1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር አራት ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ሻረ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 28 2016

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ አራት የክልሉን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከሃላፊነት አነሱ ። የህወሓት ጽሕፈት ቤት ሐላፊ አቶ ዓለም ገብረዋህድን ጨምሮ በፕሬዝደንቱ ከሃላፊነታቸው የተነሱ ባለሥልጣንት በፓርቲው ሆነ በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ከፍተኛ ሚና የነበራቸው ናቸው ተብሏል።

https://p.dw.com/p/4YZlp
 ፎቶ፤ የህወሃት ጽሕፈት ቤት መቀለ
በትግራይ ክልል አራት ባለሥልጣናት ከሃላፊነት መነሳታቸው እያነጋገረ ነው። ፎቶ፤ የህወሃት ጽሕፈት ቤት መቀለምስል Million Hailesilassie/DW

አራት ባለሥልጣናት መነሳታቸው

ሰሞኑን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት እና የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ እየወሰዱት ካለ፥ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ከሐላፊነት የማውረድ እርምጃ በመጥቀስ፥ ህወሓት የውስጥ መከፋፈል እንደገጠመው ብዙዎች እየገለፁ ይገኛሉ። ትናንት የተሰራጩ ደብዳቤዎች የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ የህወሓት ጽሕፈት ቤት ሐላፊ የሆኑት እና በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በምክትል ፕሬዝደንት ማዕረግ የፕሬዝደንቱ «የሕዝብ ማነሳሳት ጉዳዮች አማካ»' የነበሩት ከአቶ ዓለም ገብረዋህድን ጨምሮ፥ የፕሬዝደንት ጽ/ቤት (ቺፍ ካቢኔ ሴክተርያት) አቶ አማኑኤል አሰፋ ፣ የትግራይ ሰሜን ምዕራብ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ተክላይ ገብረመድህን እና የትግራይ ደቡብ ምሥራቅ ዞን አስተዳዳሪ ወ/ሮ ሊያ ካሣ ከመንግሥታዊ ሐላፊነታቸው መነሳታቸውን አመላክተዋል። ከሃላፊነታቸው የተነሱ የቀድሞ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በህወሃት ውስጥ የሥራ አስፈጻሚ እና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ያላቸው ናቸው።

ከፍተኛ ባለሥልጣናቱ ከሃላፊነታቸው መነሳታቸውን ተከትሎ ቀደም ሲል በሕወሓት ውስጥ መከፋፈል ስለመፈጠሩ ይሰራጩ የነበሩ መረጃዎችን ያጠናክራል ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ። ስለተወሰደው እርምጃ ማብራርያ የጠየቅናቸው የትግራይ ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሐላፊ አቶ ረዳኢ ሓለፎም የተወሰደው እርምጃ ማነኛውም አስተዳደር የሚያደርገው የተለመደ ተግባር ነው ሲሉ ገልፀውታል። «ሰዎች መመደብም፣ ሰዎች ከምደባቸው ማንሳትም የአንድ መንግሥት መደበኛ ሥራ ተደርጎ የሚታይ ነው» በማለት አቶ ረዳኢ ሓለፎም እርምጃው የተለየ መልክ የሌለው ነው ሲሉ ገልፀዋል።

የትግራይ ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ሐላፊ እና የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ አባሉ አቶ ረዳኢ ሓለፎም
የትግራይ ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ሐላፊ እና የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ አባሉ አቶ ረዳኢ ሓለፎም ምስል Million Hailesilassie/DW

በህወሓት ውስጥ የሐሳብ ልዩነት እና ግልፅ ልዩነት ስለመኖሩ የተጠየቁት የትግራይ ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ሐላፊ እና የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ አባሉ አቶ ረዳኢ ሓለፎም በህወሓት ውስጥ የተለመደ የሐሳብ ልዩነት አለ፣ ሁሌም ግን ብዙሃኑ ያሸንፋል ሲሉ ገልፀዋል።

በሰሞነኛው የህወሓት እና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እሰጥ አገባ ዙርያ አስተያየታቸው ያጋሩን የሕግ ምሁሩ እና ኹነቱን በቅርበት የሚከታተሉት አቶ የማነ ካሣ የጊዜያዊ አስተዳደሩን እርምጃ በህወሓት ውስጥ የቆየ መከፋፈል በግልፅ በአደባባይ ያሳየ ብለውታል። አቶ የማነ ካሣ ጨምረውም ይህ ክፍፍል በተለይም ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በኋላ ከታየው የህወሓት ክፍፍል የሚያመሳስል እና የሚለይበት ምልክቶች እንዳሉትም አስረድተዋል። በዚህ ጉዳይ ዙርያ ከህወሓት ጽሕፈት ቤት እና ከሥልጣን ከታገዱት አመራሮች ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። ከዚህ ቀደምም እንዲሁ በየዞኑ የነበሩ የፖለቲካ ጉዳዮች አማካሪዎች ከሥልጣናቸው እንዲነሱ ተደርገዋል። ከቀናት በፊት ህወሓት በመቐለ ሊያደርገው ያቀደው የካድሬዎች ስብሰባ፥ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር «ሕገወጥ» በማለት ኮንኖት እንደነበርም ይታወሳል።

ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