1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአቶ ልደቱ አያሌው አዲሱ ሰነድና የኢትዮጵያ ፖለቲካ

ቅዳሜ፣ ግንቦት 3 2016

ኢትዮጵያውያን ገጥሟቸዋል ካሉት የህልውና አደጋ ተርፈው ወደተሻለ ለውጥ መሸጋገር የሚችሉት ሁሉን አቀፍ የሆነ የሽግግር ሂደት በመጀመርነው ሲሉ ፖለቲከኛው አቶ ልደቱ አያሌው ገለጹ።

https://p.dw.com/p/4fk8o
Äthiopien Addis Abeba | Lidetu Ayalew, äthiopischer Politiker
ምስል privat

አቶ ልደቱ አያሌው ለኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ያቀረቡት ጥሪ

የአቶ ልደቱ አያሌው አዲሱ ሰነድና የውይይት መድረክ

 

ኢትዮጵያውያን ገጥሟቸዋል ካሉት የህልውና አደጋ ተርፈው ወደተሻለ ለውጥ መሸጋገር የሚችሉት ሁሉን አቀፍ የሆነ የሽግግር ሂደት በመጀመርነው ሲሉ ፖለቲከኛው አቶ ልደቱ አያሌው ገለጹ።

አቶ ልደቱ፣ለመገናኛ ብዙኃን በቅርቡ ባሰራጩት አዲስ የውይይት ሠነድ ላይ እንዳመለከቱት፣የሁሉም የፖለቲካ ኀይሎች የወቅቱ ቀዳሚና የመተባበሪያ የትግል ስልት፣ይኸው የሽግግር ሂደት አጀንዳ ሊሆን እንደሚገባ ነው።

አቶ ልደቱ፣" የችግራችን ምንጭ፣ ያለንበት ሁኔታና የመዳኛው መንገድ" በሚል ርዕስ ስር ያዘጋጁትን የመወያያ ሰነድ፣ሰሞኑን ዶይቸ ቨለን ጨምሮ ለተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን አሰራጭተዋል።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የሚታወቁት አቶ ልደቱ፣ መገናኛ ብዙኃኑ በራሳቸው ወይም እንግዳ በመጋበዝ በመነሻ ሰነዱ ላይ እንዲወያዩበት፣የፖለቲካ ሰዎች፣ምሁራንና ማኀበራዊ አንቂዎችም ግምገማና ትችት እንዲያቀርቡበት ይፈልጋሉ።

ልደቱ አያሌው በሕመም ሳቢያ ከፖለቲካ መገለላቸውን አስታወቁ

ለሀገሪቱ ዘላቂ መፍትሄ ይሆናሉ ያሏቸውን ዐሳቦች ባጋሩበት በዚሁ ሰነድ ላይ፣ የማጠቃለያ የውይይት መድረክ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ መሆናቸውንም አቶ ልደቱ ከዶይቸ ቨለ ጋር በነበራቸው ቆይታ አስታውቀዋል።

"የውይይቱ ሂደት፣ከዚህ ከብሄር ገደብ አልፎ ተገናኝተው የማያውቁ ሰዎች ተገናኝተው የማያውቁ ሚዲያዎችም አንደኛው ሌላኛው ቦታ እየሄደ፣ዐሳብ መለዋወጥ እንዲችሉ በመነሻነት የቀረበት ጽሑፍ ነው። ለመሻሻልና ለመታረም ክፍት ነው፣ እና በእዛ ላይ ውይይት እንዲያደርጉ ነው።"

ለሃገሪቱ የቀረበ ዘላቂ መፍትሔ

ኢትዮጵያ አሁን የምትገኝበትን ተጨባጭ ሁኔታ፣ባዘጋጁት ሰነድ በዝርዝር ያስቀመጡት አቶ ልደቱ፣ አገሪቱን ከጥፋት የሚታደግ ያሉት አዲስ የሽግግር ሂደት መጀመር እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ለዚህ ሂደትም፣ የፖለቲካ ድርጅቶችን በጭፍን ከማውገዝ እና ከማጥላላት አባዜ በመውጣት እንዲጠናከሩ ማገዝ ያስፈልጋል ብለዋል።

የአቶ ልደቱ የዋስትና መብት አከራከረ

" እንደዚህ በተበታተነ ሁኔታ፣ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የት ነው የሚደርሱት?ስለዚህ የሚቻል ነው ወደ አንድ እንኳን መምጣት ባይቻል ሁለት ሦስት ብሎክ ለምንድን ነው መፍጠር የማይቻለው የሚለውን ጉዳይ ለማጉላት ነው።"

"አደጋ ላይ ነን"

አሁን ለምን በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱም፣" አደጋ ላይ ነን። በማንኛውም ጊዜ ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ ወጥተው በጣም ከፍተኛ ጦርነት ነው ያለው፣ አብዛኛው የአገሪቱ ክፍል የጦርነቱ አካል ሆኗል።ስለዚህ አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት፣ በጦርነቱ ግፊትም በራሱ ችግር ቢፈራርስ ሀገሪቱን ይዞ ነው የሚጠፋው። ስለዚህ እንዲህ ዐይነት አደጋ ከመጣ እንዴት ነው እቺን ሃገር ማሻገር የሚቻለው? የሚለው የሽግግር ሂደት የማይቀር ነገር ነው፣አስፈላጊ ነገር ነው። መንግስት በራሱ ችግርም ቢፈርስ ተቃዋሚዎችም ታግለው ቢያሸንፉት፣ መደበኛ መንግስት ለማቋቋምና ወደ መደበኛ ሂደት ለመግባት የሽግግር  ጊዜ የማይታለፍ ነገር ነው።ስለዚህ ጥርት ያለ አቋም መያዝ ይጠበቅብናል።"

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የሥልጣን ውዝግብ 

ከውይይት መድረኩ ምን ይጠበቃል?

በቀድሞው የኢትዮጵያ ፓርላማ አባልነት እና በፖለቲካ ፓርቲ መሪነት፣ በአገሪቱ የፖለቲካ ሂደት በቀጥታ የተሳተፉት አቶ ልደቱ፣የ31 ዓመታት የትግል ተሞክሮዬን ተጠቅሜ አዘጋጀሁት ባሉት በዚሁ ሰነድ ላይ የሚደረገው የውይይት መድረክ፣ አንዳች ውጤት ያመጣል የሚል ተስፋ ስንቀዋል።

" እዛ ላይ ቢያንስ ቢያንስ ልንግባባቸው የምንችላቸውና በጣም መሰረታዊ ልዩነት ናቸው የምንላቸው ነገሮች ግልጽ ሆነው ይታያሉ።እና በርግጥም ከምንለያይበት በላይ በአብዛኛው ተቃዋሚ ጎራ ውስጥ ያለው ኀይል የሚስማማበት የጋራ የሚባል ጉዳይ የበለጠ ይሆናል የሚል እምነት አለ።"ብለዋል።

 ታሪኩ ኃይሉ 

ታምራት ዲንሳ