1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማሕደረ ዜና፣ ዕዉቅና የሌላት ሪፐብሊክ ዕዉቅ የፖለቲካ ሥርዓት

ነጋሽ መሐመድ
ሰኞ፣ ኅዳር 16 2017

የያኔዉን የአየር ኃይል ኮሎኔል ሙሴ ቢሒ አብዲን የመሰሉ ዕዉቅ የጦር መኮንኖችን የሚያስተናብረዉ ተዋጊ ቡድን ሕዝብ አወያየ።ቡድኑና መሪዎቹ ኢትዮጵያን ጨምሮ የብዙዎቹ ሐገራት የቀድሞ አማፂ ኃይላት እንደሚያደርጉት የዉይይት፣ክርክሩን ሒደትን በጠመጃ አላፈኑም፤ እነሱን እንደሚመች አልጠመዘዙትምም ።በሕዝብ በጣሙን በጎሳ መሪዎችና በልሒቃን ምክር---

https://p.dw.com/p/4nPuq
የሶማሊላንድ ሕዝብ በየጊዜዉ የወደፊቱን ፕሬዝደንትና የምክር ቤት አባላትን ይመርጣል።በዘንድሮዉ ምርጫም ወደ 700 000 የሚጠጋ ሕዝብ ድምፅ ሰጥቷል
ከ1991 ጀምሮ ራስዋን እንደ ነፃ መንግስት የምትቆጥረዉ የሶማሊላንድ ሕዝብ በየአምስት ዓመቱ ፕሬዝደንቱን ለመምረጥ ድምፁን በነፃነት ይሰጣል።ሰልፉ በ2017 የተደረገዉ ምርጫ ጊዜ ነዉ።ምስል Getty Images/AFP

ማሕደረ ዜና፣ ዕዉቅና የሌላት ሪፐብሊክ ዕዉቅ የፖለቲካ ሥርዓት

በቆዳ ሥፋት ከኢትዮጵያዉ የአማራ ክልል የምታንስ፣176 ሺሕ 120 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ግዛት የምታካልል ትንሽ ናት።ግን ታሪካዊ።ደሐ ናት።ግን ሥልታዊ።አንድም ሐገር እንደ መንግሥት አያዉቃትም።ግን የዓለም ሐያላን፣ የአረብ ሐብታሞች፣ የአፍሪቃ ብልጦችም ሲፈልጓት ይወዳጇቷል፤ ሥልታዊነቷን ይጠቀሙበታል።ሶማሊላንድ።በቅርቡ ባደረገችዉ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ደግሞ መቻቻል፣ሰጥቶ መቀበል፣የአሸናፊ-ተሸናፊዎችን ትዕግሥትና ብልሐትን ለአራተኛ ጊዜ አስመከሰረች።የምርጫዉ ሒደት ዉጤት መነሻ፣ የፖለቲከኛ፣የጦርና የጎሳ መሪዎችዋ ብልሐት ማጣቃሻ አስተምሕሮቱ መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።

የአፍሪቃ ቀንድ የግጭት፣ ዉዝግብ የአምባገነቶች ማዕከል

የሶማሊያ ፌደራል ሪፐብሊክ ዘንድሮም እንደአምና ሐቻምናዉ በዉዝግብ፣ ግጭት፣ሽብር ትተራመሳለች።33 ዓመቷ።ጅቡቲ እንደ ዴሞክራሲዉ ወግ ምርጫ ታደርጋለች።በ1977 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ነፃ ከወጣች ወዲሕ የምታዉቀዉ መሪ ግን ሁለት ነዉ-የመጀመሪያዉ ሲሞቱ ሁለተኛዉ ተተኩ።በቃ።

ሱዳኖች ሁለት ጄኔራሎች ባበቀሉት ጠብ ሰበብ ሰላምንም፣ የሕዝብ ጥያቄ፣ ዴሞክራሲንም ረስተዉ እርስ በርስ ዉጊያ ላይ ናቸዉ።ደቡብ ሱዳን ከ30 ዓመታት ጦርነት፣ ከአምስት ዓመት ሽግግር በኋላ በ2011 ነፃነትዋን አወጀች።በቅድመ-ነፃነት የካርቱም ገዢዎችን በጋራ ሲወጉ የነበሩት ፖለቲከኞች የጁባ ቤተ መንግስት የምቾት ኑሮ አላመቻች ብሏቸዉ በ2013 ዉጊያ ገጠሙ።

በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግምት 4 ሚሊዮን ሕዝብ የፈጀዉ ጦርነት ከቆመም በኋላ የዚያች አዲስ ሐገር አዳዲስ ገዢዎች ምርጫ ማስተናገድ፣ተባብሮ መግዛት፣ ዘላቂ ሠላም ማስፈንም አልቻሉም ወይም አልፈለጉም።

ኤርትራ ከብዙ ዓመታት ጦርነት በኋላ በ1991 Defacto ወይም ይፋ ያልሆነ፣ በ1993 በይፋ ነፃ መንግሥት መሥርታለች።ያኔ ግንቦት በተደረገዉ ሕዝበ ዉሳኔ ከመቶ በ99.8 ድምፅ ከኢትዮጵያ መገንጠልን ያፀደቀዉ የኤርትራ ሕዝብ እስከ ዛሬ ምርጫ፣ ሕገ-መንግሥት፣ ምክር ቤት፣ ነፃ መገናኛ ዘዴ አያዉቅም።የሚያዉቀዉ አንድ መሪ፣ ከጎረቤቶች ጋር ተደጋጋሚ ጦርነት፣ ዉዝግብና ምናልባት ሥደትን ነዉ።

በ1991 የአዲስ አበባን ቤተ መንግሥት የተቆጣጠሩት የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች የኤርትራን ነፃነት ደግፈዉ ለኢትዮጵያ የሕግ የበላነትን፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን፣የመድብለ ፓርቲ አገዛዝን ለማስረፅ፣ የሰብአዊ መብትን ለማስከበር እንደሚጥሩ ያልገቡት ቃል አልነበረም።በ2018 የሕዝብ አመፅ እስኪያስገድዳቸዉ ድረስ ግን ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ መፍቀድ፣ ሥልጣናቸዉን ለሌላ ማስረከብ ዓይደለም እርስበራሳቸዉ መተካካትን እንኳን አልፈቀዱም።

በ2018 ሥልጣን ያስረከቡትና የተረከቡት የቀድሞ የአንድ ግንባር አለቃና ምንዝሮች በ2020 ሕዝባቸዉን ከጦርነት የመሰጉበት አንዱ ትልቅ ምክንያት በምርጫ ጊዜ ይራዘም-አይራዘም ተጣልተዉ ነዉ።የአዲስ አበባና የመቀሌዎች ጠብ መቶ ሺዎችን አርግፏል።ሚሊዮኖችን አፈናቅሏል።በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሐብት ንብረት አዉድሟል።

የሶማሊላንድ ርዕሰ ከተማ ሐርጌሳ።ሐርጌሳ ለሶማሊላንድ የፖለቲካ ዋና ከተማ ብቻ ሳትሆን የኤኮኖሚም፣ የወደብ ከተማም ናት
የሶማሊላንድ ርዕሰ ከተማ ሐርጌሳ።ሐርጌሳ ለሶማሊላንድ የፖለቲካ ዋና ከተማ ብቻ ሳትሆን የኤኮኖሚም፣ የወደብ ከተማም ናትምስል Eshete Bekele/DW

ኢትዮጵያ ሰፊ ግን ግጭትና ጦርነት የሚያደቃት፣ ታሪካዊ ግን ወደብ አልባ፣ የአፍሪቃ የነፃነት አብነት ግን ሚሊዮኖች በፖለቲካ ነፃነት እጦትና በሰላም መታወክ የሚማቅቁባት፣ የ120 ሚሊዮኖች ሐገር ግን ደሐ ናት።

የሶማሊላንድ ልዩ አብነት

ከሱዳን እስከ ሶማሊያ፣ ከኤርትራ እስከ ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ እስከ ጅቡቲ የሚገኙ ሐገራት አንድም አንዳቸዉ ከሌላቸዉ፣ ሁለትም በግጭት ጦርነት ሲተራመሱ፣ሶስትም በአንባገነኖች ጭቆና ሲማቅቁ ያቺ የመንግሥትነት ዕዉቅና የሌላት ግዛት ከ1991 ጀምሮ የሕዝቧን ነባር የጎሳ ባሕል ከዘመኑ ዴሞክራሲዊአስተሳሰብ ጋር ቀይጣ የሰላም ብልፅግና ቀና ጉዞ ጀምራለች።ሶማሊላንድ።

