1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጀርመን ጥምር ዜግነት ለኢትዮጵያውያን ምን ፋይዳ አለው?

ቅዳሜ፣ መጋቢት 7 2016

የጀርመን መንግሥት ላዕላይ ምክር ቤት ወይንም ቡንደስታኅ ባለፈው ጥር 10 ቀን፣ 2016 ዓ.ም ጥምር ዜግነት አሰጣጥን በተመለከተ ያጸደቀው የተሻሻለው አዲስ ሕግ ተግባራዊ ሊሆን ጥቂት ወራት ይቀሩታል ። ለመሆኑ ከዚህ የጥምር ሕግ ዜግነት ተጠቃሚዎች እነማን ናቸው? ኢትዮጵያውያንስ?

https://p.dw.com/p/4dhq8
ጀርመን ለሚኖሩ የውጭ ዜጎች ጥምር ዜግነትን በተቀላጠፈ መንገድ ማስገኘት የሚያስችል ነው
አዲሱ የዜግነት ማሻሻያ ጀርመን ለሚኖሩ የውጭ ዜጎች ጥምር ዜግነትን በተቀላጠፈ መንገድ ማስገኘት የሚያስችል ነውምስል picture-alliance/blickwinkel/McPHOTO/C. Ohde

የጀርመን ጥምር ዜግነት ለኢትዮጵያውያን ምን ፋይዳ አለው?

የጀርመን መንግሥት ላዕላይ ምክር ቤት ወይንም ቡንደስታኅ ባለፈው ጥር 10 ቀን፣ 2016 ዓ.ም ጥምር ዜግነት አሰጣጥን በተመለከተ ያጸደቀው የተሻሻለው አዲስ ሕግ ተግባራዊ ሊሆን ጥቂት ወራት ይቀሩታል ። ለመሆኑ ከዚህ የጥምር ሕግ ዜግነት ተጠቃሚዎች እነማን ናቸው? ኢትዮጵያውያንስ?

ከሁለት ወራት ግድም በፊት በጀርመን ላዕላይ ምክር ቤት ወይንም ቡንደስታኅ የፀደቀው የተሻሻለ የዜግነት አሰጣጥ ሕግ ተግባራዊ ሊሆን ሦስት ወራት ብቻ ቀርተውታል ። ስለተሻሻለው የዜግነት ሕግ ጀርመን ውስጥ የተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ለተጠቃሚ ሠራተኞቻቸው ግንዛቤ በመስጠት ላይ ናቸው ።  ጀርመን የተማሩትና የሚሠሩት የምጣኔ ሀብትና የሥራ አስተዳደር ባለሞያው ዶ/ር ፀጋዬ ደግነህ የተሻሻለው የጀርመን ጥምር ዜግነት ስላካተታቸው ጥቅሞች ቀጣዩን ብለዋል ።

የጀርመን ጥምር ዜግነት 

«ዜግነት የጀርመን ሲወስዱ እንደ ቀድሞው የኢትዮጵያ ፓስፖርታችሁን አምጡ እና እና ወደ ኤምባሲ እንልክላችኋለን የሚባለው አይኖርም ማለት ነው የጀርመንን ብቻ መስጠት ነው የቀረው ግን የኢትዮጵያ ጉዳይ ነው የሚሆነው ማለት ነው »

ያ ማለት፦ ቀደም ሲል የጀርመን ዜግነት ለማግኘት የውጭ ሀገር ዜጋው የሀገሩን ዜግነት መመለስ የግድ ይጠበቅበት ነበር ። ያ አሁን ቀርቷል ። ሆኖም፦ ጀርመን ማንኛውም መስፈርቱን ለሚያሟላ እና በሀገሯ ለሚኖር የውጭ ዜጋ የሀገሩን ፓስፖርት እንደያዘ ጥምር ዜግነት የምትሰጠው በአመልካቹ ሃገርም ጥምር ዜግነት ተቀባይነት ካለ ብቻ ነው ። አለበለዚያ የተሻሻለው የጥምር ዜግነት ደንብ «ከንቱ ነው» ይላል የቤርሊን ወኪላችን ይልማ ኃይለሚካኤል ።

ምር ዜግነት የሚፈቅዱ ሃገራት የተሻሻለው የጀርመን ጥምር ዜግነት ሕግ ተጠቃሚ ናቸው
የተለያዩ ሃገራት ፓስፖርቶች ። ጥምር ዜግነት የሚፈቅዱ ሃገራት የተሻሻለው የጀርመን ጥምር ዜግነት ሕግ ተጠቃሚ ናቸውምስል Maksym Yemelyanov/Zoonar/picture alliance

