1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዩክሬንና መካከለኛው ምሥራቅ ላይ ያተኮረው የአውሮጳ ኅብረት ሚኒስትሮች ስብሰባ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 16 2016

የአውሮጳ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የአውሮጳውያኑን የበጋ ወቅት የመጀመሪያ ስብሰባቸውን ትናንት በብራስልስ አካሂደዋል። በዚህም ወቅት በበርካታ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች በተለይም በዩክሬንና የመካከለኛው ምሥራቅ አጀንዳዎች ላይ በመወያየት ውሳኔዎች አሳልፈዋል።

https://p.dw.com/p/4idfZ
የአውሮጳ ኅብረት ፓርላማ
የአውሮጳ ኅብረት ፓርላማ ምስል Philipp von Ditfurth/dpa/picture alliance

የአውሮጳ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ

ዩክሬንን በተመለከተው ውይይት የዩክሬኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ሚስተር ኩሌባ በአስረጅነት ተገኝተው፤ ሩሲያ አሁንም በሀገራቸው ላይ እየፈጸመችው ያለውን ጥቃትና እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለሚኒስትሮቹ ገልጸዋል። ሁሉም ሚኒስትሮች ሩሲያ በተለይ በሲቪሎች ላይ የምታደርሰውን ጥቃት ያወገዙ መሆኑን የስብሰባው መሪና የኅብረቱ የውጭ ጉዳይ ሀላፊ ጆሴፍ ቦርየል በጋዜጣዊ መገልጫቸው ወቅት አንስተዋል፤ « ሚኒስትሮቹ ሁሉም በሚባል ደረጃ ሩሲያ በሲቪሎች ላይ  በተለይ ደግሞ በኪየቭ የሕጻናት ሆስፒታል ላይ የፈጸመችውን የሚሳይል ጥቃት አውግዘዋል» በማለት ይህም ዩክሬን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አሁን የአየር መቃወሚያ መሳሪያ የሚያስፈልጋት መሆኑን ሚስትሮቹ እንዲገነዘቡ ያደረጋቸው መሆኑን አስታውቀዋል።

የሩሲያ- ዩክሬን ጦርነት የወራሪና ተወራሪ ጦርነት መሆኑን ማስረዳት ስለማስፈለጉ

በቅርቡ በስዊዘርላንድ የተክሄደው የዩክሬን የሰላም ጉባኤ ውጤትና ቀጣይነት ላይ ውይይት እንደተደረገና የስብሰባውን የጋራ መግለጫ ከተቀበሉት 90 አገሮች በተጨማሪ ሌሎቹንም በመድረስ፣ ጦርነቱ የወራሪና ተወራሪ መሆኑን ማስገንዘብ እንደሚያስፈልግ የታመንበት እንደሆነ ቦርየል አስረድተዋል።

የወቅቱ የኅብረቱ ፕሬዝደንት ሀንጋሪ መሪዎች ላይ የተነሳው ተውሞና የተወሰዱ እርምጃዎች

የወቅቱን የአውሮጳ ኅብረትንፕሬዝደንትነት የያዘችው የሀንጋሪ ጠቅላይ ሚኒስተር ቪክቶር ኦርባን በቅርቡ በኪየቭ፣ ሞስኮና ቤጂንግ ባካሄዱዋቸው ጉብኝቶች ያነሷቸው ሀስቦችና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸውም በመንግሥታት ድርጅት ያሰሙት ንግግር፤ የሩሲያን ወራሪነትና የዩክሬንን ተጠቂነት ያላወሱ በመሆናቸው፤ ከአንድ አባል አገር ሚኒስተር በቀር ሁሉም ሚኒስትሮች ሀንጋሪን አውግዘዋል ተብሏል። በዚህም ምክኒያት በሚቀጥለው ነሐሴ ወር በቡዳፔስት ሊካሄድ የነበረው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ በብራስልስ የሚካሄድ መሆኑ ተገልጿል። ቀደም ሲልም የአውሮጳ ኮሚሽን በዚሁ የጠቅላይ ሚኒስተር ኦርባን የሞስኮ ጉብኝት ምክኒያት በወሩ መጀመሪያ በቡዳፔስት በተካሄደ ስብሰባ ኮሚሽነሮቹን ባለመላክ ተቃውሞውን የገለጸ መሆኑ ታውቋል።

ጆሴፍ ቤርየልፎቶ ከማኅደር
ተሰናባቹ የአውሮጳ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ሀላፊ ጆሴፍ ቤርየልፎቶ ከማኅደርምስል Dursun Aydemir/Andalou/picture alliance

የከፋው የመካከለኛው ምሥራቅ ሁኔታና ያለው ተስፋ

ሚኒስትሮቹ  በመካከለኛው ምሥራቅ ላይ ያካሄዱት ውይይት፤ ሁኔታዎች ከመሻሻል ይልቅ የከፉ መሆናቸው በሰፈው የተወሳበት መሆኑን ነው ሚስተር ቦርየል የገለጹት። «ከአስር ወራትና ከ290 ቀናት በኋላም በጋዛ ጦርነቱ የቀጠለበትና አዳዲስ መፈናቀሎችም የሚታይበት ሁኔታ ነው ያለው። ዛሬ በጋዛ 17 ሺህ ወላጅ አልባ ሕጻናት ይገኛሉ» በማለትም የሁኔታውን አሳዛኘትና አስከፊነት ቦርየል አጽንዖት ስጥተው ተናገረዋል። በጋዛ ምንም ዓይነት ዓለም አቀፍ ሕግና የዓለም ፍርድቤት ውሳኔም ተግባራዊ እንደማይሆን፤ የሰብአዊ እርዳታንም በተገቢው ሁኔታ ለማድረስ እንደማይቻል ያነሱት ቦርየል፤ «አካባቢው ሁሉም ዓይነት ወንጀል የሚፈጸምበት የሜዲትራንያን መቅዲሹ ሆኗል» ብለዋል።  

በሌላ በኩል ግን የአውሮጳ የኢንቨስትመንት ባንክና የአውሮጳ ኮሚሽንም ለፍልስጤም አስተዳደር እርዳታ ሊሰጡ መሆናቸው መሰማቱ ተስፋ ሰጭ መሆኑን ጠቅሰዋል። ሆኖም ግን አሉ ቦርየል በመገለጫቸው  ማጠቃለያ፤ «ሆኖም ግን ሊደርስ የሚችለውን እልቂት ለማስቀረት መፍጠን ያስፈልጋል።»

 ጆሴፍ ቦርየል ላለፉት አምስት ዓመታት የያዙትን የኅብረቱን የውጭ ጉዳይ ሀላፊነት ከሳምንታት በፊት  ለተመረጡት ለቀድሞዋ የኢስቶኒያ ጠቅላይ ሚኒስተር ካያ ካላስ በቅርቡ ያስርክባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ገበያው ንጉሤ

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