1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስደተኞች አበሳ በሊብያ

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 6 2016

ናይጄሪያዊው ስደተኛ ማይክል ሺራ "የምፈልገው ነገር ቢኖር አውሮፓ መድረስ ነው ፤ የተረጋጋ ሕይወት ማግኘት እንደምችል አምናለሁ፤ ይሁን እንጂ ከፊቴ ያለው መንገድ ረጅምና አደገኛ ነው ፤ ወደፊትም ቢሆን አደጋዎችን መቋቋም እችል እንደሆነ አላውቅም ።" በማለት ስጋቱን ገልጿል።

https://p.dw.com/p/4iFQb
አፍሪካውያን ስደተኞች
አፍሪካውያን ስደተኞችምስል picture-alliance/AP/Libyan Coast Guard

ኢትዮጵያና ኤርትራን ጨምሮ ከተለያዩ የአፍሪካ ሐገራት በሊብያ በኩል ወደ አውሮፓ ለመሻገር የሚሞክሩ ስደተኞች በበረሃ በውሃጥምና ረሃብ እንዲሁም በጉዞ ድካም ሰውነታቸው ዝሎ ለሕልፈት የሚዳረጉ በርካቶች ሆነዋል። በረሃውን እንደምንም አቋርጠው ሊብያ የደረሱትም በሃገሪቱ በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች፣ ሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎችና ደላሎች በርካታ ግድያና የሰብአዊ መብት ረገጣዎች እንደሚደርስባቸው መረጃዎች ያመላክታሉ።
ዶይቼቨለ የእንግሊዝኛው ክፍል ያነጋገራቸው ስደተኞች በመንግስት ወታደሮች ጭምር ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደሚደርስባቸው ያስረዳሉ።
ናይጀሪያዊው የ19 ዓመቱ ሚኪኤል ሺራ ወደ አውሮጳ ለመጓዝ የሚያስችለውን ገንዘብ ለማጠራቀም በሊብያ ሥራ ሲያፈላልግ ነበር። ይሁንና የመንግስት ወታደሮች በየጊዚው አፍሪካውያኑ ስደተኞችን እያፈሰ እንደሚያስር ለዶይቼቨለ ተናግሯል። እሱ በቅርቡ ከተካሄደ አፈሳ ለጊዜው ቢያመልጥም በስጋት የተሞላ ሕይወት እንደሚገፋ ተናግሯል።

በአነስተኛ ጀልባ ጉዞ ወደ አውሮጳ
በአነስተኛ ጀልባ ጉዞ ወደ አውሮጳምስል Johan Ben Azzouz/Photopqr/Voix du Nord/MAXPPP/dpa/picture alliance


በስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ቲም ኢቶን ከዶይቼቨለ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተከታዩን ብለዋል።

"በአንዳንድ መንገዶች ሰዎች ሊቢያን አቋርጠው ለመጓዝ እንዲቸገሩ የሚያደርጓቸው ነገሮችም አሉ ። ምክንያቱም ግጭት ፣ ሕግና ሥርዓት አለመኖሩ፤ ሕገ ወጥ ንግድ የሚሳተፉ ሰዎች እንዲበለጽጉ ከፍተኛ ዕድል ፈጥሯል። ይህ ንግድ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ያካትታል። ከዚህ ሕገወጥ ንግድ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ይገኛል ።
ስለዚህ ከ2011 ጀምሮ በሊቢያ ውስጥ በተቀሰቀሰው ግጭት ሳቢያ ወደ አውሮፓ ለመሻገር ሲሉ በሊቢያ አድርገው የሚጓዙ ስደተኞች ቁጥር በእጅጉ ጨምሯል ።
እንደ እውነቱ ከሆነ በሊቢያ ውስጥ ሕግና ሥርዓት አለመኖሩና አብዛኛውን ጊዜ ከባለሥልጣናት ጋር በተወሳሰበ ሁኔታ መረቦችን የዘረጉ ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ሥራቸውን በቀላሉ እንዲያከናውኑ ረድቶአቸዋል። ይህ ማለት ደግሞ እነዚህ ዘዴዎች ቀጣይነት ያላቸው ናቸው ማለት ነው ።"

አፍሪካውያን ስደተኞች በሊብያ ድንበር
አፍሪካውያን ስደተኞች በሊብያ ድንበርምስል Yousef Murad/AP/picture alliance


የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ቃል አቀባይ ሊዛ ቴርሶል ድርጅታቸው በሊብያ በስደተኞችና ተገን ጠያቂዎች ላይ የሚፈጸመውን የሰብአዊ መብት ረገጣ እየተከታተለው እንደሆነና በቅርቡ የተገኙት በጅምላ የተገደሉ ስደተኞች መቃብሮችን ለመመርመር ፍላጎት እንዳለው ለዶይቼቨለ አስረድቷል።
የተመድ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር የሆኑት ቮልከር ቱርክ የሊቢያ ባለሥልጣናት በቅርቡ በሊቢያ-ቱኒዚያ ድንበር አካባቢ በተገኘ የጅምላ መቃብር ላይ ምርመራ እንዲያደርጉ፤ እንዲሁም በዚህ ዓመት መጋቢት ወር ላይ በሊቢያ አል-ጃህሪያ ሸለቆ ውስጥ ቢያንስ 65 አስከሬኖችን መገኘታቸውን ማወቅ እንደተቻለ በሚገልጸው ዘገባ ላይ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቀዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በስደተኞችና ተገን ጠያቂዎች ከሚደርሱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፤  ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ፣ ድብደባ ፣ የግዳጅ ሥራ ፣ ቅሚያ ፣እገታ፣ አስነዋሪ የሆኑ እስር ቤቶች መበራከትና የሰው ልጆች ሽያጭ ይገኙበታል ሲል ይፋ አድርጓል ። 
በሊብያ የስደተኞች የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ዴቪድ ያምቢዮ በሊብያ ስለሚገኙ ስደተኞች ተስፋና ስጋት እንዳላቸው አልሸሸጉም
"በአገሪቱ የሚገኙ ስደተኞች ሁኔታ የሚሻሻልበት አጋጣሚ እንደሚኖር ተስፋ አለኝ። ይሁን እንጂየአውሮፓ ሕብረት በሊብያ ያለው የፖለቲካ ምህዳሩን ፣ የግል ሚሊሻዎቹንና መንግሥታዊ አካላቱን መደለል እስካላቆመ ድረስ ይህ እውን ሊሆን አይችልም።"

ናይጄሪያዊው ስደተኛ  ማይክል ሺራ  "የምፈልገው ነገር ቢኖር አውሮፓ መድረስ ነው ፤ የተረጋጋ ሕይወት ማግኘት እንደምችል አምናለሁ፤ ይሁን እንጂ ከፊቴ ያለው መንገድ ረጅምና አደገኛ ነው ፤ ወደፊትም ቢሆን አደጋዎችን መቋቋም እችል እንደሆነ አላውቅም ።" በማለት ስጋቱን ገልጿል።

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

ፀሐይ ጫኔ