1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሕዳሴ ግድብ 19 ቢሊዮን ብር ማዋጣቱ ተነገረ

ዓርብ፣ መጋቢት 27 2016

የፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱን መረጃ መሰረት በማድረግ ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ እንደገለፁት ለግድቡ ግንባታ እስካሁን 193 ቢሊዮን ብር ወጪ ሆኗል፣ የግድቡ አፈፃፀም 95.8 ከመቶ መድረሱን የተናገሩት ወ/ሮ ፍቅርተ አንዳንድ ሚዲያዎች የግድቡ አጠቃላይ ግንባታ 99.8 ከመቶ ደርሷል ብለው የሚዘግቡት ስህተት ነው ብለዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4eT9o
የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ ከ2013 ጀምሮ የሐገሪቱ ሕዝብ ከ19 ቢሊዮን በላይ ብር አዋጥቷል
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምታስገነባዉ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ በከፊል (ፎቶ ከክምች ክፍላችን)ምስል Minasse Wondimu Hailu/AA/picture alliance

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሕዳሴ ግድብ 19 ቢሊዮን ብር ማዋጡን ተነገረ

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ይፋ ከተደረገበት ከመጋቢት 24/2003 ዓ ም ጀምሮ መላው ኢትዮጵያውን ግንባታውን በተለያዩ መንገዶች ሲደግፉት ቆይተዋል፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጰያውያን በቦንድ ግዥ፣ ቀጥታ ለግድቡ ግንባታ ገንዘብ በመስጠትና በተለያዩ መንገዶች አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡ህዝቡ ባለፉት 13 ዓመታት ያደረገው ድጋፍ ከፍተኛ እንደነበር የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎና ድጋፍ አሰባሳቢ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽ/ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ፍቅርተ ታምር ተናግረዋል፣ በአጠቃላይ ህዝቡ ለግድቡ ከ19 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ገልጠዋል፡፡
“... በጉልበት፣ በእውቀት፣ በሀሳብ፣ በቁሳቁስ ብዙ ድጋፍ ይደረጋል፣ በገንዘብ ደግሞ እስከ የካቲት 30/2016 ዓ ም ድረስ 19. 2 ቢሊዮን ብር ለግድቡ ግንባታ ከህብረተሰቡ ተሰብስቧል”  ብለዋል፡፡
አጠቃላይ ለግድቡ ስራ እስካሁን 193 ቢሊዮን ብር ወጪ መሆኑን ወ/ሮ ፍቅርተ ተናግረዋል፡፡ የሲቪል ግንባታው በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ  እንደሚጠናቀቅ ያመለከቱት ወ/ሮ ፍቅርተ የመካኒካል ሥራዎች ደግሞ በ2017 ይጠናቀቃሉ ተብሎ እቅድ መያዙን አስረድተዋል፡፡ ቀሪ ስራዎችን ለማጠናቀቅም ወደ 50 ቢሊዮን ብር ስፈልጋል ብለዋል፡፡
የፕሮጀክት ጽ/ቱን መረጃ መሰረት በማድረግ ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ እንደገለፁት ለግድቡ ግንባታ እስካሁን 193 ቢሊዮን ብር ወጪ ሆኗል፣ የግድቡ አፈፃፀም 95.8 ከመቶ መድረሱን የተናገሩት ወ/ሮ ፍቅርተ አንዳንድ ሚዲያዎች የግድቡ አጠቃላይ ግንባታ 99.8 ከመቶ ደርሷል ብለው የሚዘግቡት ስህተት ነው ብለዋል፡፡ እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ በእርግጥ የሲቪል ስራው 99.8 ከመቶ ቢደርስም የኤሌክተሮ ሜካኒክ ስራዎች ብዙ ስራ ይቀራቸዋል ነው ያሉት፡፡ ሲቪል ግንታው በዚህ ዓመት መጨረሻ እንደሚጠናቀቅ እቅድ መያዙን ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡ ቀሪ የኤሌክተሮ ሜካኒክ ስራዎች ግን በ2017 ዓ ም የሚጠናቀቁ ሲሆን አጠቃላይ ለቀሪ ስራዎች 50 በሊሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ለዶይቼ ቬሌ በስልክ አመልክተዋል፡፡