«ብዙውን ጊዜ የሁለት ዜግነት ጉዳይ ሲነሳ ከዚህ ከጀርመን አንጻር ነው አሁን ያየነው እንጂ ሌላ ሀገር ያሉ ተወላጆች፦ ለምሳሌ የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ የኬንያ ይህንን መብት እቀበላለሁ፤ የእኔ ዜጎች ሁለቱንም ሊያገኙ ይችላሉ የሚለውን ነገር በሕገ መንግሥቱ አለያም በአሠራራቸው ውስጥ እስካልከተቱ ድረስ ከንቱ ነው »

የተሻሻለው የጥምር ዜግነት ሕግ ጀርመን ውስጥ የሚኖሩ የውጭ ዜጎች የጀርመን ዜግነት የሚያገኙበትን መንገድ ያቀላጥፋልም ተብሏል ። እስካሁን ድረስ የውጭ ዜጎች ለጀርመን ዜግነት ለማመልከት ማሟላት ከሚገቧቸው መስፈርቶች መካከል ጀርመን ውስጥ ስምንት ዓመታት መኖርም ግድ ይላቸው ነበር ።  በተሻሻለው ሕግ መሠረት ግን አምስት ዓመት መኖር በቂ ነው ። ያም ብቻ አይደለም ። ጀርመን ውስጥ ከማኅበረሰቡ ጋ በፍጥነት ለመዋሀድ ማስረጃ ለሚያቀርቡ ጀርመን ውስጥ ሦስት ዓመት ኖረውም ለዜግነት ማመልከት ይችላሉ ። ጀርመን የጥምር ዜግነት ማሻሻያ ያደረገችበትን ምክንያት ይልማ እንዲህ ያብራራል ።

«ዋናው ነገር ምንድን ነው? የሰው አእምሮን፤ እዚህ ጀርመን የተገኘውን ዝም ብሎ ከማባከን፤ እነሱን አቅፎ፤ እነሱን ይዞ መሄድ ነው ይኼ የዘር ጥያቄ፤ የደም ጥያቄ ወዘተ ወዘተ የሚለው ነገሩ የዞረበት እንደሆነ ለማሳየትም ጭምር ነው »

ኢትዮጵያን ጨምሮ በምስሉ ላይ የሚታዩ ጥቂት የቀፍሪቃ ሃገራት ጥምር ዜግነት አይፈቅዱም ።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በምስሉ ላይ የሚታዩ ጥቂት የቀፍሪቃ ሃገራት ጥምር ዜግነት አይፈቅዱም ። ይህ በ2016 የነበረውን የሚያሳይ ነው

ዶ/ር ፀጋዬ የጀርመን የጥምር ዜግነት ማሻሻያን በተመለከተ፦ እንደውም «እስከዛሬም ተኝተውበት የነበረ ጉዳይ ነው» ብለዋል ። የሕጉ ማሻሻያ የተደረገውም፦ የተማረ ኃይል በመሰብሰብ ኤኮኖሚያቸውን ለማቃናት፤ ብሎም ለጡረተኞች የሚከፍላቸውም ስለሚፈልጉ ይመስለኛል ሲሉም አክለዋል ። ይህን አጋጣሚም ኢትዮጵያ እንድትጠቀምበት ጥሪ አስተላልፈዋል ።

«ሦስት ሚሊዮን በላይ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ በውጭ ይኖራል እየተባለ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ገንዘብ ፈሰስ ወደ ኢትዮጵያ እየተላከ ባለበት ሰአት ይኼ በጣም ትንሹ መደረግ የሚገባው ነገር ይመስለኛል »

ኢትዮጵያ እንደ ጎረቤት ሃገራት ኬንያ እና ጅቡቲ የጥምር ዜግነትን ስለማትፈቅድ በጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የዚህ የተሻሻለው ጥምር ዜግነት ተጠቃሚ መሆን አልቻሉም ። ከጀርመን ሕዝብ 14 በመቶው ወይም ከ12 ሚሊዮን የሚበልጠው የጀርመን ዜግነት የለውም ። ከመካከላቸው ወደ 5.3 ሚሊዮኑ ቢያንስ ለዐሥር ዓመታት ጀርመን የኖሩ ናቸው ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረ-እግዚአብሔር