ኢትዮጵያውያን በታይላንድ እና በማይናማር ለመስራት የሚከፍሉት ዋጋ
ዓርብ፣ ኅዳር 6 2017ወይዘሮ ሀሊማ ኢትዮጵያ ነው ያሉት። ልጃቸው ለስራ በሚል ወደ ታይላድ ከሄደ አንድ ዓመት ከአንድ ወር አለፈው ይላሉ ። ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ እንደወጣ ስራ አግኝቶ ለሁለት ወራት ያህል በአንድ የግል ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ እየሰራም ነበር። ይሁንና የተሻለ ስራ ያገኘ መስሎት ታይላንድ ሀገር ለመሄድ ወሰነ። «ስራው ኦንላይ ማርኬት ላይ ነው። በወር ከ 1000 - 1500 ዶላር ታገኛለህ። እንግሊዘኛ ከቻልክ እና ፓስፖርት ካለህ ተባለ። አንዲት ደላላ ናት እንዲሄድ ያደረገችው።»
እናቱ እንደሚሉት ደላላዋ ኢትዮጵያዊት ነበረች። ወይዘሮ ሀሊማ እና ልጃቸው ብቻ አይደሉም በራሳቸው ሀገር ዜጎች የተሸወዱት።
«ችግራቸው ለእኛም ተረፈ»
«ትምህርት ማስረጃውን እና ሌሎች መረጃውን ጠየቁት። በአራት ቀናት ውስጥ አዘጋጀ። ቪዛ ጠየቀ፣ ጥቁር አንበሳ ሄዶ ክትባት ወሰደ። እኛም ድንገት ሆነብን እና ምንድን ነው ይኼ ነገር አልነው። ይኼው እንደዚህ አይነት ስራ ተገኘ አለን። እኛም ራሳችን ነን የሸኘነው። »ይላሉ ሌላው ያነጋገርናቸው አባት። ለራሳቸውም ሆነ ለልጃቸው ደህንነት ስለሚሰጉ ስም እንዳንገልፅ ጠይቀውናል።
የኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ምሩቅ የሆነው ልጃቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ስራ አጥቶ ተቀምጦ እያለ ታይላንድ ሀገር በዓመት 90 ሺ ዶላር ሊያገኝ የሚችልበት ስራ ተመቻችቶልሀል ሲባል ለመወሰን ጊዜ አልፈጀበትም።በደላሎች የተታለለው ወጣት መዳረሻ ታይላንድ ሳይሆን ማይናማር ሆናለች። ስራውም በኦንላይ ገንዘብ እያጭበረበረ ለተቀጠረበት ድርጅት ማስገባት ነው። አልችልም ወይም አልፈልግም ማለት አይሰራም። አባቱ እንደነገሩን ልጃቸው ደሞዝ እየተከፈለው አልነበረም። መልሱኝ የሚሉ ሰዎችም እስከ አንድ ሚሊዮን ዶላር ይጠየቃሉ።
«በዛን ጊዜ ስልክ አልተቀሙም ነበር። ለእኛ ይደውሉ ነበር ። ይኼ የስራ ቦታ ጥሩ አይደለም፣ ገንዘብ ክፈሉ ተብለናል ፣ ብር ፈልጉልን ይል ነበር። አሁን ከልጄ ጋር ከተነጋገርን አንድ ዓመት አልፎናል። »
ወይዘሮ ሀሊማ በአንፃሩ እድለኛ ናቸው። ለመጨረሻ ጊዜ ከልጃቸው የሰሙት በዚህ ሳምንት ነው። ስልክ ማውራት ባይችልም አልፎ አልፎ የድምፅ መልዕክት ይልክላቸዋል። ይሁንና ሁሌም የሚልክላቸው መልዕክት የሚያስጨንቅ ነው።«ደሞዝ አይከፈልም። 18 ሰዓት ነው የሚያሰሩን። አንተኛም። ምግብ ብቻ አይከለክሉንም ይለኛል።» ልጄ ያለበት ቦታ ያሉት ብቻ ኢትዮጵያውያን ከ 800 እስከ 1000 እንደሆኑ ነው የሚነግረኝ። እንደዛ አይነት ድርጅቶች ደግሞ ከ 10 በላይ አሉ እና በትንሹ ከ 3000 በላይ ኢትዮጵያውን እንዳሉ ነው የሚነግረኝ።»
