1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስኢትዮጵያ

የጡት ካንሰርን የሚመረምር ዘመናዊ የጡት መያዣ ተሰራ

ረቡዕ፣ ኅዳር 12 2016

በአሜሪካው የማሳቹሴት የቴክኖሎጅ ተቋም የተሰራው ይህ የጡት ካንሰር ጠቋሚ ጡት መያዣ ካሜራዎች የተገጠሙለት እና ጡት ላይ የሚከሰት ዕጢን ከተለያዩ አቅጣጫዎች በቀላሉ ማየት የሚችል ነው። ጡት መያዣው ማግኔት የተገጠመለት በመሆኑም፤ መደበኛ ጡት መያዣ ላይ ያለባለሙያ ድጋፍ በቀላሉ በመለጠፍ መጠቀም የሚቻል መሆኑን ተመራማሪዎቹ ገልፀዋል።

https://p.dw.com/p/4ZHOC
የጡት ካንሰር ጠቋሚ ጡት መያዣ
በአሜሪካው የማሳቹሴት የቴክኖሎጅ ተቋም የተሰራው አዲሱ የጡት ካንሰር ጠቋሚ ጡት መያዣምስል Canan Dagdeviren/MIT

ካንሰርን ለመመመርመር የሚያገለግለው አዲሱ ጡት መያዣ

እንደ ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት መረጃ የጡት ካንሰር በገዳይነቱ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ የካንሰር ዓይነት ነው።በጎርጎሪያኑ 2020 ዓ/ም ብቻ በዓለም ላይ 2.3 ሚሊዮን ሴቶች በጡት ካንሰር ተይዘው 685 ሺህ የሚሆኑት ለሞት መዳረጋቸውን የድርጅቱ መረጃ ያሳያል።የጡት ካንሰር በአብዛኛው በሴቶች ላይ የሚከሰት ቢሆንም፤ ከ1 በመቶ በታች በወንዶችም ይከሰታል።
ይህ የካንሰር አይነት ስር ሳይሰድ ከታወቀ የመዳን ዕድሉ ከፍተኛ ቢሆንም በምርመራ ሳይታወቅ ከቆዬ ግን ለሞት የሚያበቃ በሽታ ነው።ይላሉ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለበርካታ አመታት ያገለገሉት እና  በአሁኑ ጊዜ በግላቸው የሚሰሩት የካንሰር ስፔሻሊስት ዶክተር ቦጋለ ሰለሞን።

ማሞግራም የጡት ካንሰርን ለመመርመር የሚያገለግል መሳሪያ ነው
የጡት ካንሰርን ለመመርመር የሚውለው የማሞግራፊ አገልግሎትምስል Monkey Business Images/Colourbox

የጡት ካንሰር በሽታን ለማወቅ ጥቅም ላይ ከሚውለው ዘዴ አንዱ ማሞግራም/Mammogram/ በተባለው መሳሪያ የሚደረግ ምርመራ ነው።ያም ሆኖ በአዳጊ ሀገራት የማሞግራፊ /Mammography/ አገልግሎት ተደራሽነት ውሱን በመሆኑ ሰዎች ለህክምና የሚመጡት ከፍተኛ ደረጃ ከደረሰ በኋላ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ። በኢትዮጵያም ሁኔታው ተመሳሳይ ዶክተር ቦጋለ ይገልፃሉ።ኢትዮጵያ ውስጥ የተበራከተው የጡት ካንሰር

የማሞግራፍ አገልግሎት ቢገኝ እንኳ በመደበኛ  የምርመራ ጊዜዎች መካከል ባለው ክፍተት የሚከሰቱ የጡት እጢዎችም ይኖራሉ። እነዚህ እጢዎች የጊዜ ክፍተት ካንሰር/interval cancers / በመባል የሚታወቁ ሲሆን፤ ከአጠቃላዩ የጡት ካንሰር በሽታ ከ20 እስከ 30 በመቶ ያለውን የሚይዙ ናቸው።እጢዎቹ በመደበኛ ምርመራ ወቅት ከሚገኙት የበለጠ አደገኛ መሆናቸውንም ባለሙያዎች ይገልጻሉ።በቅርቡ በአሜሪካው የማሳቹሴት የቴክኖሎጅ ተቋም  የተሰራው አዲስ የጡት ካንሰር መመረመሪያ መሳሪያ ግን፤ በማንኛውም ጊዜ እና ቦታ የካንሰር ዕጢዎችን በመለየት በሽታውን ስር ሳይሰድ ለማከም ተስፋ ፈንጥቋል።
አዲሱ የጡት ካንሰር ጠቋሚ መሳሪያ ካሜራዎች የተገጠሙለት እና  ጡት ላይ የሚከሰት ዕጢን ከተለያዩ አቅጣጫዎች በቀላሉ ማየት የሚችል ነው። ጡት መያዣው  የሚተጣጠፍ  እና አይነ በጎ በሚመስሉ ጥቃቅን ቀዳዳዎቹ ላይ ማግኔት የተገጠመለት በመሆኑም፤ መደበኛ ጡት መያዣ ላይ ያለባለሙያ ድጋፍ  በቀላሉ በመለጠፍ መጠቀም የሚቻል መሆኑን ተመራማሪዎቹ ገልፀዋል።
መሳሪያው መሽከርከር የሚችል በመሆኑም፤ ለምርመራ አመቺ በሆነ መልኩ ለማንቀሳቀስ  እና የጡት ህዋሳትን ከተለያየ አቅጣጫ ለመመርመር አመቺ መንገድ ፈጥሯል።

