1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት የሥራ እንቅስቃሴ

ዓርብ፣ ሐምሌ 5 2016

ላለፉት 30 ዓመታት ከሀገር ለመውጣትም ይሁን ከውጭ ወደ ውስጥ ለመግባት "እግድ" ተጥሎባቸው የነበሩ የተባሉ 10 ሺህ ሰዎች ከእግድ ነፃ መደረጋቸውን የኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አስታወቀ። ሦስት የተቋሙ የበላይ ኃላፊዎች በሰጡት መግለጫ እነዚህ ከእግድ ነፃ የሆኑ ሰዎች ጉዳያቸው "በተረሳ ሁኔታ" ውስጥ የነበሩ ናቸው።

https://p.dw.com/p/4iDtG
ጋዜጣዊ መግለጫ
የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት የሥራ እንቅስቃሴ ጋዜጣዊ መግለጫ ምስል Solomon Muche/DW

የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት የሥራ እንቅስቃሴ

የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት የሥራ እንቅስቃሴ

ከ1986 ዓ .ም ጀምሮ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ከሀገር ለመውጣትም ይሁን ከውጭ ወደ ውስጥ ለመግባት "እግድ" ተጥሎባቸው የነበሩ የተባሉ አሥር ሺህ ሰዎች ከእግድ ነፃ መደረጋቸውን የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት አስታወቀ። ሦስት የተቋሙ የበላይ ኃላፊዎች ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ በሰጡት መግለጫ እነዚህ ከእግድ ነፃ የሆኑ ሰዎች ጉዳያቸው "በተረሳ ሁኔታ" ውስጥ የነበሩ ናቸው ተብሏል። 
የኢሚግሬሽን እና ዜግነት እገልግሎት "ዜግነት የማጣራት ሥራውን በልምድ የሚያከናውን፣ ውሳኔው ዜግነትን በሚያጣራው ግለሰብ መልካም ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ነው" በሚል የፌዴራል ዋና ኦዲተር በቅርቡ ለተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበውን የክዋኔ ኦዲት "ሥራው በልምድ አይሰራም" በማለት ውድቅ አድርጎታል። 18 ሺህ የውጭ ሀገር ዜጎች ሀሰተኛ ቪዛ እና የመኖሪያ ፈቃድ ይዘው በመገኘታቸው ወደመጡበት እንዲመለሱ ማድረግን ጨምሮ ሌሎች እርምጃዎች ስለመወሰዳቸው በመግለጫው ተጠቅሷል። 


እግድ የተነሳላቸው ዜጎች ጉዳይ 

ባለፈው ዓመት የ350 ሺህ ዜጎች የተከማቸ የፖስፖርት ፍላጎት ስለነበር ለሕክምና ወደ ውጭ መሄድ የነበረባቸው፣ የትምህርት እድል ያገኙ ወጣቶች፣ በውጭ ሀገር እየኖሩ ፓስፖርታቸው በጊዜው ያልታደሰላቸው ኢትዮጵያውያን ለከፋ ለችግር እና ምሬት ተጋልጠዋል። ከዚህ በመነሳት የአሰራር ለውጥ ማድረጉን ያስታወቀው የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ከዚህ አልፎ ለሰላሳ ዓመታት እግድ የነበረባቸውን ሰዎች ነፃ ማድረጋቸውን ዋና ዳይሬክተሯ ሰላማዊት ዳዊት እና ምክትላቸው ጎሳ ደምሴ ዛሬ ተናግረዋል።

ተቋሙ ዜግነትን የሚያጣራው በልምድ ነው የተባለው ላይ የተሰጠ ምላሽ


የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል ጊዜ ለዜጎች የፓስፖርት አገልግሎት ሳይሰጥ በመቆየቱ ዜጎች ለከፍተኛ እንግልት እና ሮሮ ተዳርገው መቆየታቸውን ያስታወሱት የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት በቀን ይታተም ከነበረበት 200 ፓስፖርት አሁን ይህንን ቁጥር ወደ 14 ሺህ ማሳደግ ስለመቻሉ አብራርተዋል።