የወይዘሮ ሀሊማም ልጅ ታይላንድ ተብሎ ሄዶ አሁን የሚገኘው ማይናማር ነው። እዛም ለመድረስ አንድ ቀን ተኩል እንደፈጀባቸው እና ደላሎች ተቀባብለው እንደወሰዷቸው ወይዘሮ ሀሊማ ከልጃቸው ሰምተዋል።
በተናጠል መፍትሔ ያላገኙት ወላጆች ተሰባስበው እነሱ እንደሚሉት ጉዳዩን ከሰባት ወራት በፊት ለኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ቆንስላ አመልክተዋል። ያገኙትም ምላሽ፤ «በጎረቤት ሀገራት መንግሥታት በኩል ነው እንጂ እዛ ኤምባሲ የለንም። በተስፋ ጠብቁ ። ያሉት የማይመች ቦታ ነው ። የሚል መልስ ነው የተመለሰልን »
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ
«ዜጎቻችን የህገወጥ ሰዎች አያዘዋዋሪዎች ሰለባ ሊሆኑ አይገባም» ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው ትናንት ሀሙስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መንግሥት ችግር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ከሳዑዲ አረቢያ ፣ ሊባኖስ እና ማይናማር ማስወጣቱን ተናግረዋል። ከማይናማር የተመለሱትን በሚመለከት «እስካሁን በተደረገ ጥረት 31 ዜጎቻችን ከነበሩበት አስቸጋሪ ሁኔታ ወጥተው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል። ዜጎች መዳረሻ አድርገው ከመረጧቸው ሀገራት ጋር የስራ ስምሪት ስምምነት አለመኖር ፣ ምንም ባልተያዘ እና ባልተጨበጠ መረጃ ላይ ተመስርተው በህገ ወጥ ሰዎች አዘዋዋሪዎች ተታለው ወደ ተለያዩ ቦታ የሚያቀኑ ሰዎች በየጊዜው የችግሩ ሰለባ እየሆኑ መጥተዋል። ያሉበትንም ቦታ፣ ቁጥራቸውንም ለማወቅ አስቸጋሪ ይሆናል። ማይናማር አካባቢ የገጠመንም ችግር ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው። »
ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉዳዩን እንዲከታተል የ 149 ወጣቶች ስም ዝርዝር ከእነ ፓስፖርት ቁጥራቸው ሰጥተን ነበር የሚሉት ወይዘሮ ሀሊማ ለጊዜው ሚኒስቴሩ ተመልሰዋል ካላቸው 31 ኢትዮጵያውያን መካከል የሚያውቁት ሰውም ሆነ ቤተሰብ የለም። ይሁንና ገንዘብ ከፍለው ወይም ድርጅቱ አሰናብቷቸው የተመለሱ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ያውቃሉ። ከእነዚህ መካከል ስሟን የማንገልፀው ተከታይዋ ወጣት ትገኛለች። ወደ እዛ የሄድኹት አንድ የማውቀው ጓደኛዬ በሰጠኝ ጥቆማ ተታልዬ ነው ትላለች። « እዛ እያለ አልፎ አልፎ እንደዋወል ነበር። ስለስራው ስናወራ ኦንላይን ማርኬቲን እንደሆነ እና ቀላል ነው፤ እቃ መሸጥ ነው። አልፎ አልፎም ተጨማሪ ክፍያ አለው ይለኝ ነበር። እዚህ ተመልሶ ሲመጣም አየሩ አልተስማማኝም። በቂ ገንዘብ ይዤም ስለተመለስኩ መቆየቴ ምን ይጠቅመኛል? ነው ያለኝ። »