የሶማሊላንድ የፖለቲካ ጉዞ የተሟላ፣ ሁሉን አስደሳች፣ አብነታዊ ነዉ ማለት በርግጥ ያሳስት ይሆናል።በሁሉም መመዘኛ ግን ሥርዓቱ ብዙዎቹን የአካባቢዉ ሐገራት ሕዝብን የሚያስቀና ነዉ። የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ምክር ቤት እንደራሴ ዶክተር አብዲ መሐመድ ቡባል እንደሚሉት የሶማሊላንድ የፖለቲካ ሥርዓት ብዙ ሚስጥር የለዉም።መሠረቱ እንጂ።

«የሶማሊላንድ መሠረት በሕዝቦች ሥምምነት ነዉ የተመሠረተችዉ።እንደሚታወቀዉ በ1991 የሶማሊያዉ የዚያድ ባሬ መንግሥት ሲፈርስና ሐገሪቱ ወደ ሽግግር የመሔዷ ሁኔታ ሳይሳካ ሲቀር፣ሶማሊላንድ የነበረዉ SNM የሚባለዉ ታጣቂ ቡድን፣የሲቢል ማሕበራትን፣ የጎሳ መሪዎችን፣የሐገር ሽማግሌዎችንና የተለያዩ አካላትን በማሳተፍ ቡርኦና ቦረማ የሚባል ስብሰባና ዉይይቶች አድርጓል።በዚሕም ምክንያት ሶማሊላንድ በስምነት ነዉ የተመሠረተችዉ።በመግባባት፣ በዉይይት መሠረት የጣለች---»

በ1980ዎቹ ማብቂያ የያኔዉን የሶማሊያ ገዢ የመሐመድ ዚያድ ባሬን መንግሥት በነፍጥ ይወጉ የነበሩት አብዛኞቹ አማፂ ኃይላት በኢትዮጵያ ይደገፉ ነበሩ።ከነዚሕ አማፂያን መካከል የሶማሊያ ብሔራዊ ንቅናቄ (SNM) በ1991 ሐርጌሳን እንደተቆጣጠረ የንቅናቄዉን መሪ አብዲረሕማን አሕመድ ዓሊ ቱሬን በጊዚያዊ አስተዳዳሪነት ሾመ።

የያኔዉን የአየር ኃይል ኮሎኔል ሙሴ ቢሒ አብዲን የመሰሉ ዕዉቅ የጦር መኮንኖችን የሚያስተናብረዉ ተዋጊ ቡድን ሕዝብ አወያየ።ቡድኑና መሪዎቹ ኢትዮጵያን ጨምሮ የብዙዎቹ ሐገራት የቀድሞ አማፂ ኃይላት እንደሚያደርጉት የዉይይት፣ክርክሩን ሒደትን በጠመጃ አላፈኑም፤ እነሱን እንደሚመች አልጠመዘዙትምም ።ይልቅዬ በሕዝብ በጣሙን በጎሳ መሪዎችና በልሒቃን ምክር መሰረት የንቅናቄዉ አባል ያልሆኑት የቀድሞዉ የሶማሊያ ጠቅላይ ሚንስትር መሐመድ ሐጂ ኢብራሒም ኢጋል ፕሬዝደንት ሆኑ።

ሐርጌሳ የሚገኘዉ የዉጊያ መታሰቢያ ሐዉልት።የሶማሊላንድ ሕዝብ ከዚያድ ባሬ አገዛዝ ነፃ ለማዉጣት ከፍተኛ ተጋድሎ አድርጓል
የሶማሊላንድ ሕዝብ ጥንት ከብሪታንያ ቅኝ አገዛዝ ነፃ ለመዉጣት በ1990ዎቹ ማብቂያ አካባቢ ደግሞ ከዚያድ ባሬ አገዛዝ ነፃ ለመዉጣት ከፍተኛ ተጋድሎ አድርጓል።የዉጊያዉ መታሰቢያ ሐዉልትምስል Eshete Bekele/DW

«እሳቸዉ (ኢጋል) የSNM ታጣቂ ቡድን አባል አልነበሩም።ታጋይ አልነበሩም።ከሶማሊያ ነፃነት መሥራቾች አንዱ ነበሩ።እስከ ጠቅላይ ሚንስትር ደርሰዉ ከዚያም ታሥረዉ ነበር።እና በልምድም፣ በዕዉቀትም በጣም የተካኑ ሰዉ ነበሩ።አስተዋፅኦ አድርገዋል።ዋናዉ ግን እስከ ዛሬ ሶማሊላንድ----አስተማማኝ ዴሞክራቲክ ኢንስቲትዎችን መገንባት ላይ መሠረቱ ዉይይትና ሰጥቶ መቀበል ባሕል ሆኗል።»