የፌዴሬል ዋና ኦዲተር ኢሚግሬሽን በግለሰብ ስም የሒሳብ ቁጥር ከፍቶ ገቢ እንደሚሰበስብና፣ በዓመቱ ከሰበሰበው ውስጥ ያለ ስልጣኑ "ለትርፍ ሰዓት ክፍያ እና ለሠራተኞች ስጦታ" በሚል ማባከኑን በቅርቡ በሪፖርቱ ጠቅሶ ነበር።

ገንዘቡ በግለሰብ ሒሳብ ቁጥር ገባ የተባለው ሀሰት ነው ያሉት ወይዘሮ ሰላማዊት ሥራቸውን ለማዘመን እና የፓስፖርት አገልግሎትን በተፋጠነ ሁኔታ ለመስጠት ሲባል ሠራተኞች ከመደበኛ የሥራ ሰዓት ውጪ በመሥራት ላገለገሉበት ዋና ኦዲተር እንዳለው ለሰራተኞች የትርፍ ሰዓት ክፍያ መከፈሉን ገልፀዋል። ተቋሙ "ዜግነት የማጣራት ሥራውን በልምድ የሚያከናውን፣ ውሳኔው ዜግነትን በሚያጣራው ግለሰብ መልካም ፈቃድ ላይ የተመሠረተ" የሚለውን የዋና ኦዲተር አስተያየት ግን ሌላኛው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢቂላ መዝገቡ ውድቅ አድርገውታል።

ሰላማዊት ኃይሌ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር
ሰላማዊት ኃይሌ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተርምስል Solomon Muche/DW


"አሁን ላይ  ፓስፖርት ማግኘት ችግር አይደለም"
"አሁን ላይ  ፓስፖርት ማግኘት ችግር አይደለም" የሚለው የኢሚግሬሽን እና ዜግነትአገልግሎት ሰነድ አሟልቶ አለመቅረብ ለአገልግሎት መጓተትና ለብልሹ አሰራር በር የከፈተ መሆኑን ገልጿል።

በአሁኑ ወቅት ለአገልግሎቱ ጠያቂዎች ቀጠሮ ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ አዲስ ፓስፖርት ለመስጠት ሁለት ወራት፣ እድሳት ከቀጠሮ ጀምሮ በአንድ ወር ውስጥ መስጠት መቻሉንም አስታውቋል። በዓመቱ 1.1 ሚሊዮን ፓስፖርት መታተሙን ያስታወቀው የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ያም ሆኖ የሕዝቡ "ለቅሶ ቆሟል" ወደሚባል ደረጃ አለመደረሱን አቶ ጎሳ ደምሴ ተናግረዋል።


በቅርቡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያፀደቀውና ኢትዮጵያውያን ከሀገር እንዳይወጡ የማገድ ሥልጣንን ከፍርድ ቤት ለኢሚግሬሽን አገልግሎት የበላይ ኃላፊ የሚሰጠው ድንጋጌ የዜጎችን ሕገ መንግሥታዊ የመንቀሳቀስ መብት እንዳይገድብ እንዴት እንደሚተገበር ዋና ዳይሬክተሯን  ጠይቀን ምላሽ ሰጥተዋል።

ሕገ ወጥ ሰነድ ይዘው የተገኙት የውጭ ዜጌች ጉዳይ


ለ188 ሀገራት ለጉብኝት ለሚመጡ ሰዎች በሯ ክፍት የሆነው ኢትዮጵያ ባለፈው አንድ አመት 820 ሺህ የውጭ ዜጎች የቪዛ አገልግሎት ማግኘታቸው ተነግራል። ሆኖም በዚው ረገድ 18 ሺህ የውጭ ዜጎች አንድም ሀሰተኛ ቪዛ፣ በሌላ በኩል ሕገ ወጥ የመኖሪያ ፈቃድ ይዘው በመገኘታቸው እርምጃ እንደተወሰደባቸው ተነግሯል። ተቋሙ ከነሐሴ 1 ቀን 2016 ዓ .ጀምሮ የአገልግሎት ክፍያ ማሻሻያ እንደሚያደርግ አስታውቋል። ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ ለስብሰባ እና ለጉብኝት ለሚመጡ የውጭ ዜጎች የቪዛ አገልግሎት ክፍያ እንዲቀንስ መደረጉም በመግለጫው ተገልጿል።

 

ሰለሞን ሙጬ

አዜብ ታደሰ 

ፀሐይ ጫኔ