ከአራት ወራት ገደማ በኋላ ከማይናማር የተመለሰችው ወጣት
እሷም መጀመሪያ የሄደችው የታይላንድ ዋና ከተማ ባንኮክ ነበር። በኋላ ግን እሷ እና እንደሷ የተታተሉ ወጣቶች ለ 9 ሰዓት ያህል ከተጓዙ በኋላ ራሳቸውን የማይናማር ድንበር አካባቢ አገኙት ። አንድ ሆቴል ካደሩም በኋላ ሰዎች አዋክበው በአንዲት ትንሽዬ መርከብ ውኃ አሻግረው እንደወሰዷቸው ነግራናለች። « ብዙ ወታደሮችም ነበሩ። በእነሱ ተጠብቀን ነው የወሰዱን። ከዛ ጫካ ውስጥ ያለ ትልቅ ካምፓኒ ነው። ስንገባ ሌላ ታሪክ ነው። ብዙ ኢትዮጵያውን አሉ። ብዙ አፍሪቃውያንም አሉ። »
ወጣቷም ለአራት ወራት ያህል እዛ ቆይታለች። በእነዚህም ጊዜያት ስራዋ የተነገራት እና የጠበቀችው ሳይሆን የማጭበርበር ስራ እንደሆነ ትረዳለች። ለመመለስም መፍትኼ ሆኖ ያገኘችው ለስራው ብቁ ሆኖ አለመገኘትን ነው። « ቀጣሪዎቻችን ለምግብ እና ማደሪያ እስከ 10 ሺ ዶላል ወጪ እንደምናስወጣቸው እና የሚጠበቅብንን ስራ ብቁ ሆነን ካልተገኘን እንደሚያሰናብቱን ስንሰማ ራሳችንን ችግር ውስጥ በማያስገባን መልኩ ተቃራኒውን ማድረግ ጀመርን ትላለች። ለመመለስም እንደ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ተጨማሪ ገንዘብ መክፈል አልነበረባትም። በዚህም እድለኛ ነች።
«ሁለት አይነት ነው ያለው። በመንግሥት ቁጥጥር ስር ያለ አለ። እኛ የነበርንበት እዛ ነው። እኛ ስለምንፈራ አንጠይቅም እንጂ መመለስ ከፈለጋችሁ ኑ እዚህ ጋር የሚል አንድ ቢሮ አለ። ሌሎች ቦታዎች የተሸጡ ጓደኞቼ ደግሞ አሉ የስቃይን ጥግ የሚያዩበት »
ወጣቷ ካለፈችበት ተሞክሮ ሌሎች ወጣቶችን መምከር የምትፈልገው፣«አንዳንዶች እድል ቀንቷቸው ብዙ ገንዘብ ያገኛሉ። አንዳንዶች ደግሞ መከራ ውስጥ ይገባሉ። ከዚህ ሁሉ መከራ አለመሄድ በጣም ተመራጭ ነው። የሚባለው ነገር እውነት ነው። አንዳንድ ሰዎች ካላየሁ አላምንም ይላሉ። ግን በቂ መረጃ ኖሯቸው ቢሄዱ ይሻላል። የገዛ ቤተሰባቸው አታሏቸው የሄዱ አውቃለሁ። »
ወይዘሮ ሀሊማ ለልጃቸው እስካሁን መፍትሔ ባያገኙም ፤ እሳቸውም ወላጆችም ሆኑ ስራ ፈላጊ ወጣቶች ለውሳኔ እንዳይቻኮሉ እና ከሌሎች ተሞክሮ እንዲማሩ ይመክራሉ። «ልጆች እንደዚህ አይነት ስራ አገኘን በሚሉበት ሰዓት ቤተሰብ ህጋዊነቱን ማረጋገጥ ይኖርበታል። የስራ ውል መምጣቱን ማየት እንዳለባቸው፣ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ እና ሰራተኛ እና ማህበራዊ ሚኒስቴር ማረጋገጡን ፤ውል መፈረሙን እንደዚህ አይነት ውስጥ እንዳይገቡ ነው የምመክራቸው።»
ልደት አበበ
እሸቴ በቀለ