1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጃል መሮና መንግሥት፤ የጌታቸዉ ረዳ ርምጃ፤ አከራካሪዎቹ ቦታዎች

ዓርብ፣ ጥቅምት 30 2016

በአሸባሪነት የፈረጀዉ የኦነሰ ሰራዊት አዛዥ ኩምሳ ዲሪባ፤ ከመንግሥት ተወካዮች ጋር ሊደራደሩ መሆኑ፤ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ፤ ከፍተኛ የህወሓት ባለስልጣናትን ከስልጣን ማንሳታቸዉ፤ እንዲሁም የትግራይና የአማራ ክልሎች የሚወዛገቡበት ቦታ በሕዝበ ዉሳኔ መልስ ያገኛል መባሉ ላይ የተሰጡ አስተያየቶች ተሰባስበዉበታል።

https://p.dw.com/p/4YgRF
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር  አርማ
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አርማ ምስል Michael Tewelde/AFP

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የኢትዮጵያ መንግስት «ኦነግ-ሸኔ» በሚል ስም በአሸባሪነት የፈረጀዉ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አዛዥ  ኩምሳ ዲሪባ ፤ ከመንግሥት ተወካዮች ጋር ሊደራደር ታንዛንያ ዳሬሰላም ገባ መባሉ፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ፤  ከፍተኛ የህወሓት ባለስልጣናትን ከስልጣን ማንሳታቸዉ፤ እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግሥት በሰሜናዊ ኢትዮጵያ የትግራይ እና የአማራ ክልሎች በይገባኛል የሚወዛገቡበት ቦታ በሕዝበ ዉሳኔ መልስ እንደሚያገኝ መግለፁ፤ በተሰኙ ርዕሶች ላይ የተሰጡ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚ አስተያየቶችን ሰብስበን ይዘናል ።ስለ ታንዛንያው ድርድር የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች ተስፋ

የኢትዮጵያ መንግስት «ኦነግ-ሸኔ» በሚል ስም በአሸባሪነት የፈረጀዉ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አዛዥ  ኩምሳ ዲሪባ (ጃል መሮ) የተገኙበት በፌዴራል መንግስት እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መካከል ሁለተኛ ዙር የሰላም ንግግር መጀመሩን የዲፕሎማሲ ምንጭ በዚሁ ሳምንት ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል።  ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ምንጭ በመንግስት እና በታጣቂ ቡድኑ መካከል ሁለተኛ ዙር ንግግር እንዲጀመር ከሁለት ሳምንት በላይ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ልዑካንን በመወከል በጄኔራል ጌታቸው ጉዲና የሚመራ የተደራዳሪ ቡድን ድርድሩ ወደ ሚደረግበት ታንዛንያ  ዳሬ ሰላም መድረሳቸው ተገልጿል። የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ዋና አዛዥ ኩምሳ ዲሪባ (ጃል መሮ) እና ምክትላቸው ገመቹ እንዲሁም የታጣቂ ቡድኑ ደቡብ ኦሮሚያ አዛዥ ገመቹ ረጋሳ በድርድሩ ላይ ለመሳተፍ ወደ ስፍራው ማቅናታቸውን ምንጫችን አረጋግጠውልናል። ከመንግስት የተደራዳሪ  ቡድን ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት እንደሚገናኙ የሚጠበቀው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ዋና አዛዥ ኩምሳ ዲሪባ (ጃል መሮ) ከሚገኙበት ምዕራብ ወለጋ ዞን ቤጊ ወረዳ በምስራቅ አፍሪቃ በይነ መንግስታት ኢጋድ የአሜሪካ እና የኖርዌይ መንግስታት አስተባባሪነት በአየር በቅድሚያ ወደ ናይሮቢ መወሰዳቸውን የገለጹልን ምንጫችን ዋና አዛዡ ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ፊት ለፊት መገናኘታቸው በኦሮሚያ ክልል ለአምስት ዓመታት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ጦርነት እልባት ለማበጀት ጥርጊያ እንደሚያበጅ እምነታቸው መሆኑን ገልፀዋል።   የኦነግ የአገር ማረጋጋት ጥሪና የመንግሥት አስተያየት

