1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጨረር ህክምና

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 30 2016

በህብረተሰቡ ዘንድ በሽታው አይድንም ብሎ በማሰብ ቶሎ ወደ ህክምና ያለመምጣት፤ እንዲያም ሲል በሽታው ከአንዱ ወደ ሌላኛው ይዛመታል በሚል የግንዛቤ ችግር ምክንያት በተለይም የማህጸን በርና የጡት ካንሰር ታካሚዎች ባሎቻቸው ጥለዋቸው እንደሚሄዱ ዶክተር ሚካኤል ይገልጻሉ።

https://p.dw.com/p/4b1cI
Symbolbild Krebsvorsorge Krebs Diagnose Screening MRT
ምስል Rui Vieira/empics/picture alliance

የካንሰር የጨረር ህክምና

በኢትዮጵያ የተለያዩ ዓይነት የካንሰር በሽታዎች ቢኖሩም የጡት ካንሰር፤ የማህጸን በር ካንሰርናየከአንገት በላይ ወይም የአፍንጫና ሰርን አካባቢ ካንሰሮች ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ደረጃ እንደያዙ ጥናቶች ያመላክታሉ። በኢትዮጵያ በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2020 በተካሄደ ጥናት በየዓመቱ ወደ 77,000 የሚሁኑ ሰዎች በካንሰር በሽታ ይጠቃሉ። በየዓመቱ ደግሞ በዚሁ በሽታ ምክንያት ወደ 50,000 ሰዎች ይሞታሉ።


"ራድዮ ቴራፒ" ወይም የጨረር ሕክምና

የካንሰር በሽታ የተለያዩ ደረጃዎች ያሉት ሲሆን ህክምናውም የዚያኑ ያህል የተለያየ እንደሆነ በሐረማያ ዩኒቨርስቲ የሕይወት ፋና ሆስፒታል የካንስር ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ሚካኤል ሻውል ይገልጻሉ። በሽታው ከሚታከምባቸው ዘዴዎች አንዱ የጨረር ህክምና ወይም "ራድዮተራፒ" እንደሆነ ዶክተር ሚካኤል ይናገራሉ።

"ከካንሰር ህክምናዎች አንዱ የጨረር ሕክምና ነው። ቃሉ ይገልጸዋል ብለን አናምንም። "ራድዮተራፒ" ነው የሚባለው። ይህ ህክምና ከኬሚካል፤ ሆርሞንና ከሌሎች የህክምና አሰጣጦች ጋር በመሆን ለካንሰር ታማማሚዎች የሚሰጥ የሕክምና ዓይነት ነው።"
ለካንሰር ታማሚዎች የሚሰጠው "ራድዮተራፒ" ወይም በተለምዶ የጨረር ሕክምና ከፍተኛ መጠን ያለው ጨረርን ተጠቅሞ ካንሰር አምጪ ህዋሳትን በመግደል የሚሰጥ ሕክምና እንደሆነ ባለሙያው ያብራራሉ። 
"ለምሳሌ ለራጅና ለሲቲስካን  የሚሰጠው የጨረር መጠን በጣም አነስተኛ ሲሆን ለካንሰር የሚሰጠው የጨረር መጠን ግን ከነዚሁ ከ10 እስከ 20 እጥፍ ይሆናል። ለዚህ ህክምና በቀን እስከ 2 ሜጋ ቮልቴጅ የሚደርስ ጨረር በመስጠት ታካሚዎቻቸንን የምናክምበት ዘዴ ነው። የሚሰጠው የጨረር መጠን እና ጊዜ ግን እንደየበሽታው ደረጃ ይለያያል።"

3D Blue Virus Molecules
ምስል Zoia Fedorova/Zoonar/picture alliance


ካንሰር ሙሉ በሙሉ ሊድን ይችላል?

ካንሰርን ለማከም የጨረር ህክምናና የኬሚካል ህክምና በማጣመር እንደሚሰጥ የገለጹት ረዳት ፕሮፌሰር ሚካኤል፤ በሽታው ቀደም ብሎ ከታወቀና ገና ወደ መላ ሰውንነት ሳይዳረስ ህክምና ከተደረገለት ሙሉ ለሙሉ መዳን የሚችል መሆኑን ያስረዳሉ።

