1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዓለም ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን የሚከላከል ቀን

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 23 2016

የተባበሩት መንግሥታት ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል በሚደረገው ትግል አንድም ልጅ ከጀርባ እንዳይተው በሚል ሀሳብ በዛሬው ዕለት ይህንን አክብሯል። የዘንድሮው የዓለም አቀፍ የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን የመከላከል ቀን በተለይ የሕፃናትን ያልተገባ ዝውውር ለማስቆም የተፋጠነ ርምጃ እንዲወሰድ የሚጠየቅበት ነው።

https://p.dw.com/p/4ivBJ
Bangladesch I Hoffnung für Klimaflüchtlinge
ምስል Zakir Hossain Chowdhury/AA/picture alliance

ያልተገባ የሰዎች ዝውውርን ለማስቆም የተፋጠነ ርምጃ ያሻል

የተባበሩት መንግሥታት ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል በሚደረገው ትግል አንድም ልጅ ከጀርባ እንዳይተው በሚል ሀሳብ በዛሬው ዕለት ይህንን አክብሯል። የዘንድሮው የዓለም አቀፍ የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን የመከላከል ቀን በተለይ የሕፃናትን ያልተገባ ዝውውር ለማስቆም የተፋጠነ ርምጃ እንዲወሰድ የሚጠየቅበት ነው።

"በአለም አቀፍ ደረጃ በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ ከሆኑት 3 ሰዎች አንዱ ሕፃን ነው" ያሉት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ "የኢትዮጵያ መንግሥት የሕፃናትን ሕገ-ወጥ ዝውውር ለማስቆም ርምጃውን እንዲያፋጥን ጥሪ አቅርበዋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ምርምር የሚያደርጉ አንድ ባለሙያ በበኩላቸው፣ በተለይ  በኢትዮጵያ እና አካባቢው ያለው ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል "ለመቆጣጠርም ሆነ ለመከላከል አዳጋች ሆኗል" ብለዋል።

ፎቶ ከማኅደር፦ ወይዘሮ ራኬብ መሰለ፤ በስተግራ ቀና ብለው የሚታዩት
ፎቶ ከማኅደር፦ ወይዘሮ ራኬብ መሰለ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ምክትል ኮሚሽነር የዛሬ ሁለት ዓመት መግለጫ ሲሰጡምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የሕገ- ወጥ የሰዎች ዝውውር ፈተናዎች

በየአካባቢው በሚከሰቱ ተደራራቢ ቀውሶች ምክንያት ሕፃናት ለሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ተጋላጭነታቸው እየጨመረ እንደሚሄድና በዚህ ዙሪያ በተሰማሩ አደገኛ ሰው አጥማጆች መረብ ውስጥ እንደሚወድቁ የተባበሩት መንግሥታት አስታውቋል።

ሕፃናት በዚህ መነሻ በግዳጅ ለጉልበት ብዝበዛ፣ ለልመና እንዲሰማሩ አልያም በታጣቂ ኃይሎች ምልመላ ውስጥ በግዳጅ እንዲወድቁ፣ ለጾታዊ ጥቃትና ለሌሎችም ብዝበዛዎች እንዲጋለጡ ይሆናል።

ሕፃናትና ሴቶች በዋናነት የዚህ ሰለባ ይሁኑ እንጂ፣ ወጣቶችም ቢሆን ነገር ለተሻለ በሚል ዛሬን በመከራና ሥቃይ የበረሃ ሲሳይ፣ የባሕር እራት እየሆኑ በወጡበት ወድቆ መቅረት የግዴታ ዕጣቸው ሲሆን በየጊዜው ተስተውሏል።

ከብዙ ውጣውረድ በኋላ  በድንበር ጠባቂዎች እየተያዙ ወደመጡበት ሀገር የሚመለሱ የመኖራቸውን ያህል በመተላለፊያ እና መዳረሻ ሀገራት ውስጥ የሚደርስባቸው ፈተናም አሰቃቂ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ የሚመራመሩት ዶክተር ግርማቸው አዱኛም ይህንኑ ያረጋግጣሉ።

መደበኛ በሆነ ሁናቴ የወጡ ባለመሆኑ ባለፉት አሥር ዓመታት ብቻ 900 ሺህ ያህል ኢትዮጵያውያን ከሳዉዲ አረቢያ ብቻ ተመልሰዋል የሚሉት ባለሙያው፣ ችግሩ "ለመቆጣጠርም ሆነ ለመከላከል አዳጋች ሆኗል"ም ይላሉ።

ድህነት ፣ ሥራ አጥነት፣ የማኅበራዊ መገናኛዎች አሳሳች የመረጃ ስርጭቶች፣ ችግሩን እያሰፉ ውስብስብም እያደረጉት "ከመንግሥትም አቅም በላይ እየሄደ ያለ" ሆኗል ሲሉም ባለሙያው አብራርተዋል።

የሕገወጥ ሰዎች አዘዋዋሪዎች መረብ ሰንሰለቱ ድንበር ተሻጋሪ ነው
የሕገወጥ ሰዎች አዘዋዋሪዎች መረብ ሰንሰለቱ ድንበር ተሻጋሪ ነውምስል Reuters/Bangladesh Coast Guard

ሕገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች  በእነዚህ የተሻለ ኑሮ ፈላጊ ሰዎች ላይ የሚያደርጉት አደገኛ ቁጥጥር፣ ማስገደድ፣ ማታለል እና ዛቻ ከመንግሥታት ቁርጠኝነት ማነስ ጋር ተዳምሮ የየሀገራት ባለሥልጣናት ጣልቃ እንዳይገቡና እርምት እንዳያደርጉ አስቸጋሪ ሁኔታን ይፈጥርባቸዋል። "መረቡ፣ ሰንሰለቱ ድንበር ተሻጋሪ ነው።

የሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መነሻም፣ መተላለፊያም የሆነቸው ኢትዮጵያ ብዙ ዜጎቿ የዚህ ሰላባ መሆናቸውን በቅርቡ ከሳውዲ አረቢያ እሥር ቤቶች በመንግሥት ድጋፍ ወጥቶ ሀገሩ የገባው ወጣት ይመሰክራል።

"በዓለም አቀፍ ደረጃ በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ ከሆኑት 3 ሰዎች አንዱ ሕፃን ነው" ያሉት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ "የኢትዮጵያ መንግሥት የሕፃናትን ሕገ-ወጥ ዝውውር ለማስቆም ርምጃውን እንዲያፋጥን ጥሪ አቅርበዋል።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