1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር የጦር መሳርያ ዝውውርን ለመቆጣጠር እየጣረ መሆኑን አስታወቀ

ሰኞ፣ ግንቦት 12 2016

የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር በስፋት እየታየ ነው ያለው ሕገወጥ የጦር መሳርያ ዝውውር ለመቆጣጠር ጥረት ላይ መሆኑ አስታወቀ። ከዚህ በተጨማሪ የጦርነቱ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ ጥረቶች መቀጠላቸውን የትግራይ ክልል ግዚያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/4g4na
የትግራይ ክልል ግዚያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ
የትግራይ ክልል ግዚያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ የጦር መሣሪያ ዝውውር ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ምስል Million Haileslassie/DW

የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር የጦር መሳርያ ዝውውርን ለመቆጣጠር እና ተፈናቃዮችን ለመመለስ እየጣረ መሆኑን አስታወቀ

በወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ ትላንት ለክልሉ አስተዳደር መገናኛ ብዙሐን ማብራርያ የሰጡት የትግራይ ክልል ግዚያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ፥ በተለይም የጦርነቱ ተፈናቃዮች ለማስመለስ ከፌደራል መንግስቱ ጋር የተደረሰው ስምምነት የእስካሁን አፈፃፀም እንዲሁም በስፋት እየታየ ነው ባሉት ሕገወጥ የጦር መሳርያ ዝውውር ዙርያ ማብራርያ ሰጥተዋል።

ጦርነቱ ተከትሎ በርካታ ሕገወጥ የጦር መሳርያ በተለያዩ ሐይሎች እና ግለሰቦች እጅ እንዳለ፣ ይህም ሕገወጥ ዝውውሩ እንዲበራከት እና የፀጥታ ስጋት እንዲሆን እንዳደረገው የሚገልፁት ጀነራል ታደሰ አሁን ላይ እየታየ ያለው ሕገወጥ የጣር መሳርያ ዝውውሩ፥ የተደራጀ፣ በከፍተኛ በጀት የሚመራ፣ 'ትግርኛ ተናጋሪዎች እና የአጎራባች ክልል' ያልዋቸው ሐይሎች ጭምር የሚሳተፉበት መሆኑ ተናግረዋል። ይህ ለመቆጣጠርም ጥረቶች ቀጥለዋል ብለዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥሪ በትግራይ

ከፌደራል መንግስት ጋር በተደረሰ ስምምነት እና የስራ አፈፃፀም የግዜ ሰሌዳ መሰረት እስከ ሰኔ 30 ድረስ የጦርነቱ ተፈናቃዮች የመመለስ ተግባር ለመፈፀም ታልሞ እየተሰራ መሆኑ ያነሱት ጀነራል ታደሰ ወረደ፥ ይሁንና የፌደራል የፀጥታ ሐይሎች እስካሁን የሚጠበቅባቸው ተግባር አለመወጣታቸው አንስተዋል።

በጦርነት  የተፈናቀሉ ዜጎች ትግራይ
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ተፈናቃዮችን ለመመለስ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ጄኔራል ታደሰ ወረደ ተናግረዋልምስል Million Haileselassie/DW

በትግራይ ያሉ የጦርነቱ ተፈናቃዮች ከክረምት በፊት ወደ ቀዬአቸው በመመለስ ለእርሻ ዝግጅት እንዲያደርጉ፣ ከቀጣይ ተመፅዋችነት እንዲገላገሉ በክልሉ አስተዳደር እና ፌደራል መንግስቱ ፍላጎት መኖሩም ጀነራሉ ጨምረው ገልፀዋል።

ትግራይ:- የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ሰላማዊ ህይወት የመመለስ እቅድ

ጀነራል ታደሰ ወረዳ ከሳምንታት በፊት ሰጥተውት በነበረ መግለጫ የራያ እና ፀለምቲ ተፈናቃዮች እስከ ግንቦት 30፣ የምዕራብ ትግራይ ተፈናቃዮች እስከ ሰኔ 30 ድረስ ለመመለስ መግባባት መደረሱ ተናግረው እንደነበር ይታወሳል።

ሚሊዮን ኃይለስላሴ

እሸቴ በቀለ