1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቀጠለው የመሬት ናዳ ሥጋት በደቡብ

ሰኞ፣ ነሐሴ 13 2016

በጎፋ ዞን ጎፋ ደንባ ወረዳ ውርጪ ላኢማ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑትካሰች ተስፋዬ እና በሀይሉ ዳሮታ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በቀበሌው መቶ ሜትር ርዝመት ያለው መሬት ተሰንጥቋል ብለዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4jdFE
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በተደጋጋሚ እየተከሰተ የሚገኘው የመሬት ናዳ አሁንም  የነዋሪዎችን አስግቷል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በተደጋጋሚ እየተከሰተ የሚገኘው የመሬት ናዳ አሁንም  የነዋሪዎችን አስግቷል።ምስል Privat

የቀጠለው የመሬት ናዳ ሥጋት በደቡብ


በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በተደጋጋሚ እየተከሰተ የሚገኘው የመሬት ናዳ አሁንም  የነዋሪዎችን ህይወት በሥጋት የተሞላ እንዲሆን አድርጎታል ፡፡ የመሬት ናዳው ባለፈው ሐምሌ ወር አጋማሽ በክልሉ ጎፋ ዞን ተከስቶ ከ240 በላይ ሰዎችን ለሞት ካበቃ ወዲህ በዎላይታና በጋሞ ዞኖችንም በተመሳሳይ አደጋ 15 ሰዎችን ሞተዋል፤ በርካቶችም ተፈናቅለዋል ፡፡  

በጎፋ ዞን ከንባ ጎፋ ወረዳውም ባለፉት ሦስት ቀናት በተለያዩ ቀበሌያት በደረሰ የመሬት ናዳ የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉን የወረዳው መንግሥት ኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ብርቱካን ጣሰው ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል ፡፡
የመሬት መሰንጠቅ
አሁን ላይ እየቀጠለ ከሚገኘው የዝናብ ሥርጭት ጋር ተያይዞ በከፍታ ቦታዎች ላይ የሚገኙ ነዋሪዎች ሥጋት ላይ መውደቃቸውን ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል  ፡፡ ካሰች ተስፋዬ እና በሀይሉ ዳሮታ በጎፋ ዞን ጎፋ ደንባ ወረዳ ውርጪ ላኢማ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። 

 ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በቀበሌው የመሬት መሰንጠቅ ማስተዋላቸውን የጠቀሱት ካሰች እና በሀይሉ “ በቀበሌው መቶ ሜትር ርዝመት ያለው መሬት ተሰንጥቋል ፡፡ ቦታው ከፍታማ በመሆኑ ዝናብ ከጣለ ሊናድ ይችላል የሚል ሥጋት አለ ፡፡ አካባቢውን የተመለከቱ የወረዳው አመራሮች ወደ ሌላ ሥፍራ እንደምንዛወር ነግረውናል “ ብለዋል ፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ጋንታ ገመአ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ጋንታ ገመአ ምስል Privat


ከሥጋት ቀጠናዎች የማስወጣት ሂደት
በክልሉ ከመሬት ናዳ ጋር ተያይዞ በአደጋው የተጠቁ ነዋሪዎችን መልሶ የመቋቋም ሥራዎች በመከናወን እንደሚገኝ የክልሉ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ጋንታ ገመአ ለጋዜጠኞች ገልጸዋል ፡፡የተጎዱትን ከመደገፍ ጎን ለጎን በሺህዎች የሚቆጠሩ አባወራዎችን የአደጋ ተጋላጭ ከሆኑ አካባቢዎች ወደ ሌላ ሥፍራ ማዛወር  መጀመሩን የተናገሩት ኮሚሽነሩ ‘’ ነዋሪዎችን ከሥጋት ቀጠና የማውጣቱ ሥራ እየተከናወነ የሚገኘው በክልሉ የአደጋ ሥጋት ምክር ቤት በወጣው ዕቅድ መሠረት ነው ፡፡ ነዋሪዎቹ የሚወጡባቸው አካባቢዎች ቀይ ዞን በሚል በባለሙያዎች ቡድን አማካኝነት በጥናት ተለይተዋል “ ብለዋል ፡፡
የጥንቃቄ መልዕክቶች

በኢትዮጵያ ባለፍው የሰኔ እና የሐምሌ ወራት አስቀድሞ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ ሲጥልባቸው በነበሩ የደቡብ እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ፣ የኦሮሚያ ፣  የሲዳማ  እና የአማራ ክልሎች  የመሬት መንሸራተት አደጋ ሊያጋጥም እንደሚችል የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ተቋም አስታውቋል ፡፡ በእነኝህ አካባቢዎች እስከ መጪው መስከረም ወራት ከመደበኛ በላይ ዝናብ ስለሚኖር ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲደረግ ተቋሙ ማሳሰቡ ይታወቃል ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ኂሩት መለሰ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር