1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮ ሶማሌላንድ ስምምነት፤ የኢትዮ ቴሌኮም ትርፍ፤ ያንዣበበዉ የረሃብ አደጋ

ዓርብ፣ ጥር 17 2016

አነጋጋሪነቱ የቀጠለዉ የኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የመግባቢያ ስምምነት፤ የኢትዮ ቴሌኮም ከፍተኛ ትርፍ ማግኘቱ፤ እንዲሁም በኢትዮጵያ ያንዣበበዉ ረሃብ በተሰኙ ርዕሶች ላይ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተሰጡ አስተያየቶች ተጠናቅረዉበታል።

https://p.dw.com/p/4bjaU
በርበራ ወደብ
በርበራ ወደብ ምስል Brian Inganga/AP/picture alliance

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

አነጋጋሪነቱ የቀጠለዉ የኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የመግባቢያ ስምምነት፤ የኢትዮ ቴሌኮም ከፍተኛ ትርፍ ማግኘቱ፤ እንዲሁም በኢትዮጵያ ያንዣበበዉ ረሃብ በተሰኙ ርዕሶች ላይ የተሰጡ አስተያየቶችን ተጠናቅረዉበታል። ኢትዮጵያ ራሷን የሶማሊላንድ ሪፐብሊክ ብላ ከምትጠራው እና ሶማሊያ የግዛቴ አካላ ናት ከምትላት ሶማሊላንድ ጋ የወደብ ጉዳይን በሚመለከት የተፈራረመችው የመግባቢያ ሰነድ አነጋጋሪነቱ ቀጥሏል።

ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪቃ ቀጣና «ያለመረጋጋት ሳይሆን የመረጋጋት መንስኤ ናት» ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  ለግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር  መግለጫ ምላሽ ሰጥቷል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ፦ አምበሳደር መለስ ዓለም፦ ግብጽ ኢትዮጵያን የአካባቢው አለመረጋጋት መንስኤ አድርጋ መክሰሷን «ቧልት» ብለውታል።  የአረብ ሊግ በዚሁ ጉዳይ የሰጠውን መግለጫም አምባሳደር መለስ፦ «ለአፍሪቃውያን ንቀት» ብለውታል ።  በግብጽና በአረብ ሊግ መካከል ያለውን ግንኙነት «የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ» ሲሉም አክለዋል ። ግብጽ በሶማሊያም ሆነ በጸጥታዋ ላይ ምንም አይነት የደህንነት ስጋት እንዲፈጠር አትፈቅድም ሲሉ ፕሬዝዳንት አብድል ፋታህ አል-ሲሲ መናገራቸዉ ይታወቃል። አልሲሲ ይህን የተናገሩት የሶማሊያውን ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድን ካይሮ ላይ ጋብዘዉ ከተወያዩ በኋላ ነበር።  

አቢቹ ኮ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ፤ ኢትዮጵያን ማንም ልያስቆም አይችልም። የግብጽ ድንፋታ ለሳምንት ነዉ ሲሉ አስተያየታቸዉን ጽፈዋል። እዮኤል ንጉሴ የተባሉ ሌላ አስተያየት ሰጭ በበኩላቸዉ፤ የሱማሌላንድነገርን በተመለከተ ለመሆኑ ሕጉ ምን ይላል? ይህንን ስምምነት ዓለም አቀፉ ደንብ ይፈቅድላታል? እስቲ ባለሞያ ቢያብራራልን ጥሩ ነዉ ሲሉ ጥያቄ አይነት አስተያየት ጽፈዋል። 

እሙሽ የዳዬዉ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፤ ተቃዉሞ ምን ያመጣል። እኛ ኢትዮጵያዉያን የበይ ተመልካች መሆን ሰልችቶናል። እኛም እንደማንኛዉም አገር የባህር በር ማግኘት አለብን። ከተቻለ በዲፕሎማሲ። ካልሆነ እኛ ተሰዉተን ለልጆቻችን ምቹ ሀገር ከማስረከብ የሚያስቆመን ያለ አይመስለኝም። ለዚህም ምስክሩ የህዳሴዉ ግድባችን ነዉ ሲሉ አስተያየታቸዉን ቋጭተዋል።

ሁሴን ካተሞ የተባሉ የፊስቡክ ተከታታይ፤ በግብጽ ላይ ወደብ አንጠይቅ እንጂ፤ አላህ አንድነቱን ይስጠን እንጂ፤ ኢትዮጵያ ጀግና ልጆች እና ጀግና ወታደሮች አሏት፤ የግብጽ መግለጫ ተራ ወሬ ነዉ፤ ደሞስ በጎረቤታችን ምን ያገባታል ሲሉ አስተያየታቸዉን ጽፈዋል።

አማን አወልም ተመሳሳይ አይነት አስተያየት ነዉ ያስቀመጡት። የግብጽ ጩኸት እዉነት ለሶማልያ ሳይሆን፤ በአባይ ግድብ ምክንያት፤ ጥቅሟን ለማስመለስ የምታደርገዉ መፍጨርጨር ነዉ። የግብፅ አቅም እኮ ይታወቃል። እንኳን ኢትዮጵያን ቀርቶ ስምንት ዓመት ሙሉ የየመን ሁቲ አማጽያንን ለአራት ሆነዉ ማንበርከክ አልቻሉም፤ ሲሉ ጽፈዋል።

ያሬድ አሰፋ ይመር የተባሉ አስተያየት ሰጭ በበኩላቸዉ፤ ኢትዮጵያ ወደብ መፈለጓ ሳይሆን፤ ለሱማሌላንድን እንደ አገር እውቅና እሰጣለሁ ማለቷ ነው ችግሩ። የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ለምን ሐሳቡን እንደሚገለባብጡት አይገባኝም ፤ሲሉ አስተያየት ጽፈዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ት ፍሬህይወት ታምሩ
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ት ፍሬህይወት ታምሩምስል Hanna Demissie/DW

ደግናቸዉ አንተነህ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ እንደሚሉት ደግሞ፤ የግብፅ ለኢትዮጵያ ጠላትነት እጅግ የቀነጨረ ነው። ለኛ ተኝታ አታውቅም ። ቀበሮ የበግ ላት ይወድቅልኛል ብላ በጉን እሰከ ቤቱ እንደ ተከተለችው ሁሉ፤ እኛ እርስ-በርስ በተናቆርን ቁጥር፤ ምኞቷ መናሩ የታወቀ ነው። ይህን ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያን ታሪክ መርሳት አጉል ጫወታ ነው ፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን ቋጭተዋል።

ነብዩ ሳሙኤል ፤ ለየት ያለ አስተያየት እና ጥያቄ ብጤ አስተያየት አስፈረዋል። ነብዩ ሳሙኤል እንደሚሉት፤ ዎገኖቼ በአገራችን ጉዳይ አንድ ብንሆን እንዴት በአማረብን ። እስኪ ደሞ እሱን እንሞክረው፤ እባካችሁ አንድ እንሁን ሲሉ አስተያየታቸዉን አብቅተዋል።

ኢትዮ ቴሌኬም በግማሽ ዓመት 42,9 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘቱን በዚህ ሳምንት አስታዉቋል። ድርጅቱ ዘንድሮ ያገኘው ገቢ ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ካስገባው በ8,86 ቢሊየን ብር እንደበለጠ ነዉ የተገለፀዉ ። ድርጅቱ እንዲህ ያለውን ትርፍ ማግኘት ያስቻለው ስልታዊ የዲጂታል ፈጠራዎችን እና የተሻሻለ የመሰረተ ልማት ማስፋፋት ሥራዎችን በማከናወኑ መሆኑን ነው ያመለከተው። ከፀጥታው ችግር  ባሻገር፦ በኔት ወርክ ላይ የሚደርሱ አደጋዎች የፋይበር ኮፐር ስርቆት እና መቆራረጥ፤ የግንባታ እቃ አቅርቦት እጥረት እንዲሁም የዋጋ ንረት የገበያ አለመረጋጋት  እና የኃይል  አቅርቦት መቆራርጥ  ተግዳሮቶች ቢሆኑም ቴሌኮም በዘንድሮው ዓመት አጋማሽ ያስገባው ገቢ ካለፈው ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ መሻሻል አሳይቷል ሲሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ ፍሬህይወት ታምሩ ገልፀዋል። ሚሚ ይሻዉ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ የቴሌኮም ተጠቃሚ ነኝ ፤ እስቲ ነጻ ልቀቁልን። ለዋና ስራ አስኪያጅዋ ንገሩልን ሲሉ ጽፈዋል።

