1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሳህል ሃገራት የጽንፈኞች ጥቃትና የሩስያ ፍላጎት

ረቡዕ፣ የካቲት 27 2016

አክራሪ ጽንፈኞች እና የሩሲያ ድብቅ ፍላጎት ከሰሃራ በታች ባሉ የሳህል አካባቢ አፍሪቃ ሀገራት ላይ ስጋት ደቅነዋል ሲሉ የጀርመን ልማት ሚኒስትር ስቬንያ ሹልዘ አስጠነቀቁ። ሚኒስትሯ ይህን የተናገሩት በያዝነዉ ሳምንት ሰኞ ለፖለቲካዊ ዉይይት ወደ ቡርኪናፋሶ እና ቤኒን ከማቅናታቸዉ በፊት ነዉ።

https://p.dw.com/p/4dDLi
በጎርጎረሳዉያኑ 2018 ዓም አንድ የጀርመን ወታደር በማሊ
በጎርጎረሳዉያኑ 2018 ዓም አንድ የጀርመን ወታደር በማሊ ምስል Adrian Wyld/The Canadian Press/picture alliance

የጀርመን የልማት ሚኒስትር በዋጋዱጉ ቆይታቸዉ የዶቼ ቬለ አካዳሚን ጎብኝተዋል

አክራሪ ጽንፈኞች እና የሩሲያ ድብቅ ፍላጎት ከሰሃራ በታች ባሉ የሳህል አካባቢ አፍሪቃ ሀገራት ላይ ስጋት ደቅነዋል ሲሉ የጀርመን ልማት ሚኒስትር ስቬንያ ሹልዘ አስጠነቀቁ። ሚኒስትሯ ይህን የተናገሩት በያዝነዉ ሳምንት ሰኞ ለፖለቲካዊ ዉይይት ወደ ቡርኪናፋሶ እና ቤኒን ከማቅናታቸዉ በፊት ነዉ። 

የጀርመን ልማት ሚኒስትር ስቬንያ ሹልዘ በጀርመን፣ በፈረንሳይ እና በአውሮጳ ህብረት የሳህል ግዛቶችን ለመደገፍ የተመሰረተው የሳህል ህብረት ሊቀመንበር ናቸው። ጀርመን ለለምዕራብ አፍሪቃዊያኑ ሃገራት ቡርኪናፋሶ እና ማሊ ትልቋ እና አራተኛዋ ለጋሽ አገር ናት። ቡርኪናፋሶ መፈንቅለ መንግሥት ከተካሄደ በኋላ በጎርጎረሳዉያኑ 2022 መስከረም ወር ላይ ወታደራዊዉ መኮንን ኢብራሂም ትራኦሬ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ አንድ የአዉሮጳ ባለስልጣን ቡርኪናፋሶን ሲጎበኝ የጀርመንዋ የልማት ሚኒስትር የመጀመሪያዋ ናቸዉ።

የሚኒስትሯ ማስጠንቀቂያ የተሰማዉ ቡርኪናፋሶ በተለይም በሰሜናዉ የሃገሪቱ ክፍል በአሸባሪዎች ጥቃት መመታትዋ በተሰማበት ወቅት ነው። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ብቻ በሰሜናዉ ቡርኪናፋሶ በተከሰተ ተከታታይ ጥቃት በትንሹ 170 ሰዎች ተገድለዋል። በዚሁ ሳምንት መጨረሻ ቤተ-ክርስትያን እና መስጂድ ላይ በደረሰ ሌላ ጥቃት 29 ሰዎች ተገድለዋል። ለጥቃቱ እስካሁን ኃላፊነት የወሰደ አካል የለም። የቡርኪና ፋሶ መዲና ዋጋዱጉ ነዋሪ ይህንኑ ይገልፃል።   

