የሩስያ ቅጥረኛ ወታደሮች በማሊ አማጺያን ብርቱ ጉዳት ደረሰባቸው
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 27 2016ዋግነር የተባለው የሩስያ ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ምዕራብ አፍሪቃዊቷ ማሊ ውስጥ ብርቱ ጉዳት እንደደደረሰበት ከሰሞኑ ተዘግቧል ። የቅጥረኛ ወታደር ቡድኑ ወደ ዐሥር የሚጠጉ ወታደሮች በቱዋሬግ አማጺያን ተገድለዋል አለያም ተማርከዋል ተብሏል ። ጉዳቱ የደረሰው የማሊ አማጺያን ቅንጅት በመፍጠር የማሊ ጦር ሠራዊትን ከብበው ጥቃት በሰነዘሩበት ወቅት ነው ተብሏል ። የማሊ ጦር ሠራዊት ጦሩ ተከብቦ ብርቱ ጉዳት እንደደረሰበት በሀገሪቱ ብሔራዊ ማሠራጪያ ጣቢያ በመግለጫ አስነብቧል ። መግለጫውንም የማሊ ራዲዮ እና ቴሌቪዥን ጽ/ቤት ጋዜጠኛ ካህዲዳቱ ኮኔ እንዲህ አንብባለች ።
«ሐሙስ ሐምሌ 18 የማሊ ጦር ሠራዊት ለመጀመሪያ ጊዜ በአሸባሪዎች ጥቃት ደርሶበታል ። የጦሩ ፈጣን ርምጃም አሸባሪዎች በፍጥነት እንዲሸሹ ከማድረጉም ባሻገር ጠላት ብርቱ የሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳት እንዲደርስበት አስችሏል ። የተዳከመው ጠላት እየሸሸ ነበር ። ከዚህ የአሸባሪዎች የመጀመሪያ ሙከራ በኋላ የአየር ንብረቱ ከፍተና አስተዋጽኦ አድርጓል ። ሌሊቱን የነበረው ኃይለኛ አሸዋ የቀላቀለ አውሎ ንፋስ አሸባሪዎች እና ተባባሪዎቻቸው ዳግም ኃይላቸውን እንዲያሰባስቡ እና በቀጣናው ካሉ አሸባሪ ድርጅቶች ሁሉ ድጋፍ አግኝተው እንዲደራጁ አስችሏቸዋል ።»
ከአልቃይዳ ጋ ግንኙነት እንዳለው የሚነገርለት ጃማአት ኑስራት ኧል-ኢስላም ዋል ሙስሊሚን (JNIM) የተባለው አሸባሪ ቡድን የማሊ ጦር ሠራዊት ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ዐሳውቋል ። ለሁለት ቀናት በተከታታይ ነበር በተባለው ብርቱ ውጊያ የማሊ ጦር መጠነ ሰፊ የሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳት እንደደረሰበት አልሸሸገም ።
«ዓርብ ሐምሌ 19 ውጊያው እጅግ ተጠናክሮ ቀጥሏል ። ታጣቂ አሸባሪዎቹ እስላማዊ መንግሥት በታላቁ ሠሃራ ከተሰኙት ጥቅመኛ ተባባሪዎቻቸው እና ከከአልቃይዳ ጋ ግንኙነት ካለው ጃማአት ኑስራት ኧል-ኢስላም ዋል ሙስሊሚን ጋ በመጣመር ጦራችን ላይ በርካታ ጥቃት ሰንዝረዋል ። በሳኅል አሸባሪ ቡድኖች ጥምረት የተከበበው የማሊ ጦር ሠራዊት ተጨማሪ ኃይል እስኪደርስለት ድረስ ብርቱ ተጋድሎ አድርጓል ። የወታደሮቻችን አብነት የሌለው ጀብድ በሰው እና በንብረት ላይ የደረሰውን ጥፋት መከላከል አልቻለም ።»
ከዚያም ባሻገር ታጣቂ ቡድኑ ከጦሩ ጋ አብረው ሲዋጉ የነበሩ ያላቸው የሩስያ ዋግነር ቅጥረኛ ወታደሮችን ደቡብ ቲንዛውቴኔ ውስጥ ማጥቃቱን ይፋ አድርጓል ። ለእስልምና አክራሪ የቱዋሬግ ቡድን አባላት የሩስያ ቅጥረኛ ወታደሮች ያሉበትን ሁኔታ መረጃ በማቀበል የስለላ ተግባር የፈጸመችው ዩክሬን መሆኗም ተገልጧል ። ድርጊቱ ሩስያ እና ዩክሬን በብዙ ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት ከውቅያኖስ ማዶ በአፍሪቃ ምድር የእጅ አዙር ፍልሚያ መጀመራቸውን ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ።
በማሊ ከጎርጎሪዮሱ 2020 ጀምሮ በመፈንቅለ መንግስት ሥልጣኑን የተቆጣጠረው ወታደራዊ ሁንታ ከምዕራባውያኑ ጋር የነበረውን ወታደራዊ ትብብር አቋርጧል ። በአካባቢው ሰፍረው የቆዩ የምዕራባውያን ወታደሮች ጦር ሰፈሮቻቸውን ለቅቀው ለመውጣት ከተገደዱ ቆይቷል ። የማሊ ወታደራዊ ሁንታ ከሩስያ ጋር አዲስ ትብብር መጀመሩም የሚታወስ ነው ።
ልፋተ-ዐልቦ ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
አዜብ ታደሰ