የአባይ ድልድል
የአባይ ድልድልምስል Seyoum Getu/DW

በጣም ደስ የሚል ዜና አላህ ሰላም ያርጋችሁ፤  ያስማማችሁ ሲሉ አስተያየታቸዉን ያስቀመጡት የፌስቡክ ተጠቃሚ አብዱልሰመድ አብዱላሂ ናቸዉ ።

ነሲቡ ከ ማራሚ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ ፤ ድርድሩ ካለፈው ጉዳይ ይልቅ፤ ለወደፊቱ፤ የሕዝብ ጥቅምን አብሮነት መቻቻልን ማዕከል ያደረገ፤ የቀደምት ኦሮሞ  ገዳ ስርዓትን የሚያንፀባርቅ ውይይት እንዲሆን እመኛለሁ።  ለሌሎችም ተምሳሌት ሆኖ የሚመዘገብ እንደሚሆን ተስፋ አድርጋለሁ ብለዋል። 

ያረቢ ሰላም ለኢትዮጵያ ሲሉ አስተያየታቸዉን የጀመሩት ደግሞ አህመድ የወሎልጅ የተባሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ ናቸዉ። ጃል መሮን ቀጥታ አራት ኪሎ አምጥታችሁ፤  ከአብይ ጋር በበቀጥታ ስርጭት አነጋግራችሁ ችግራቸዉን ይፍቱ። የፋኖ ችግር የለዉም።  በመንደር ሽማግሌ ችግሩ ይፈታል ሲሉ አስተያየታቸዉን ቋጭተዋል።

ያሬድ አሰፋ ይመር የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፤ አደራዳሪው IGAD ወርቅነህ ገበየሁ፣ የኦነግ መሪው ድሪባ ኩምሳ፣ የኢትዮጵያን መንግሥት የወከለው ጄነራል ጌታቸው ጉዲና ሲሆኑ ሁሉም ኦሮሞዎች ናቸው። ታዲያ ድርድሩ በኦሮሞ ወገኖቻችን መካከል ነው ብንል አይሻልም? ሲሉ በጥያቄ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል።

መልካም ዜና ነዉ፡ በሁለቱም በኩል የአቋም ለዉጥ ያስፈልጋል፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን የጀመሩት ኢማሙ አህመድ አጋዜ የተባሉ ናቸዉ። የአቋም ለዉጥ ያስፈልጋል። ከሚያለያዩ ነገሮች ይልቅ በሚያግባቡ ጉዳዮች ላይ አተኩረዉ ቢወያዩ ለኦሮሚያ ክልል ህዝቦች ብቻ ሳይሆን፤ ለመላዉ ኢትዮጵያ ህዝቦች መልካም የሚባል የፓለቲካ ልምምድ ይሆን፤ ብለዋል።

በትግራይ ክልል የከፍተኛ ባለስልጣናት ከኃላፊነት ማመነሳት

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ፤ አራት የክልሉን ከፍተኛ ባለስልጣናት ከኃላፊነት ማንሳታቸዉ በዚህ ሳምንት አበይት ሆነዉ ከተሰሙ ዜናዎች መካከል አንዱ ነዉ። የሕወሓት ጽ/ ቤት ኃላፊ አቶ ዓለም ገብረዋህድን ጨምሮ በጌታቸዉ ረዳ ከኃላፊነታቸው የተነሱ ባለሥልጣናት በፓርቲውም ሆነ በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ከፍተኛ ሚና የነበራቸው ነበሩ። የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፤  እስካሁን 10 ከፍተኛ እና መካከለኛ የህወሓት አባላትን ከአስተዳደራቸው ከኃላፊነት ማንሳታቸዉ ተዘግቧል።የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር አራት ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ሻረ

