1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሱዳን ጦርነት መዘዝ ለኢትዮጵያዉያን ስደተኞች

ረቡዕ፣ መስከረም 30 2016

ከምዕራብ ትግራይ ተፈናቅለው በሱዳን መጠልያዎች ያሉ ስደተኞች መንግስት፣ እርዳታ ሰጪ ተቋማት እና ሌሎች እንዲደርሱላቸው በቅርቡ ከሱዳን የተመለሱት ያነጋገርናቸው ተፈናቃዮች ጥሪ ያቀርባሉ።

https://p.dw.com/p/4XPpM
ማፋዛ፣ ሱዳን መጠለያ ጣቢያ የደረሱ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች
የትግራዩን ጦርነት ሸሽተዉ ሱዳን ከገቡ ስደተኞች በከፊልምስል Ashraf Shazly/AFP

ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች በችግር እየተሰቃዩ ነዉ

             

የሱዳን ተፋላሚ ኃይላት የገጠሙት ጦርነት እዚያዉ ሱዳን ዉስጥ የሚኖሩና የተጠለሉ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞችን ለከፋ ችግር ማጋለጡ አሁንም እየተነገረ ነዉ።ሱዳን ዉስጥ በይፋ የተመዘገቡ ከ73 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች ተጠልለዋል።አብዛኞቹ በትግራይ ጦርነት ወቅት ከምዕራብ ትግራይ የተሰደዱ ናቸዉ።ከስደተኞቹ አንዳዶቹ እንዳሉት የሱዳኑ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲሕ በርካታ ስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎቻቸዉን እየጣሉ ወደተለያዩ አካባቢዎች እየተበተኑ ነዉ።

የ65 ዓመቱ አዛውንት አቦይ ገብረጨርቆስ ገብሩ ላለፉት ሶስት ዓመታት ኑሮአቸው በሱዳን መጠልያ ጣብያዎች ያደረጉ ኢትዮጵያዊ ስደተኛ ናቸው። እንደ ልጆቻቸው አጠራር አቦይ ገብረጨርቆስ ሀገራቸው፣ ቤተሰባቸው፣ ቀዬአቸው ጥለው ወደ ሱዳን የተሰደዱት ወደው አልያም የተሻለ ኑሮ ሽተው ሳይሆን፥ የዛሬ ሶስት ዓመት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተቀሰቀሰው ጦርነት ተከትሎ በተፈጠረ ሁኔታ ምክንያት መሆኑ አጫውተውናል። ከጦርነቱ በፊት እስከተሰደዱበት ግዜ ድረስ በትግራይ ምዕራባዊ ዞን ማይካድራ ከተማ ከመላ ቤተሰባቸው ጋር ይኖሩ እንደነበሩ የሚገልፁት እኝህ አዛውንት፥ በ2013 ዓመተምህረት መጀመርያ ጦርነቱ ሲቀሰቀስ፥ በተለይም በአካባቢያቸው የነበረ አስጊ ሁኔታ በመሸሽ፥ ቤት ንብረታቸው ጥለው እሳቸው ወደ ሱዳን ባለቤታቸውና ልጆቻቸው ወደ ሌላው የትግራይ ክፍል መበታተናቸው ይናገራሉ። በሱዳን ሓምዳይት እና ተነድባ የተባሉ የስደተኛ መጠልያ ጣብያዎች ከባድ የጭንቅ ግዜያት ለሶስት ዓመታት ያሳለፉት እኝህ አዛውንት፥ ከጦርነቱ ፍፃሜ በኃላ ተስፋ ያደረጉት ወደ ቀድሞ ቀዬአቸው መመለስ እና ከቤተሰቦቸው ጋር መገናኘት እስካሁን እውን ባለመሆኑ እንዲሁም በሱዳን የተቀሰቀሰው ጦርነት አሳስቧቸው፥ በራሳቸው ውሳኔ፥ ጦርነት ሽሽት ያቋረጡት የኢትዮ ሱዳን ድንበር ዳግም አቋርጠው፣ አደገኛ ያሉት ረዥም ጉዞ በማድረግ በቅርቡ መቐለ የተፈናቃዮች ካምፕ ወደሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ተቀላቅለዋል። 

ከኢትዮጵያ ተሰደዉ ራቁባ መጠለያ ጣቢያ የገቡ ስደተኞች
ከሰሜን ኢትዮጵያ ክልል ትግራይ የተፈናቀሉ ስደተተኞች ምስል Hussein Ery/AFP

እኝህ በደረሱበት ሁሉ ጦርነት እየተከፈተላቸው፣ ከአንድ ወደሌላ ሀገር፣ ከአንድ ወደ ሌላ መጠልያ መንከራተት የሶስት ዓመት ኑሮአቸው የሆነው አዛውንት፥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ቢሆንም እንኳን፥ ከዓመታት በኃላ ቤተሰባቸው ማግኘታቸው ደስታ ፈሮባቸዋል።

ሌላው ከሶስት ሳምንታት በፊት ለሶስት ዓመታት የተለያቸው ቤተሰቡ ከሱዳን የስደት ሕይወት መልስ በመቐለ ማይዓይኑ የተፈናቃዮችመጠልያ ያገኘው ተፈናቃይ ሕጉስ ፍቃዱ በነበረበት የሱዳን መጠልያ ጣብያዎች፥ ከኢትዮጵያ በተለይም ከትግራይ ምዕራባዊ ዞን ጦርነቱ ሽሽት የተፈናቀለው በአስር ሺዎች የሚቆጠር ህዝብ ከሱዳኑ ግጭት ጋር ተያይዞ የከፋ ሁኔታ እያሳለፈ ስለመሆኑ ይገልፃል። "በሱዳን ባለው ስደተኛ ላይ ከባድ ችግር ነው ያለዉ። ህፃናት፣ አረጋውያን፣ እናቶች በረሃብ በበሽታ እየሞቱ ነው። አሁን ደግሞ በሱዳን ጦርነት መነሳቱ ተከትሎ እርዳታ የለም፣ ሕክምና የለም፣ ምንም ነገር የለም። ኑሮ አስቸጋሪ ሆንዋል" ይላል።

ከስድስት ወራት በፊት በሱዳን የተቀሰቀሰው ጦርነት ተከትሎ፥ በሀገሪቱ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በተለያየ መንገድ ወደ ሀገራቸው እየተመለሱ መሆኑ የኢትዮጵያ መንግስት ሲገልፅ ቆይቷል።በተለይም እነዚህ ከምዕራብ ትግራይ ተፈናቅለው በሱዳን መጠልያዎች ያሉ ስደተኞች መንግስት፣ እርዳታ ሰጪ ተቋማት እና ሌሎች እንዲደርሱላቸው በቅርቡ ከሱዳን የተመለሱት ያነጋገርናቸው ተፈናቃዮች ጥሪ ያቀርባሉ። 

መቀሌ ዉስጥ የሰፈሩ ተፈናቃዮችም ቢሆኑ በቂ ርዳታ አያገኙም
መቀሌ በሚገኘዉ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ከሚገኙ ተፈናቃዮች አንዷምስል Million Hailesillassie/DW

"በልመና መኖር አይቻልም። ተለምኖም እየተገኘ አይደለም። ስደት፣ መፈናቀል ምንኛ ከባድ መሆኑ እየኖርነው ያለነው እኛ እናውቀዋለን። ስለዚህ መንግስት በፕሪቶርያው ውል መሰረት ወደ ሌላ አካባቢ ይሁን ወደ ሱዳን የተፈናቀለው ህዝብ ወደቦታው የሚመለስበት ሁኔታ ይፍጠር ነው የምንለው" ሲሉ አቶ ሕጉስ ፍቃዱ ይናገራሉ። 

በዚህ ጉዳይ ዙርያ የሚመለከታቸው የፌደራል እና ክልል የመንግስት ባለስልጣናት ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት ለግዜው አልተሳካም።

ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ 

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