የማይታለፉ የሚመስሉ ሶማሊላንድ ፈተናዎች

ሶማሊላንድ ከዉጪ ከሞቃዲሾ አስተዳደር፣ ከወዳጆቹ፣ ከምዕራብ ኃያላን፣ ከሐብታም አረቦች፤ከአካባቢዉ መንግሥታትም ከፍተኛ ጫናና ግፊት ተለይቷት አያዉቅም።የአሸባሪዎች፣ የወርሮበሎች፣ የሕገወጥ ሰዉ አሸጋጋሪዎች አደጋን መቋቋም፣ የተለያዩ ጎሳ አባላትን ፍላጎት ማጣጣም፣ የሕዝቡን የምጣኔ ሐብት ፍላጎት ማርካት በርግጥ ሲበዛ ከባድ ነዉ።

በዚሕ ሁሉ ጫና፣ ግፊትና ፈተና መሐል በ1991 በሕዝብ ዉይይት፣ ፈቃድና ይሁንታ የተመሠረተዉ ፖለቲካዊ ሥርዓት ሳይታጎል ቀጥሏል።ባለፈዉ ሕዳር 4 ደግሞ አራተኛዉን ፕሬዝደንታዊ ምርጫ አስተናግዳለች።

ምርጫዉ፣ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሒ አብዲ ድምፅ ሲሰጡ እንዳሉት ለሶማሊላንድ ሕዝብ ድል ነዉ።

በዚሕ ምርጫ ሁሉም ሶማሊላንዳዊ ያሸንፋል።የሚያሸንፈዉ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ብቻ አይደለም።ድምፃችንን በሰላም ስነሰጥና ስንቆጥር ብሔራዊ ጥቅማችንና መንግሥታችን ድል ያደርጋሉ።»

ለሙሴ ቢሒ ዋና ተፎካካሪ ለአብዲረሕማን መሐመድ አብዱላሒ ግን ምርጫዉ ለለዉጥ የሚደረግ ነዉ።

«ለሶማሊላንድ ሕዝብ የምናገረዉ ለለዉጥ ድምፅ ስጥ ብዬ ነዉ።ለሶማሊላንድና ለሕዝቧ ስኬት ድምፅ ሥጥ።»

ሶማሊላንድ ዉስጥ ብሔራዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሶስት እንዳይበልጡ የሐገሪቱ ሕግ ይደነግጋል።በዘንድሮዉ ምርጫ የተወዳደሩትም በሥልጣን ላይ ያለዉን ፓርቲ ኮልምዬን የወከሉት ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሒ አብዲ፣ የዋነኛዉ ተቃዋሚ ፓርቲ የወጠኒ ሊቀመንበር አብዲረሕማን መሐመድ አብዲ ኢጋል (ኤሮ)ና የፍትሕና የበጎ አድርጎት ፓርቲ ተወካይ ፈይሰል ዓሊ ወራቤ ነበሩ።

ሁለቱ ዋነኛ ተፎካካሪዎች ድምፅ ሲሰጡ በየፊናቸዉ እንዳሉት በርግጥም ሁለቱም ድል አደረጉ።ሙሴ ቢሒ አብዲ እንዳሉት ወደ ሰባት መቶ ሺሕ የሚጠጋ ሕዝብ በሰላም ድምፁን ሰጠ።ቆጠራዉም በሰላም ተጠናቀቀ።ሶማሊላንድ በጥቅሉ ድል አደረገ።በዚያዉ ልክ የዋነኛዉ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ አብዲረሒም መሐመድ አብዲላሒ እንደጠየቁት የሶማሊላንድ ሕዝብ ለለዉጥ ድምፁን ሰጠ።

የሶማሊላንድ ሕዝብ ለዉጥን ደገፈ

የቀድሞዉ የሶማሊላንድ እዉቅ ዲፕሎማት፣የምክር ቤት አፈ ጉባኤና ሥልት አዋቂዉ ፖለቲከኛ አብዲረሕማን መሐመድ አብዱላሒ ኢጋል (ኤሮ) አሸነፉ።የሐገሪቱ አስመራጭ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሴ ሐሰን ባለፈዉ ማክሰኞ።

