1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የህወሓትን ሕጋዊ ሰውነት ሊመልስ የሚችል ሕግ ፀደቀ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 27 2016

አንድ የምክር ቤት አባል ማሻሻያው ህወሓትን ወደ ሕጋዊ መስመር ለመመለስ ያለመ፣ድርጅቱ አሁንም በአማራ እና አፋር ክልሎች ችግር እየፈጠረ መሆኑን በመጥቀስ ማሻሻያውን ተቃውመዋል። ህወሓት በተለይ በአማራ ሕዝብ ላይ በማይካድራ፣ በራያ ቆቦ፣ በጭና ፣ በአጋምሳ፣ በኮምቦልቻ ፣ በጋሸና ፣ ሰሜን ሸዋ "በርካቶችን ጨፍጭፏል" ሲሉ ተቃውመዋል።

https://p.dw.com/p/4gdAU
የኢትዮጵያ ፓርላማ
የኢትዮጵያ ፓርላማምስል Solomon Muche/DW

ተሻሽሎ የፀደቀው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና ሥነ ምግባር አዋጅ

የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)ን ሕጋዊ ሰውነት መልሶ የሚሰጥ እንዲሁም፤ ግጭት በሚስተዋልባቸው ክልሎች እየተንቀሳቀሱ ያሉ ወደ ሀገራዊ ምክክር መድረኩ መግባት ለሚፈልጉ ቡድኖችና ድርጅቶች እድል የሚሰጥ የተባለ የተሻሻለ አዋጅ ፀደቀ። ተሻሽሎ የፀደቀው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና ሥነ ምግባር አዋጅ "ኃይልን መሠረት ያደረገ የአመጽ ተግባር ውስጥ የተሳተፈ" ነገር ግን ይህንን ተግባር ማቆሙንና በሰላም ለመንቀሳቀስ መስማማቱን የገለፀ የፖለቲካ ቡድን ከሚመለከተው የመንግሥት ተቋም የሚሰጠውን ማረጋገጫ መነሻ በማድረግ "በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ" እንዲመዘገብ እድል ይሰጣል።የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ግንቦት 27 ቀን 2016 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ጉባኤውን ከታደሙ 239 አባላት መካከል የአዋጁ ማሻሻያ በሁለት ተቃውሞ እና በአንድ ድምጽ ተዓቅቦ ፀድቋል። ማሻሻያው ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ፤ ህወሓት ሕጋዊ ሰውነቱን መልሶ እንዲያገኝ ያስችለዋል።

የምክር ቤቱ ውሎ፣ የተሰጡ አስተያየቶች

የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና ሥነ ምግባር አዋጅ "በአመጽ እና በሕገ-ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረ ፓርቲን ለመመዝገብ የሚያስችል ድንጋጌ" ስላልነበረው ይህንን ለማካተት ማሻሻያው እንዳስፈለገ ተገልጿል። ቀድሞ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ ሳይቀርብ ዛሬ ለምክር ቤቱ የቀረበው ይህ የማሻሻያ አዋጅ፤ ስምንት የምክር ቤት አባላት አስተያየት እና ጥያቄ የሰጡበት ሲሆን አብዛኞቹ ማሻሻያውን ደግፈው አስተያየት ሰጥተዋል። "ጦርነት ውስጥ ገብታችሁ ነበር፣ ግጭት ውስጥ ገብታችሁ ነበር፣ አሁን ብትመለሱም አንቀበልም ማለት የሰላም መንገድ አይደለም"የሕወሓት ሕጋዊ ሰውነት መሰረዝና አንደምታው


በምክር ቤቱ ኢዜማን የወከሉ አንድ አባል ማሻሻያውን ደግፈው ነገር ግን "አዙሪት ውስጥ ይከተናል" በማለት ሕጉ ጠንካራ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል። 
አንድ የምክር ቤት አባል ግን ማሻሻያው ሕወሓትን ወደ ሕጋዊ መስመር ለመመለስ ያለመ መሆኑን በመጥቀስ እና ድርጅቱ አሁንም በአማራ እና አፋር ክልሎች ችግር እየፈጠረ መሆኑንም በመጥቀስ ማሻሻያውን ተቃውመዋል።ሕወሓት በተለይ በአማራ ሕዝብ ላይ በማይካድራ፣ በራያ ቆቦ፣ በጭና ፣ በአጋምሳ፣ በኮምቦልቻ ፣ በጋሸና ፣ ሰሜን ሸዋ "በርካቶችን ጨፍጭፏል" ሲሉ ተቃውመዋል።

የህወሓት አርማ
የህወሓት አርማ

የአዋጁ የማሻሻያ ሀሳብ አስፈላጊነት

የአዋጁን የማሻሻያ ሀሳብ አስፈላጊነት ያብራሩት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ተስፋዬ በልጅጌ "እጅግ ኋላ ቀር የፖለቲካ ባሕል ያላት" ባሏት ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ አመለካከቶች የግጭትና የጦርነት አዙሪት ውስጥ እየከተቱን" ስለቆዩ ያንን ለመቀየር ታልሞ የቀረበ መሆኑን ጠቅሰዋል። በተሻሻለው አዋጅ "እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ለመመዝገብ የሚያመለክት ቡድን በሰላማዊ እና ሕጋዊ አግባብ ለመንቀሳቀስ መስማማቱን "ከሚመለከተው የመንግሥት ተቋም የሚሰጠውን ማረጋገጫ" መነሻ በማድረግ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማመልከቻው በቀረበ በ15 ቀናት ውስጥ ምዝገባ ይፈጽማል ይላል። ማረጋገጫ ይሰጣል የተባለው የመንግሥት ተቋም ማን ነው? የሚለው ጥያቄ ከምክር ቤት አባላት ቀርቧል።የሕወሓት የፓርቲነት ሕጋዊ ሰውነት መሰረዝ ላይ የተሰጡ አስተያየቶች 


ለቀረቡ ጥያቄዎች መልስ የሰጡት የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌድዮን ጤሞትዮስ ከሕወሓትም ሆነ በተለያዩ ክልሎች ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂ አካላት ጋር ለመነጋገር ፣ ምክክር ለማድረግ ጥረት መደረጉን ጠቅሰው፤ ስለሆነም ይህንን ኃላፊነት በዚህ ሂደት ለተሳተፉ የመንግሥት አካላት እንጂ ለአንድ ተቋም ብቻ መስጠቱ አላስፈለገም ብለዋል። "ይህ አዋጅ አላማው ምህረት መስጠት፣ ይቅርታ ማድረግ ወይም ተጠያቂነትን ማስቀረት አይደለም።

የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምስል Solomon Muchie/DW

ወደ ሕጋዊ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ይመለሳሉ ብለን ተስፋ እያደረግን ላለነው ፓርቲዎች እንዲሁም በሌሎች ግጭት በሚስተዋልባቸው ክልሎችም እየተንቀሳቀሱ ያሉ ቡድኖች፣ ድርጅቶች ወደ ሀገራዊ ምክክር መድረኩ ለመምጣት ቢፈልጉ ለሁሉም መንገድ እንዲከፍት ተደርጎ የተዘጋጀ ነው" በዚሁ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት ተፈርጆ የቆየው ሕወሓት፤ "ኃይልን መሠረት ያደረገ የአመጻ ተግባር" ውስጥ እየተሳተፈ ነው በሚል በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥር 10 ቀን 2013 ዓ.ም ከሕጋዊ የፖለቲካ ድርጅትነት ሕልውናው መሰረዙ ይታወሳል።

ሰሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