስጋት በመደቀናቸው በተለይ ወጣት የጀርመን መራጮች ፅንፈኛ ፓርቲዎችን እንዲመርጡ ምክንያት እንደሆነ ጥናቶች ያመላክታሉ።
የተጣማሪው መንግስት መፍረስ
የጀርመን መንግስትን ከመሰረቱት 3 ፓርቲዎች አንዱ የሆነውን FDP እየተባለ የሚጠራው የነጻ ዴሞክራቶች ፓርቲ መሪ የሆኑት የገንዘብ ሚኒስትር የነበሩት ክርስትያን ሊንድነር በመራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልስ ከስልጣን መባረራቸውን ተከትሎ ፓርቲው ከጥምር መንግስቱ እራሱን አግልሏል። በመሆኑም ጥምር መንግስቱ እንዲፈርስ ተገዷል። 
ይህን ተከትሎ ኦላፍ ሾልስ ለሃገሪቱ ምክርቤት ቡንደስታግ የመተማመኛ ድምጽ ለማግኘት የጠየቁ ሲሆን ምክርቤቱ በአብላጫ ድምጽ የመተማመኛ ድምጽ ነፍጎአቸዋል። በመሆኑም የሐገሪቱ ፕረዚደንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር በሐገሪቱ ሕገመንግስት መሰረት ምክርቤቱን እንዲበተን አድርገዋል። ይህን ተከትሎም እንደጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር የፊታችን የካቲት 23 ቀን 2025 ወቅቱን ያልጠበቀ ምርጫ እንዲካሄድ ተወስኖየምረጡኝ ዘመቻው ተጧጡፏል።
የአፍሪካውያን ስደተኞች ተስፋና ስጋት
የቅድመ ምርጫውን ሂደት ለመከታተል የአማርኛውን ጨምሮ ከተለያዩ የአፍሪቃ ቋንቋዎች ክፍል የተውጣጣው የዶቼቬለ የጋዜጠኞች ቡድን ወደ ማግድቡርግ፣ በርሊንና ፍራንክፈርት ተንቀሳቅሶ የአፍሪቃዎያን መራጮች አስተያየትን አሰባስቧል። የኤኮኖሚ ባለሞያው ዶክተር ፈቃዱ በቀለ ትውልደ ኢትዮጵያ ጀርመናዊ ሲሆኑ የተለያዩ ምርምሮችን በማካሄድ፤ በዩኒቨርስቲዎች በማስተማርና በራሳቸው ድረ-ገጽ በአፍሪቃና ኢትዮጵያ ጉዳዮች በመጻፍ ይታወቃሉ። የበርሊን ከተማ ነዋሪው ዶክተር ፍቃደ «መጤ ጠል» እየተባለ የሚወቀሰው አማራጭ ለጀርመን  ፓርቲ ከከዚህ ቀደሞቹ ምርጫዎች የተሻለ ድምጽ ያገኛል ተብሎ ቢጠበቅም መንግስት የመመስረት ዕድል ስለሌለው ግን ለአፍሪካውያን ስደተኞች ብዙም አያሰጋም ይላሉ።

«ይሄ ፓርቲ ብዙ ድምጽ ያገኛል ወደ 20፤21 በመቶ፤ ይሁንና ግን መንግስት የመመስረት ሃላፊነት ሳይሆን ሌሎች ዴሞክራቲክ ፓርቲዎች እንደ ክርስትያን ዴሞክራቲክ ፓርቲ፣ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲና ሌሎችም ከዚህ የቀኝ ፓርቲ ጋራ አንድ ላይ ተጣምረው መንግስት ለመመስረት አይፈልጉም። በተለይም ከእንደዚህ ዓይነት ፓርቲ ጋር መስራት ማለት ፖለቲካሊ ኢኮኖሚካሊ አደጋ ሊያስከትል ይችላል የሚል ግምት አላቸውና በዚህ ምክንያት የተነሳ የውጭ አገር ሰዎች ኢትዮጵያውያንም ጨምሮ በዚች ሐገር ጥገኝነት ጠይቀው የሚኖሩ ይህንን የሚያህል ስጋት እንዲያድርባቸው የሚያስፈልግ አይመስለኝም።»
ከ30 ዓመታት በላይ በጀርመን ኖረዋል። በበርሊን የተመሰረተው «የአፍሪካ ምክርቤት» የተባለ ተቋምን በበላይነት ይመራሉ። ትውልደ ናይጀሪያ የሆኑት አክዬ ኦላፓንሰን። እሳቸው እያደገ የመጣው የቀኝ አክራሪዎች ድጋፍለአፍሪቃውያን ዳያስፖራትልቅ ስጋት መደቀኑን ይናገራሉ። ይህንና መሰል ችግሮችን ለማስወገድ ከጀርመን መንግስትና የተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር እየሰሩ እንደሆነ ነግረውናል። አፍሪቃውያን ከጀርመን የሕዝብ ቁጥር አንጻር አናሳ ቁጥር ያላቸው በመሆኑ ተደራጅተው ዴሞክራቶችን እንዲመርጡ ጥረት እያደረጉ ነውም ብለውናል። በዚህ ጥረትም ድምጽ የመስጠቱን ጥቅም ተረድተዋል ይላሉ። 

