1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ እና የሶማሊላንድ ግንኙነት ዕድገት

ሰለሞን ሙጬ
ዓርብ፣ ጥቅምት 8 2017

ራስ ገዝ የሆነችውና የሶማሊያ ሪፐብሊክ መንግስት የራሴ አካል የሚላት ሶማሊላንድ ኢትዮጵያ ውስጥ ላላት የዲፕሎማቲክ ተልእኮ መገንቢያ የሚሆን ቦታ ከኢትዮጵያ መንግሥት መረከቧን ዐሳወቀች ። የመሠረት ድንጋይ መቀመጡ እውነት መሆኑን በአፍሪቃ ሕብረት እና ኢጋድ የሶማሊላንድ ልዩ መልእክተኛ የሆኑት አምባሳደር አብዱላሂ ሙሐሙድ ለዶቼ ቬለ አረጋግጠዋል።

https://p.dw.com/p/4lxzn
አምባሳደር አብዱላሂ ሞሐመድ
በአፍሪቃ ኅብረት እና ኢጋድ የሶማሊላንድ ልዩ መልእክተኛ የሆኑት አምባሳደር አብዱላሂ ሞሐመድ ከዶይቸ ቬለ ጋር ቃለ መጠይቅ ባ,ደረጉበት ወቅትምስል Solomon Muche/DW

የሶማሊላንድ ባለሥልጣን የመሠረት ድንጋይ መቀመጡ እውነት ነው አሉ

ራስ ገዝ የሆነችውና የሶማሊያ ሪፐብሊክ መንግስት የራሴ አካል የሚላት ሶማሊላንድ ኢትዮጵያ ውስጥ ላላት የዲፕሎማቲክ ተልእኮ መገንቢያ የሚሆን ቦታ ከኢትዮጵያ መንግሥት መረከቧን ዐስታወቀች ። የሶማሌላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኢሳ ካይድ «ወደፊት አዲስ አበባ ውስጥ ለሚኖረው የሶማሊላንድ ሪፐብሊክ ኤምባሲ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል» ሲል የራስ ገዟ ሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በቀድሞው ትዊተር በ X ገጹ አስፍሯል ። 

የመሠረት ድንጋይ መቀመጡ እውነት መሆኑን በአፍሪቃ ሕብረት እና ኢጋድ የሶማሊላንድ ልዩ መልእክተኛ የሆኑት አምባሳደር አብዱላሂ ሙሐሙድ ለዶቼ ቬለ አረጋግጠዋል። የሶማሊላንድ ባለስልጣናት የመሰረት ድንጋዩን ሲያስቀምጡ የሚያሳይ ምስል የተለቀቀ ሲሆን በጉዳዩ ላይ ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማረጋገጫ ለመጠየቅ ያደረግነው ጥረት ለጊዜው ምላሽ አላገኘም ።

ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ መንግሥት ለተልእኮዋ የሚሆን መሬት መረከቧን ግለፀች

ሶማሊያ ሊፋቅ በማይችል ሁኔታ የሉዓላዊ ግዛቴ አንድ አካል ናት የምትላት ሶማሊላንድ በፊናዋ ራስ ገዝ መሆኗን ነው የምታምነው። ይህንን መሠረት አድርጋ ከኢትዮጵያ ጋር የተፈራረመችው የባህር በር ማስገኛ የመግባቢያ ስምምነት የኢትዮጵያ እና የሶማሊያን ግንኙነት በእጅጉ አሻክሯል፣  በቀጣናውም አዳዲስ ጥምረቶችን እየፈጠረ ይገኛል።

ከየትኛውም ሀገር እውቅና ያላገኘችው ሶማሊላንድ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚኖራት ወይም ላላት ተልእኮ መቀመጫ የሚሆን ግንባታ ማከናወኛ መሬት በኢትዮጵያ መንግስት በልግስና  እንደተበረከተላት ትናንት አስታውቃለች። ይህም በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት በማጠናከር ረገድ ትልቅ እመርታ አለው በሚል ተገልጿል። በአፍሪቃ ኅብረት እና ኢጋድ የሶማሊላንድ ልዩ መልእክተኛ የሆኑት አምባሳደር አብዱላሂ ሞሐመድ ይህ እውነት መሆኑን ዛሬ ከዶቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አረጋግጠዋል። ምንም እንኳን ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል በዚህ ዙሪያ እስካሁን ምንም የተባለ ነገር ባይኖርም።

"ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳሉት ሌሎች ተልእኮዎች መሬቱን አግኝተናል። በኢትዮጵያ የሶማሊላንድን ተልእኮ የምናከናውንበት መሬት ተሰጥቶናል። እዚህ ቀድሞውኑም ጥሩ ተልእኮ አለን። ብዙ ሰራተኞችም አሉን። ኢትዮጵያም በሀርጌሳ ጥሩ የሚባል ትልቅ ትልእኮ አላት"።

ሶማሊላንድ በርበራ ወደብ
ሶማሊላንድ በርበራ ወደብምስል Eshete Bekele/DW

ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ባለፈው ጥር የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት ለሁሉም የቀጣናው ሀገራት በደህንነት፣ በልማት፣ በአካባቢያዊ ውህደት እና ቀጣናውን በማሳደግ ረገድ ትልቅ ዕድል ነው ያሉት የሥራ ኃላፊው፣ ሆኖም ግብጽ ወደ አካባቢቢው ዘልቃ በመግባት  እያደረገችው ያለው እንቅስቃሴ ለቀጣናው የፖለቲካ እና የፀጥታ ሁኔታ ትልቅ አደጋ እና ሥጋት የሚጋርጥ ነው ብለዋል።

"የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንሳ ኬይስ እና እኔ -  የሶማሌላንድ የአፍሪካ ሕብረት እና የኢጋፍ ልዩ መልዕክተኛ እንደመሆኔ፣ በኢትዮጵያ ተልዕኮአችንን በምንገነባበት መሬት ላይ የመጀመሪያውን ድንጋይ አስቀምጠናል። በእርግጥም አዲስ አበባ የአፍሪካ ሕብረት ልብ እና ማዕከል እንደመሆኗ ለአፍሪካ ሕብረት ጭምር ነው። ስለዚህ እኛን በሚመለከት ለዚሁ ሥራ ሀብት እና በጀት በቅርቡ እንመድባለን። በመሆኑም ይዋል ይደር እንጂ የሶማሊላንድን ተልእኮ በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ሕብረት በአዲስ አበባ እምብርት ላይ ታያላችሁ። ይህንን ቦታ ያዘጋጁትን የኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናትን እና የአካባቢ መስተዳድር ኃላፊዎችን እናመሰግናለን"።

ይህ ማለት ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ እውቅና አገኘች ማለት ነውን?

ስለዚህ ይህ ማለት ሶማሊላንድ በኢትዮጵያ መንግስት በይፋ ዕውቅና አግኝታለች ማለት ነው? በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ  "እንደዚያ አላልኩም። ሶማሊላንድ እስካሁን በኢትዮጵያ ዕውቅና አልተሰጣትም። ነገር ግን እንደሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የሶማሊላንድን እውቅና እንጠብቃለን። እና ደግሞ የመግባቢያ ስምምነቱ አካል የባህር በር ፣ እውቅና ማግኘት ነው። እና በእነዚህ ጉዳዮች ላይ እየሰራን ነው የምንገኘው"።

አምባሳደር አብዲላሂ በአካባቢው በግብጽ የሚመራ ጥምረት እየተፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው "ግብጽ በድንገት የሶማሊያ ወዳጅ የሆነችበት እና ዘልቃ የገባችበት ምክንያት ምንድን ነው"? የሚለው የሁሉም ጥያቄ ነው ብለዋል።

የሶማሊላንድ በርበራ ወደብ ከፊል ገጽታ
የሶማሊላንድ በርበራ ወደብ ከፊል ገጽታምስል Eshete Bekele/DW

በዚህ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው ምላሽ አላገኘም። ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር የገባችበት ብርቱ ውዝግብ በሰላም እንዲፈታ ግፊት የምታደርገው ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ እና "ድንበር ዘልሎ የሚመጣ ትርምስ" ስለማትፈልግ መሆኑን የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአሁኑ ርእሠ ብሔር ታዬ አጽቀ ሥላሴ በቅርቡ አስታውቀው ነበር።

ኢትዮጵያ ሶማሊላንድ - ሀርጌሳ ውስጥ በልዩ መልዕክተኛ ደረጃ ለነበረው ቆንስላ ጽሕፈት ቤቷ አምባሳደር ተሾመ ሹንዴን ከወራት በፊት መሾሟ ይታወሳል።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