እኔ ነኝ የሚል የፌስቡክ መጠቀምያ ስም ያላቸዉ የፌስቡክ ተከታታይ፤ አቶ ጌታቸው ረዳ የለውጥ ሰው ነው።  ትግራይ ካለችበት አዘቅት ውስጥ በሰላማዊ መንገድ ለማውጣት የሚፈልግ በሳል ፖለቲከኛ ነው ። የህወሓት ሰዎች ደሞ ሁሉም ነገር በጦርነት መፍታት አለብን ብለው የሚያምኑ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ወጣቶችን ያስጨረሱ አሁንም ከስህተታቸው የማይማሩ ሰዎች ናቸው። ስለዚህ  አቶ ጌታቸው እነዚህን አላሰራ ያሉትን የህወሓት ካድሬዎች፤ አንድ በአንድ ፤ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ማስወገድ አለባቸዉ ሲሉ ምክረሃሳብ አስቀምጠዋል።  

ዋው አሪፍ ነው ሲሉ አስተያየታቸዉን የጀመሩት ተስፋለም መሃሪ ናቸዉ። ዋው አሪፍ ነው፤ እንኳን ደስ ያላችሁ። የትግራይ ህዝብ በተለይ ወጣቶች በህይወታቸዉ  ለውጥ ማየት ይፈልጋሉ፤ ብለዋል።

በገብረአምላክ ቢደማርያም የተባሉ ሌላ አስተያየት ሰጭ፤ የአብይ እጅ አለበት፤ አብይ የፕሪቶርያውን ስምምነት ላለመፈፀም እያቅማማ ነው ፤ የትግራይ መሬት በፋኖና ሻዕብያ አስወርሮ፤ እሱ  ተረጋግቶ ኢትዮጵያን እንደማያስተዳድር ሁሉም ማወቅ አለበት ሲሉ ማስጠንቀቅያ አዘል አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል።

ሰለሞን ሰለሞን የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ በበኩላቸዉ፤ በወጣት እና ተራማጅ አስተሳሰብ ባላቸው፤ ከተቸከለ ፖለቲካ ወጣ ብለው፤ የትግራይን ህዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር፤ በዘላቂነት በሰላም አብሮ የሚኖርበትን መንገድ የሚያሳዩ ፖለቲከኞች  መሾም አለባቸዉ፤ ሲሉ አስተያየት አስቀምጠዋል።

ክንደዉ ዮሴፍ የተባሉ ሌላዉ የፌስቡክ ተከታታይ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ያደረገዉን ከስልጣን የማንሳት እርምጃ « ጉዞ ወደ ብልጽግና» ሲሉ ሽሙጥ መሰል አስተያየታቸዉን ጽፈዋል።   

ከመጀመሪያውም አቶ ጌታቸው ረዳ ወደፊት ቢመጣ ኑሮ ጦርነቱን ማስቀረት ይቻል ነበር የሚል ግምት ነበረኝ፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን የጀመሩት አማረ ገነት ይባላሉ። ከመጀመሪያውም አቶ ጌታቸው ረዳ ወደፊት ቢመጣ ኑሮ ፤አሁንም ቢሆን አቶ ጌታቸው የሚከተሉት የሰላም መንገድ ጅማሬው ትግራይ ቢሆንም፤ መላው ኢትዮጵያን ሊገዛ የሚችል ነው።  ነገር ግን እንደ አራት ኪሎው ሰውዬ የተሻለ ልምድ ያላቸውን መሪዎች መግፋታቸዉ  ትክክል አይመስለኝም ሲሉ ምክረ አዘል አስተያየታቸዉን አጋርተዋል።