«አሁን ያለው ሁኔታ ቀላል አይደለም። በሳምንቱ መጨረሻ፣ በመላ አገሪቱ  በተመሳሳይ ጊዜ የተከሰቱ ጥቃቶች ነበሩ። አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም መስጊዶች ላይ ጥቃት ደርሷል። አሸባሪዎቹ  ጠንካራ መሆናቸውን ሊያሳዩን መጥተዉ ነበር። ግን ደካማዎች መሆናቸዉ ታይቷል። » 

የጀርመን የልማት ሚኒስትር በማሊ ጋዎ ሚኒሱማ ካምፕ
የጀርመን የልማት ሚኒስትር በማሊ ጋዎ ሚኒሱማ ካምፕምስል Mey Dudin/epd

በጀርመን የባይሮይት ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑ የቡርኪናፋሶ ተወላጅ ካማል ዶንኮ እንደሚሉት ከሆነ፣ በቡርኪናፋሶ ድህነት ወጣቶቹን ደስተኛ እንዳይሆኑ አድርጓል፤ በሕይወት ለመቆየትም አማራጭ መፍትሄዎችን እንዲፈልጉ ያስገድዷቸዋል። «በገጠር ድህነት፣ ስራ አጥነት እና ደስተኛ አለመሆን አለ። ይህ ከመንግስት እርምጃዎች እና ከግብርና ጋር በተለይ ደግሞ ከአኩሪ አተር ምርት ጋር የተያያዘ ነው።  ይህ ደግሞ ወጣቶቹን ወደ ጽንፈኝነት  ሊያመራ ይችላል።»

ወደ 23 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ያላት ወደብ አልባዋ ምዕራብ አፍሪቃዊትዋ ሃገር ቡርኪናፋሶ ለዓመታት በጽንፈኛ አሸባሪ ቡድኖች ጥቃት ሲደርስባት ኖራለች። ጥቃት አድራሾቹ ጽንፈኞች ወደ መዲናዋ ዋጋዱጉ እየተጠጉ መሆኑም እየተገለፀ ነዉ። ባለፈው ዓመት ብቻ በርካታ ሺህ ሰዎች ቡርኪናፋሶ ዉስጥ ተገድለዋል። ካማል ዶንኮ በቡርኪናፋሶ እና በቤኒን ሁኔታዉ እየተባባሰ መምጣቱን በተለይ ጸረ-ፈረንሣይ የሆኑ ስሜቶች  እንዳባባሱት ገልፀዋል።

በሳህል አካባቢ ሀገራት የሚታየዉ ጽንፈኝነት እና ሽብር
በሳህል አካባቢ ሀገራት የሚታየዉ ጽንፈኝነት እና ሽብር ምስል Java

«በክልሉ እየሆነ ያለውን እያየን ነዉ። ፀረ-ፈረንሳይ አመለካከቶች እየጨመሩ መጥተዋል። ይህ ከኒዮ-ፓን አፍሪካኒዝም ሃሳብ ጋር አብሮ ይሄዳል። በድንበር ክልሎች ያሉ ወጣቶች ሌላ ቦታ የሆነውን ነገር ማድረግ ይፈልጋሉ። ወጣቶቹ ብሩህ ጭንቅላት ያላቸዉ እና ጎረቤቶቻችን የሚያደርጉትን ሁሉ ማድረግ እንችላለን የሚሉ ወጣቶች ናቸው።» በቅርቡ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ተካሁዶ በወታደራዊ ኃይሎች እንደሚተዳደሩት ማሊ እና ኒጀር ሁሉ ቡርኪናፋሶም ወደ ሩሲያ እየተጠጋች ነው። ሦስቱም ሃገራት ቀድሞ  ወታደራዊ እርዳታ እና ፀረ-ሽብርተኝነት ድጋፍን ሲያገኙ ከነበሩት ከቀድሞዋ ቅኝ ገዣቸዉ ከነበረችዉ ከፈረንሳይ ርቀዋልወይም ፊታቸዉን አዙረዋል።  

 

አዜብ ታደሰ /ካትሪን ጌንዝለር

ነጋሽ መሐመድ