ኤልሻዳይ እግዚአብሔር የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ፤ ሁሉም የኢትዮጵያ ተቋማቶች ካለፈው ዓመት ይሔን ያክል ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው ቢሉንም ለደሃዉ ግን መሬት ላይ ጠብ ያለለት ነገር የለም።  እና ትርፉ ለግል አስቤዛ ሆኖ እንደዉ ይጠየቅ፤ ሲሉ ጽፈዋል። መድህን አሃም የተባሉ ሌላዉ አስተያየት ሰጭ እንደሚሉት፤ እንዴ እንዴት አታተርፉ ስንሞላ እየወሰዳችሁብን ሲሉ አስተያየታቸዉን ቋጭተዋል።

በትግራይ በሚሊዮኖች ተርበዋል
በትግራይ በሚሊዮኖች ተርበዋልምስል Million Haileselassie Brhane/DW

አባይ በላይ የተባሉ ሌላ አስተያየት ሰጭ እንደሚሉት ደግሞ በየ ሰዓቱ ከማንኛውም ሞባይል ተጠቃሚ ያለ ባለቤቱ ፍቃድ ከ 1 ብር እስከ 2 ብር እየቆረጠ ለምን ትርፋማ አይሆንም? ለምሳሌ እኔ ምንም በማላውቀው ከስልኬ ላይ ብር ይጠፋኛል። እስኪ ምን ሁኖ ይሆን ብየ 100 ብር ሞላሁና ለአንድ ሳምንት ምንም ሳልደውል ስከታተል ሰነበትኩ። ልክ ሳምንት ሲሞላው 60 ብር ብቻ ነው የቀረኝ። ወደ ቴሌ ደውየ ምን እንደሆነና በአካልም ሄጀ ስጠይቅ ኖርማል ነው። ምንም ነገር የለም ተባልኩ ስለዚህ ትርፍ ሳይሆን ዘረፋ ነው የሚባለው ሲሉ አስተያየታቸዉን አብቅተዋል።

ትግራይ ክልል ረሐብ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን እና አስቸኳይ ርምጃ ካልተወሰደ የከፋ ጉዳት እንደሚከሰት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ አስታዉቀዋል። አቶ ጌታቸው በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (UNICEF) የምሥራቅ እና ደቡብ አፍሪቃ አካባቢ ኃላፊ ጋር ባደረጉት ውይይት በትግራይ ባለፉት አሥር ወራት የምግብ ርዳታ በመቋረጡ ምክንያት ያንዣበበውን አስከፊ ሰብአዊ እልቂት ለመቀልበስ አፋጣኝ ርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል ። በክልሉ የምግብ ርዳታው መቋረጡን በመቶ ሺህዎች ላይ የተበየነ «የሞት ቅጣት» ነው፤ ነዉ ያሉት።  ኦቻ፤ ከኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽንን አገኘሁት ባለው መረጃ መሰረት ከፍተኛ የድርቅ ተጎጂዎች ባሉበት አማራ ክልል 1.7 ሚሊዮን ነዋሪዎች እርዳታ ጠባቂ መሆናቸውን ገልጿል። በአማራ ክልል ድርቅ የተከሰተባቸው አካባቢዎች ሰሜን ጎንደር፣ ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ሸዋ እና ሰሜን ወሎ እንዲሁም የዋግ ኽምራ እና የኦሮሞ ብሔሰረብ አስተዳደር ዞኖች እንደሆኑ በመግለጫው ማሳወቁ ይታወሳል።  

አብዱልአህሚድ ሙሃመድ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ፤ የትግራይ ክልል አመራር ህዝቡን ለመታደግ በየቀኑ መግለጫ ይሰጣል። የአማራ ክልል አመራሮች ግን ዝም እንዳሉ ነዉ ሲሉ ጽፈዋል።

አሽራብ ታደገ የተባሉ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ፤ ትግራይ ክልል 4.5 ሚሊየን የሚጠጋ ሕዝብ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ድርቅ ምክንያት የሚላስ የሚቀመስ ምግብ የለዉም፤ ሰዎች ምግብ በማጣታቸዉ ለከፋ ረሀብ ተጋልጠዋል። ሰዎች በረሃብ እየሞቱ ነዉ፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን ጽፈዋል። ከተማ ጎንፋ የተባሉ የማኅበራዊ ዘዴዎች ተጠቃሚ “የምግብ ዋጋ መናር ህይወታችንን እየፈተነ ነው በከተማም የምንኖር ረሃብ ላይ ነን ሲሊ አስተያየት ጽፈዋል። የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች ባለፉት ሳምንታት የሰጡዋቸዉ አስተያየቶች ካለወትሮ ቀንሶ መታየቱ በተለያዩ ገጾች ተስተዉሎዋል። አስተያየቶቻችሁን አስቀምጡልን እያልን ዝግጅቱን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