መንግስት "አከራካሪ አካባቢዎች" ያላቸዉ ቦታዎች ጉዳይ

የኢትዮጵያ መንግስት የፕሪቶሪያ ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መሆን አለበት ሲል መግለጫ አዉጥቷል። መንግስት "አከራካሪ አካባቢዎች" በማለት የገለጸው ግዛት ደረጃ በደረጃ በህገ መንግሥቱ መሠረት ህዝበ ውሳኔ እንዲደረግ አቅጣጫ ተቀምጧል» ሲል በዚሁ ሳምንት ገልጿል። መንግሥት "አከራካሪ አካባቢዎች" ያላቸዉ በሰላም መፍትሄ ማግኘት አይችሉም ? ለሚለዉ ጥያቄ አስተያየት ከሰጡ የዶቼ ቬለ ተከታታዮች መካከል

ሰለሞን አሰፋ ፤ ሕዝበ ውሳኔ  በተሻለ ሁኔታ ተመራጭ መሆን አለበት፤ ሲጀመር ወልቃይት፥ ራያና ሁመራ የአማራ ክልል ድንበር መሆኑ ሀገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው።  ስለዚህ የአማራና የትግራይ ሕዝብ ተዛዝነውና ተሳስበው አብረው ለመብላት ቢነጋግሩ ይሻላል፤ ሲሉ አስተያየት ጽፈዋል። 

የጫሙት ሽካ የተባሉ ሌላ አስተያየት ሰጭ፤ መፍትሄው ሕዝበ ውሳኔ ነው።  ከዚህ ውጪ በኃይል አካባቢውን መቆጣጠር ዘላቂ የጦርነት ቀጠና ማድረግ ነዉ። ለህዝቡ ሦስት አማራጮች ሊቀርቡለት ይገባል።

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት
የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ምስል Jaap Arriens/NurPhoto/IMAGO

አማራጭ አንድ፤ ራያ እና ወልቃይት እራሳበደቡብና ምዕራብ ትግራይ የነበሩ የአስተዳደር መዋቅሮች ይፈርሳሉ ስለመባሉቸው የቻሉ ክልል እንዲሆኑ፤ አማራጭ ሁለት፤  በአማራ ክልል እንዲተዳደሩ፤ አማራጭ ሦስት፤  በትግራይ ክልል እንዲተዳደሩ ከዚህ ውጪ ዘላቂ ሰላም ሊመጣ አይችልም ሲሉ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል።

ተመስገን የሁሉ ጌታ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፤ መንግስት ከሴራ እና ከተተበተበ ፖለቲካ ነፃ ቢሆን ኑሮ፤ ብዙ የመፍትሄ ሀሳቦችን አያጣም ነበር። ዳሩ መንግስት አጀንዳውን ለዕድሜው ማራዘምያ ፍጆታ አድርጎት ስላሰበው ነው። ግን የሁለቱ ክልል ህዝብና ነዋሪ፤ ሚስጢሩን በደንብ ደርሶበት፤ አንድነት በፈጠረ ጊዜ መንግስት ብዙ ዋጋ ይከፍላል ሲሉ ማስጠንቀቅያ አዘል አስተያየታቸዉን አጋርተዋል።

 አቤል ስዩም የተባሉ ሌላዉ አስተያየት ሰጭ፤ ማንም ይምራ ማን፤ ሰው ከመሬት በላይ እንጂ ከመሬት በታች አይደለም ይላሉ። ሰዉ ከመሪት በላይ ነዉ። መጀመርያ ሰው መቅደም አለበት።  ሰው ከሁሉ በላይ ክቡር ነው።  ስለዚህ እኔ ቅድሚያ የምሰጠው ለሰዉ ነዉ።  ለመሬት ተብሎ ሰው መገደል መፈናቀል መራብ የለበትም። ጠባብ ጭንቅላት እንጂ ጠባብ መሬት የለንም፤ ሲሉ አቤል አስተያየታቸዉን ደምድመዋል። አስተያየቶችን ያሰባሰብንበት የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝትን  ዝግጅትችን ለማድመጥ የድምፅ ማዕቀፉን ይጫኑ።  

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