« አነስተኛ ቁጥር ያለን እንደመሆኑ ሰዎች ድምጻቸው ትርጉም ያለው መሆኑን አይገነዘቡም፤ በመሆኑም ምርጫን እንደወሳኝ አድርገው በመውሰድ ሐላፊነታቸውን አይወጡም። በአለፉት 10 ዓመታት ባካሄድነው የማንቃት ሥራ ሰዎች የሚመሩአቸውን በመምረጥ በኩል በንቃት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ። አሁን ግን መብታቸው ለሚያስከብር ፖለቲካዊ ፓርቲ ድምጽ የመስጠት ትርጉም ገብቶአቸዋል።»
በኢትዮጵያውያን ዘንድም የጀርመን ዜግነት መውሰድ እየቻሉ ባለመውሰዳቸው ምክንያት በምርጫ የማይሳተፉ እንዳሉ ያጫወቱን ደግሞ በፍራንክፈርት ከተማ ነዋሪ የሆኑት የሕግ ባለሙያው ዶክተር ታምሩ መለሰ ናቸው። ላለፉት 37 ዓመታት በጀርመን የኖሩት ዶክተር ታምሩ የዘንድሮው ምርጫ ተስፋና ስጋት የተደቀነበት እንደሆነ አጫውተውናል።

የፖለቲካ ተንታኝ አሚዱ ትራዎሬ
የፖለቲካ ተንታኝ አሚዱ ትራዎሬምስል Silja Fröhlich/DW


 « የዘንድሮውን ምርጫ በከፍተኛ ደረጃ ከሚጠበቁት አንዱ ነው። ተስፋው ቀኝ አክራሪ ፓርቲዎች ስልጣን እንዳይዙ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚታገሉ ፓርቲዎች የሚያደርጉት ጥረት ተስፋ ሰጪ ነው። ሕብረተሰቡ ደግሞ እነዚህ አክራሪ ፓርቲዎች ወደ ስልጣን እንዳይመጡ በሰላማዊ ሰልፍ እየገለጸ ነው። ስጋቱ እነሱ ባያሸንፉም ከፍተኛ ድምጽ በማግኘት ፓርላማ ውስጥ ችግር ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ነው። በአሁኑ ጊዜ አንደኛ ወጥተው ፓርላማ ውስጥ ስልጣን ይይዛሉ የሚል ግምት የለኝም።»
ስደተኞችን የፖለቲካ መጠቀሚያ የማድረግ አባዜ
ትውልደ አይቮሪኮስታዊ ጀርመናዊው አሚዱ ትራዎሬ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለምአቀፍ ግኑኝነት ሙሁር ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት በተለያዩ ዓለማት የሚገኙ ፖለቲከኞች ለተለያዩ ችግሮች ስደተኞችን ተጠያቂ የማድረግ አባዜ ፣ተገቢ እንዳልሆነ በአጽንኦት ተናግሯል። «እኔ በተወለድኩባት አይቮሪኮስትም ሆነ በአሜሪካና አውሮፓ ስራ እጥነት ሲፈጠር፤ የድህነት ችግር ሲያጋጥም ችግሩን በተገቢው መርምሮ ተገቢውን መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ በስደተኞች ላይ ማላከክ ተገቢ አይደለም» ይላሉ አሚዱ ትራዎሬ 

«ሐገሮች የውስጥ ጉዳያቸው በተገቢው መንገድ ካልሄደ የስደተኞችን ጉዳይ ዋና ርዕስ ያደርጉታል። ለችግሩ ሐላፊነት የሚወስድ ሌላ ሦስተኛ ወገን ነው የሚፈልጉት። በሁሉም ሃገሮች በኔ ሐገር በአይቮሪኮስት ጭምር አንድ ችግር ሲፈጠር፤ የሥራ እጥነት ሲያጋጥም፤ ሰዎች ድሃ ሲሆኑ ለዚህ የመጀመሪያ ተጠያቂው ስደተኞች እንደሆኑ አድርገው ያስባሉ። 
በአንድ ሐገር ምርጫ ኖሮ የመምረጥ መብት ከሌለህ ነገሮችን ለመቀየር አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። ስለዚህ በጀርመን የሚኖሩ ዳያስፖራዎችን የምለምናቸው ነገር ቢኖር ከሕዝቡ ጋር ተዋህደው የጀርመን ዜግነት እንዲወስዱ ነው። በመሆኑም የመምረጥ መብት ይኖራቸዋል። ድምጽ መስጠት ከቻሉ ደግሞ በዚህ አገር የተለያዩ ነገሮችን ለመለወጥ ያስችላል።»

መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልስ
መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልስምስል Michael Kappeler/dpa/picture alliance

ድምጻችን ለዴሞክራቶች
የፖለቲካ ተንታኙ አሚዱ ትራዎሬ አፍሪካውያን መራጮች የጀርመን ዜግነት ወስደው የጀርመን የዴሞክራሲ ሂደትን በማጠናከርር በኩል ሚናቸውን እንዲጫወቱ አሳስበዋል። እሳቸውም ድምጻቸውን ለቀኝ አክራሪዎች ሳይሆን ለዴሞክራቶች እንደሚሰጡ በማከል።

« ድምጼን ለማን መስጠት እንደሌለብኝ አውቃለሁ። ለAFD ድምጼን አልሰጥም፤ ድምጼን ለቀኝ ርዕዮተ ዓለም አራማጆች አልሰጥም፤ ድምጼን ማኅበረሰቡን የሚከፋፍል አጀንዳ ለሚያራምዱት አልሰጥም፤ እኔ የምመርጠው የማሕበረሰቡን አንድነትን የሚያጠናክር ፓርቲን ነው። ለአፍሪካውያን ዳያስፖራ እውቅና የሚሰጥ ፓርቲን እመርጣለሁ። በዓለም ላይ ሰብአዊነትን የሚያበረታታን ፖሊሲን ለሚያራምድድምጼን እሰጣለሁ።»
ትውልደ ኢትዮጵያዊው ጀርመናዊ ዶክተር ፈቃደም መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልስ በምርጫ ቅስቀሳቸው ቅር ቢያሰኙአቸውም የሳቸውን ፓርቲ እንደሚመርጡ ግን አልሸሸጉም።

«እኔ እንግዲህ በመሰረቱ በአሁኑ ጊዜ የምመርጠው ባለቤቴም የምትመርጠው SPDን ነው። ግን ትላንትና ቡንደስ ካንስለር ሾልስ በ9 ዓመቱ ከአፍሪካ መጥቶ እዚህ ያደገ የባህል ሚኒስትር አለ በሱ ላይ የማይሆን ነገር ተናግረዋል። እና ይህ ትንሽ አስከፍቶኛል፤ ሌሎችንም አስከፍቷል። ግን በአጠቃላይ SPD  ወይም ግራ ለሆነው ነው የምንመርጠው፤ እንደየሁኔታው ነው።»

ዶክተር ፍቃደ በቀለ የምጣኔ ሐብት ሙሑርና የምርጫ ተሳታፊ
ዶክተር ፍቃደ በቀለ የምጣኔ ሐብት ሙሑርና የምርጫ ተሳታፊምስል Yohannes G Egziabher/DW


ዶክተር ፈቃደ አስከፋኝ ያሉት በዚህ ሳምንት እሁድ በሚካሄደው ምርጫ ለፓርቲያቸው እጩ መራኄ መንግሥትነት የሚወዳደሩት መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ በቅርቡ በአንድ የግል ሬሴፕሽን ላይ አፍሪቃዊ የCDU ፖለቲከኛና የበርሊን ግዛት የባህል ሚኒስትር ጆ ችያሎን «የሐብታሞች አጫዋች» ሲሉ መጥራቸውን ነው። የሾልስ አባባል ዘረኛ ተብሎ ቢተችም  ሾልስ ግን በትዊተር ገጻቸው ቃሉን መናገራቸውን ባይክዱም አባባሉ ዘረኛ እንዳይደለ በዘረኝነት ታስቦ የተነገረ አይደለም ሲሉ አስተባብለዋል።  በዚህ ጉዳይ ላይ ወደ ፍራንክፈርት ተጉዞ የነበረው የጋዜጠኞች ቡድን የፍራንክፈርት የSPD እጩ ተወዳዳሪ የሆኑት ካሜሩናዊ  ጀርመናዊ አርማንድ ዞርንም ኦላፍ ሾልስ ያሉት በፍጹም ከዘረኝነት ጋር እንደማይያዝና ለቃሉም ይቅርታ መጠየቃቸውን ገልጸዋል።

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሔር
ኂሩት መለሰ