" የጨረር ህክምና በሽታው የተነሳበትን ቦታ ለመቆጣጠር ይጠቅመናል ማለት ነው። የኬሚካል ህክምና ደግሞ በደምሥር ከተሰጠ በኋላ ወደ መላው ሰውነት በመሄድ ሰውነታችን ውስጥ የተሰራጨውን የካንሰር በሽታ ይቆጣጠርልናል ማለት ነው። እና ህክምና ስንሰጥ ሁለቱንም ዘዴዎች አንድ ላይ ነው የምንሰጠው። ይህም ህክምና በሽታውን ሙሉ በሙሉ የመቆጣጠር እድል ይኖረዋል።"

የጎንዮሽ ጉዳት
"ራድዮተራፒ" ወይም የጨረር ህክምና የተለያዩየጎንዮሽ ጉዳቶች እንዳሉት የህክምና ባለሙያው ገልጸውልናል። ጉዳቶቹ ግን ከጥቅሙ አንጻር ሲመዘኑ ከባድ እንዳልሆኑ በማከል።

"ህክምናው ከሚያስከትላቸው የጎንዮሽ ጉዳቶች በተለይ ከኬሞተራፒ ጋር ከተሰጠ ማቅለሽለሽ፣ ድካም፣ የማስመለስ፣ ጨረሩ የተሰጠበት ቦታ የመቁሰል፣ የጡት ካንሰር በምናክምበት ጊዜ ጨረሩ የሳምባ ምች ሊያስከትል ይችላል። የልብ ህመምተኞች ላይ ደግሞ ጨረሩ ልብን ስለሚነካ የራሱ ጉዳት ይኖረዋል ማለት ነው።"


ያሉት ተግዳሮቶች
በካንሰር ሕክምና ላይ ከሚታዩት ተግዳሮቶች አንዱ ለዚህ ሕክምና የሚዎሉ ማሽኖች የዋጋ ውድነትና በመስኩ ያሉ ባለሙያዎች ቁጥር አናሳ መሆን ነው። በሐረማያ ዩኒቨርስቲ የሕይወት ፋና ሆስፒታል የካንስር ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ሚካኤል ሻውል በመስኩ የተደረጉ ጥናቶችን ዋቢ አድርገው እንደነገሩን በሃገሪቱ ያሉ ባለሙያዎች ቁችር ከ80 አይበልጡም። በመላ አገሪቱ የካንሰር ሕክምና የሚሰጥባቸው ማዕከላትም 3 ብቻ ናቸው፤ በሐረማያ ዩኒቨርስቲ ሥር በሚገኘው ሕይወት ፋና ሆስፒታል፣ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታልና በጅማ ዩኒቨርስቲ ብቻ ነው።
ሌላው የመስኩ ሕክምና ተግዳሮት በማሕበረሰቡ ላይ የሚታየው የግንዛቤ ችግር ነው። የሃገሪቱ ከፍተኛ የስልጣን ማማ ላይ የተቆናጠጡ ከፍተኛ ባለስልጣናት ሳይቀሩ የማይድን ለሚሉት የፖለቲካ ችግርን ለመግለጽ "ካንሰር" የሚል አገላለጽ መጠቀማቸው የበሽታው ተጠቂዎችን ስነአዕምሮአዊ የመዳን ተስፋ ከማጨለሙም በላይ ሕብረተሰቡ በሽታው አይድንም በሚል ዕምነት ቶሎ ወደ ሃኪም ቤት ሄዶ ህክምና እንዳያገኝ፤ ሌሎች አማራጮችን ፈልጎና ሞክሮ በሽታው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ ወደ ሕክምና ስለሚመጣ የመዳን ተስፋው እንዲቀጭጭ አሉታዊ ጫና እየፈጠረ እንደሆነ ረዳት ፕሮፌሰር ሚኪኤል ይገልጻሉ። 
በህብረተሰቡ ዘንድ በሽታው አይድንም ብሎ በማሰብ ቶሎ ወደ ህክምና ያለመምጣት እንዲያም ሲል  በሽታው ከአንዱ ወደ ሌላኛው ይዛመታል በሚል የግንዛቤ ችግር ምክንያት በተለይም የማህጸን በርና የጡት ካንሰር ታካሚዎች ባሎቻቸው ጥለዋቸው እንደሚሄዱ ዶክተር ሚካኤል ይገልጻሉ።

በሽታው በወቅቱ ከታከሙት ሙሉ በሙሉ ሊድን የሚችል መሆኑን የገለጹት ባለሙያው ተመርምሮ እራስን ማወቅ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ይመክራሉ። ችግሩ ሲያጋጥም ደግሞ በፍጥነት ወደህክምና መሄድ እንዳለብን በማከል።


 ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

ማንተጋፍቶት ስለሺ