«በዚሕ ዉጤት መሠረት የወጣኒ ፓርቲ የጊዚያዊ ድምፁን ዉጤት አሸንፏል።ይሕ ማለት ተመራጩ ፕሬዝደንት አብዲረሕም መሐመድ አብዱላሒ ኢጋል ናቸዉ።ተመራጩ ምክትል ፕሬዝደንት ደግሞ መሐመድ ዓሊ አብዲ መሐሙድ ናቸዉ።»

የቀድሞዉ የዓየር ሐይል ኮሎኔል፣ የሶማሌ ብሔራዊ ንቅናቄ (SNM) ተዋጊና ሶማሊላንድን ለሰባት ዓመት የመሩት የሙሴ ቢሒ አብዲ ፓርቲ ኮልምዬ ያገኘዉ ድምፅ ከሁለቱ ተቃዋሚዎች ያነሰ ነዉ።

የሶማሊላንድ ሕዝብ በሰባት ዓመት ፕሬዝደንቱ ላይ ፊቱን ያዞረበት ምክንያት ብዙ ነዉ።ዋና ዋናዎቹ ግን ዶክተር አብዲ መሐመድ ቡባል እንደሚሉት ሶስት ናቸዉ።

ሶማሊላንድ ዉስጥ በየጊዜዉ በሚደረገዉ mምርጫ አቅመ ደካሞች፣ አካል ጉዳተኞችና አዛዉንታት ሳይቀሩ በነቂስ እየወጡ ድምፃቸዉን ይሰጣሉ
ሶማሊላንድ ዉስጥ በየጊዜዉ በሚደረገዉ mምርጫ አቅመ ደካሞች፣ አካል ጉዳተኞችና አዛዉንታት ሳይቀሩ በነቂስ እየወጡ ድምፃቸዉን ይሰጣሉምስል DW/J. Jeffrey

« ሶስት መሠረታዊ ጥያቄዎች ይመሳላሉ ወጠኒ ፓርቲ እንዲያሸንፍ ያደረገዉ።አንደኛዉ ቅድም እንዳልከዉ ኤኮኖሚዉ ነዉ።ኤኮኖሚዉ ከኮቪድ (ወረርሽኝ) በኋላ ቀዝቅዟል።ሌላዉ ቅድም የገለፅከዉ ነዉ።በሙሴ ቢሒ ጊዜ የዉስጥ ግጭቶች ተበራክተዋል።ይሕ ሙሴ ቢሒንና የኮልምዬ ፓርቲን በጣም ጎድቶታል።ከኢትዮጵያ ጋር የተደረገዉ MOU (የመግባቢያ ሥምምነት)ም አሉታዊ ተፅዕኖ አድርጓል።በተለይ በአዉዴል አካባቢ---»  

የአዲሱ ፕሬዝደንት ብልሐትን የሚሹ ፈተናዎች

ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሒ አብዲ በጨዋ ደንብ የምርጫዉን ዉጤት በፀጋ ተቀብለዉታል።ለአሸናፊዉ ፖለቲከኛም እንደ ዴሞክራሲዉ ወግ የእንኳን ደስ ያለዎት መልዕክት አስተላልፈዋል።አዲሱ ፕሬዝደንት የሥራ አጡን ወጣት ፍላጎት ማርካት፣የጎሳ መልክና ባሕሪ ያለዉን ግጭት ማርገብ በተለይ ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር በተፈራረመችዉ የመግባቢያ ስምምነት ምክንያት የተከፋዉን የአዉደል አካባቢ ሕዝብን ጥያቄ መመለስ ግድ አለባቸዉ።

ከሙሴ ቢሕ አብዲ የበለጠ ለዘብተኛ አቋም ያራምዳሉ የሚባሉት ተመራጭ ፕሬዝደንት አብዲረሕማን መሐመድ አብዱላሒ ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር የተፈራረመችዉን የመግባቢያ ሥምምነት ዝርዝር ይዘት እንደማያዉቁት በምርጫ ዘመቻቸዉ ወቅት አስታዉቀዋል።እስካሁን ያላወቁትን ስምምነት አዉቀዉ ሥምምነቱ ከዉስጥም፣ ከሞቃዲሾና ከአዲስ አበባም ያስከተለዉን መዘዝ የሚለዝቡበት ብልሐት ግን ለጊዜ ሒደት የሚተዉ ነዉ።ቸር ያሰማን።  

ነጋሽ መሐመድ 

ፀሐይ ጫኔ