ጡት መያዣው ማግኔት የተገጠመለት በመሆኑም፤ መደበኛ ጡት መያዣ ላይ ያለባለሙያ ድጋፍ  በቀላሉ በመለጠፍ መጠቀም ይቻላል
አዲሱ የጡት ካንሰር ጠቋሚ መሳሪያ ካሜራዎች የተገጠሙለት እና ጡት ላይ የሚከሰት ዕጢን ከተለያዩ አቅጣጫዎች በቀላሉ ማየት የሚችል ነውምስል Canan Dagdeviren/MIT

ከአገልግሎት አንፃርም ከአንድ ጊዜ በላይ መጠቀም እንደሚቻል ተመራማሪዎቹ አመልክተዋል። ይህ ጡት መያዣ መሰል መሳሪያ በየስድስት ወሩ እና በየዓመቱ በሚደረጉ የማሞግራም (Mammogram)ምርመራዎች መሀል የካንሰር ዕጢዎች ቢከሰቱ በፍጥነት እና በጊዜ ለማግኘት ይጠቅማል።ከዚህ አኳያ አዲሱ መሳሪያ ዶክተር ሰለሞን እንደሚሉት የመዳን ዕድልን ለመጨመር  ትልቅ ርምጃ ነው። እቴጌ፤ ስለጡት ካንሰር መረጃ የሚሰጠው መተግበሪያ
ይህ ጡት መያዣ ዶ/ር ካናን ዳግዳቫይረን በተባሉ ቱርካዊ ሳይንቲስት በሚመሩት የጥናት ቡድን በአሜሪካ ማሳቹሴትስ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ((MIT) ቤተ ሙከራ የተሰራ ነው።
የዶ/ር ካናን ይህንን መሳሪያ የመሥራት ሀሳብ የተፀነሰውም የጡት ካንሰር ታማሚ አክስታቸውን ለማስታመም ሆስፒታል በነበሩበት ወቅት ነው።በኋላም በዚሁ በሽታ ሳቢያ የአክስታቸው ህይወት በማለፉ፤የፈለሰፉትን ጡት መያዣ ለአክስታቸው መታሰቢያ ማድረጋቸውን በተቋሙ ድረ ገፅ የሰፈረው መረጃ ያሳያል።
ተመራማሪዋ ምንም እንኳ አክስታቸውን ከሞት ባይታደጉም ሌሎች ሰዎችን ለመርዳት ለዚህ  መሳሪያ ግኝት ላደረጉት አስተዋፅኦ ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል። ከስድስት ዓመታት በላይ በወሰደው በዚህ  ምርምር  የጡት እጢ የህክምና ዳራ ካላቸው አንዲት የ71 አመት ሴት ላይ መሳሪያውን መሞከራቸውን እና  እስከ 0.3 ሴንቲ ሜትር  ዲያሜትር መጠን ያላቸውን የመጀመሪያ ደረጃ እጢዎችን መለየት መቻላቸውን አስረድተዋል። ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት መሳሪያው ከነባሩ አልትራሳውንድ ጋር ሲወዳደር የተሻለ የመፍትሄ አቅጣጫ እንዳገስገኘ እና በጡት ህዋስ ውስጥ  እስከ 8 ሴንቲሜትር ጥልቀት ዘልቆ  ምስል ማንሳት ይችላል።የጡት ካንሰርን አስቀድሞ በማወቅ መታከም

የጡት ካንሰር ምርመራ ውጤትን የሚያሳይ ምስል
የጡት ካንሰር ምርመራ ውጤትን የሚያሳይ ምስል ምስል Rui Vieira/empics/picture alliance

በአዲሱ መሳሪያ  በህክምና የምስል ማዕከላት ውስጥ ከሚጠቀሙት የአልትራሳውንድ መመርመሪያ ጋር የሚወዳደር ጥራት ያለው ምስል ማግኘታቸውንም ተመራማሪዎቹ አመልክተዋል።ከዚህ አኳያ ይህ ቴክኖሎጂ ይበልጥ አስተማማኝ፣ ምቹ እና ብዙም የሚያስፈራ የምርመራ ዘዴን በማቅረብ ቀደም ሲል የነበሩትን የጡት ካንሰር ምርመራ መሰናክሎች  ለማለፍ እንደሚጠቅም የተቋሙ ባልደረባ ካትሪን ሪካርዲ ገልፀዋል። 
ጡት መያዣው በአሁኑ ወቅት ለገበያ ያልቀረበ ቢሆንም፤በጡት ካንሰር  ምርመራ እጦት ለሞት የሚዳረጉ በተለይ የአዳጊ ሀገራት ሴቶችን ይታደጋል በሚል  በብዞዎች ዘንድ ተስፋ ተጥሎበታል። ይህ የሚሆነው ግን ችግሩ በጠናባቸው ሀገራት ተደራሽነቱ ከፍተኛ ከሆነ ነው ይላሉ ዶክተር ሰለሞን።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

 

ፀሀይ ጫኔ
ዮሀንስ ገብረእግዚአብሄር