ሁሉም ክልሎች ለግድቡ ግንባታ አስተዋጽኦቸው ከፍተኛ እንደነበር  የተናገሩት ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ የድጋፉ መጠን እንደየ ክልሎቹ ጥንካሬና ቁርጠኝነት ይለያያል ብለዋል፣  ሁሉም ኢትዮጵያውያን ስላደረጉት ተሳትፎ ደግሞ ወ/ሮ ፍቅርተ አመስግነዋል፡፡
“አመራሩ ጠንክሮና በርትቶ በሚሰራባቸው ክልሎች አካባቢ የተሻለ ሀብት አሰባሰብ ያለበት ሁኔታ አለ፣ አንዳንዴ ደግሞ ወጣ ገባ የሚልበት ሁኔታ አለ፣ ህብረተሰቡ ግን ባለው አቅም ባለው ችሎታ ማንም ባይቀሰቅሰውም የድርሻውን ድጋፍ እደረገ ነው፣ ትንሽም ይሁን ትልቅ ለግድቡ ገንዘብ ያላዋጣ አለ ብለን አናሳብም መጠኑ ይደግም ይነስም፣ እስካሁን ስለተደረገው ነገር ኢትዮጵያውያንን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንንና የኢትዮጵያ ወዳጆችን በከፍተኛ ሁኔታ እናመሰግናለን፣ ለአገራችን አምባሳደር ሆነው ለሚነሱ የዲፕሎማሲ ጫናዎች ምላሽ በመስጠት የሚመጡ ተግዳሮቶችን እየመከተ እዚህ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ስላደረጉ ትልቅ ምስጋናና ክብር አለን  ”
የአማራ ክልል የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎና ድጋፍ አሰባሳቢ አስተባባሪ ምክር ቤት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ተናኘ አበበ ባለፉት 13 ዓመታት ከህብረተሰቡ ለግድቡ ድጋፍ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል ብለዋል፡፡
“የቦንድ ሽያጭ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ከመንግስት ሰራተኛው፣ ከባለሀብቱ፣ ከአርሶ አደሩ፣ ከነጋዴው፣ ከድርጅቶች፣ ከተለያዩ ተቋማት ከንግድ ባንክና ከልማት ባንክ ባገኘነው መረጃ መሰረት በአማራ ክልል እስከ የካቲት 30/2016 ዓ ም ድረስ 1 ቢሊዮን፣ 252 ሚሊዮን 571 ሺህ 79 ብር ሰብስበናል፡፡” ነው ያሉት፡፡
በጡረታ አበል የሚተዳደሩት የደብረማርቆስ ከተማ ነዋሪው አቶ ፋንታ መስተሳህል ላለፉት 13 ዓመታት አንድም ወር ሳሳልፉ በየወሩ የ1000 ብር ለግድቡ ቦንድ እየገዙ መሆኑን ነግረውናል፡፡
“ግንባታው ከተጀመረ ጀምሮ በየወሩ የአንድ፣ የአንድ ሺህ ብር ቦንድ እገዛለሁ፣ ባለፉት 13 ዓመታትም ከጡረታ አበሌ ከማገኛት እየቀነስኩ  እየቀነስኩ የ157 ሺህ ብር ቦንድ ገዝቻለሁ፣ እስከመጨረሻም እቀጥላለሁ”
ላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ በተባለ ስፋራ ላይ እየተገነባ ሲሆን ግንባታው ስራ ሲጀምር በአገሪቱ ያለውን የኃይል እጥረት በእጅጉ ይቀንሰዋል ተብሎ ይጠበቃል፣ በግንባታው መጨረሻ ምዕራፍ ላይ የሚገኘው ይህ ግድብ ሲጠናቀቅ  145 ሜትር ርዝመትና 1ሺህ 780 ሜትር ስፋት የሚኖረው ሲሆን ወደ 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሀ የማጠራቀም አቅም እንደሚኖረው መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ 13 የኃይል ማመንጫ ተርባይኖች የሚኖሩት ይህ ግድብ ከ5ሺህ ሜጋ ዋት በላይ ኃይል እንደሚያመነጭም ይጠበቃል፡፡
ዓለምነው መኮንን

በ2003 የተጀመረዉ የግድቡ ግንባታ እስከ 2017 ባለዉ ጊዜ ይጠናቀቃል ተብሎ ይገመታል (ፎቶ ከክምችታችን)
የኢትዮጵያ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ የኃይል መከታታያና መቆጣጠሪያ ማዕከል (ፎቶ ከክምችታችን)ምስል Minasse Wondimu Hailu/AA/picture alliance
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምታስገነባዉ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ በከፊል (ፎቶ ከክምችታችን)
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምታስገነባዉ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ በከፊል (ፎቶ ከክምችታችን)ምስል Minasse Wondimu Hailu/AA/picture alliance

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