1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ህወሓት ወዴት?

እሑድ፣ ነሐሴ 19 2016

"ህወሓት ፈረሰ ማለት የፕሪቶሪያ ስምምነት ፈረሰ ማለት ነው የሚል አባባል በውሉ የተካተቱ የትግራይ ባለድርሻ አካላትንና ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈሉትን የትግራይ የጸጥታ ኃይሎች መስዋዕትነት መናቅ ነው ብዬ አስባለሁ"

https://p.dw.com/p/4jrak
Äthiopien  TPLF Versammlung
ምስል Million Haileselassie/DW

የፕሪቶሪያ ስምምነት ይፈርስ ይሁን?

ህወሓት ወራትን በፈጀ ስብሰባው ከገመገማቸው ድክመቶች ዋነኛው  የስትራተጂክ አመራር ውድቀት እንደሆነፓርቲው በተደጋጋሚ ገልጿል። ይህን ተከተትሎ ደግሞ የተፈጠረውን የአመራር ችግርን ጨምሮ በፓርቲው የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ጉባኤ ማካሄድ አስፈላጊ ነው በማለትም ጉባኤውን አካሂዷል።
ይህ ጉባኤ ግን የምርጫ ቦርድ ህጋዊ ዕውቅና የለውም ሲል ተቃውሞታል። በምክትል ሊቀመንበሩ አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመሩ 14 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ በርካታ ጉባኤተኞችም በጉባኤው እንዳልተሳተፉ ተዘግቧል። በእንደዚህ ዓይነት አታካሮ የተጀመረው ጉባኤ ተጠናቆ የማዕከላዊ ኮሚቴ፣ የቁጥጥር ኮሚሽንና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን መርጦ ጉባኤውን አጠቃሏል።
ጉባኤው ሲጠቃለል ባወጣው የአቋም መግለጫ በጉባኤው ያልተሳተፉ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ከድርጅቱ በማገድ በህወሓት ስም ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንዳያካሂዱ ወስኗል። ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ የተባሉት ዶክተር ደብረጽዮን በሰጡት መግለጫም ህወሓት በጊዚያዊ አስተዳደሩ ቦታ እንዲሰጠው እንጠይቃለን ሲሉ ተደምጠዋል።
በትግራይ ጊዚያዊ መንግስት በኩል ደግሞ ጉባኤው ሕገወጥ መሆኑን በአጽንኦት በመግለጽ የጉባኤው ውጤት ተቀባይነት እንደማይኖረውና የሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎችም ተፈጻሚነት እንደማይኖራቸው ገልጿል። በተጨማሪም ከጊዚያዊ መንግስቱ እውቅና ውጭ ምንም አይነት ስብሰባዎች እንዳይካሄዱ መመሪያ አስተላልፏል።
ይህን ተከትሎ በትግራይ የፕሪቶሪያ ውል ፈርሶ ዳግም ጦርነት ይቀሰቀስ ይሁን የሚል ስጋትን አጭሯል። ዶይቸቨለ የህወሓት ከፍተኛ አመራር ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፉበት ውይይት አካሄዷል። 

የድምጽ ማዕቀፉን በመጫን ሙሉ ውይይቱን እንድትከታተሉት በአክብሮት እንጋብዛለን።

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ልደት አበበ