1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሌላው የኢትዮጵያውያን ስደተኞች የመከራ መንገድ ፤ ታይላንድ ባንኮክ

ሐሙስ፣ ሐምሌ 18 2016

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ በኮምፒዉተር ሳይን እና ተያያዥ የትምህርት መስኮች የተማሩ ኢትዮጵያዉያን ወጣቶችን እያደኑ በኦንላይን የገንዘብ ምንተፋ ተግባር የሚያሰማሩ እንደ ታይላንድ ፣ ማይናማር እና ላኦስን በመሳሰሉ ሀገራት ውስጥ የሚገኙ ኩባንያዎች ተበራክተዋል።

https://p.dw.com/p/4ijXX
China | Symbolbild Hacker
ምስል Nicolas Asfouri/AFP/Getty Images

ታይላንድ ፤ የኢትዮጵያውያን ስራ ፈላጊዎች ሌላ የመከራ መስመር

ለደህንነታቸው ስንል ስማቸውን የቀየርንላቸው እመቤት እና አቤል ወንድሞቻቸው ስራ ፍለጋ ወደ ታይላንድ ካቀኑ በኋላ በኦን ላይን ገንዘብ መንታፊዎች እጅ የወደቁባቸው ናቸው። የሁለቱም ወንድሞች በመዳረሻ ቪዛ ወደ ታይላንድ የተጓዙት ከወራት በፊት ሲሆን ከመነሻቸው የተነገራቸው ከአንድ መቶ እስከ መቶ ሃምሳ ሺ የኢትዮጵያ ብር ተከፋይ እንደሚሆኑ ነበር ።

ነገር ግን በመጨረሻ የገጠማቸው የእነርሱንም ሆነ የቤተሰባቸውን ህይወት አመሳቅሏል። ለመሆኑ የደቡባዊ ኤስያ ሃገራት ህገ ወጥ ኩባንያዎች ኢትዮጵያውያኑን ወጣቶች በምን መንገድ ይሆን የሚያጠምዱት ? እመቤት ወንድሟ ወደ ታይላንድ ያቀናበትን አጋጣሚ ትናገራለች።

«ናቲ ይባላል ወንድሜ እና ጓደኛው ነው የታይፒንግ ስራ አለ ታይላንድ አንድ ሺ ዶላር ነው የሚከፈለው ብሎ ወሰደው ማለት ነው ። እና ኢንተርቪው ተደርጓል፣ እንደማንኛውም መደበኛ ስራ ላይ የምትጠብቃቸው ነገሮች አሟልቶ ነው የሄደው።»

ኢስያውያኑ ህገ ወጥ ኩባንያዎች ኢትዮጵያውያን እርስ በእርሳቸው መልዕክት እንዲቀባበሉ እና ጥርጣሬ አልባ በሆነ መንገድ ወጣቶችን ለማጥመድ መደላድል እንደፈጠረላቸው የሚናገረው ደግሞ አቤል ነው። 
«በቅርብ በሆኑ ሰዎች ቤተሰብ፣ አጎት፣ እህት፣ ዘመድ፣ አክስት፣ የዘመድ ልጅ በሆኑ ሰዎች እና መንፈሳዊ አባት በሚባሉ ሰዎች ጨምሮ ተዓማኒነት ያላቸውን ሰዎች ተንተርሶ ነው ጥያቄው ለልጆቹ የሚቀርበው።

የአውሮጳ ህብረት በኢትዮጳያውያን ላይ የጣለው የቪዛ ቁጥጥር
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ በኮምፒዉተር ሳይን እና ተያያዥ የትምህርት መስኮች የተማሩ ኢትዮጵያዉያን ወጣቶችን እያደኑ በኦንላይን የገንዘብ ምንተፋ ተግባር የሚያሰማሩ እንደ ታይላንድ ፣ ማይናማር  እና ላኦስን በመሳሰሉ ሀገራት ውስጥ የሚገኙ ኩባንያዎች ተበራክተዋል።  ወንድሟ  ታይላንድ ሀገር በሚገኝ ጓደኛው ተታሎ መወሰዱን የምትናገረው እመቤት እዚያ ሲደርስ የጠበቀው ከመነሻው ቃል ከተገባለት እና ከጠበቀው በፍጹም የተለየ ነበር ።
«ከአንድ ጓደኛው ጋር ሁለት ሆነው ነው የሄዱት እና እዚያ ሲደርሱ ለዚህ ለጓደኛቸው ለጠራቸው ልጅ ሲደውሉ የቢሮ ሰዎች ይመጡና ይወስዷችኋል አላቸው ። ገና ሆቴልም አልገቡም ማለት ነው። ከዚያ በኋላ የ9 ሰዓት መንገድ ነው የወሰዷቸው። ረዝም መንገድ ነው የሄዱት ። ከዚያ በኋላ ጀልባ ላይ ውጡ አሏቸው። ትንሽ ጥርጣሬ ቢገባቸውም ጓደኛቸው ስለሆነ አልተጠራጠሩም ነበር።  በኋላ ግን በወታደሮች ወደ ሚጠበቅ ካምፕ ነው የወሰዷቸው   »

በዓለማቀፍ የስደተኞች ማዕከል የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች
ፎቶ ከማህደር ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ በኮምፒዉተር ሳይን እና ተያያዥ የትምህርት መስኮች የተማሩ ኢትዮጵያዉያን ወጣቶችን እያደኑ በኦንላይን የገንዘብ ምንተፋ ተግባር የሚያሰማሩ እንደ ታይላንድ ፣ ማይናማር  እና ላኦስን በመሳሰሉ ሀገራት ውስጥ የሚገኙ ኩባንያዎች ተበራክተዋል። ምስል Michele Spatari/AFP


ለወንጀል ስራ መታጨታቸውን ያልተረዱት ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በመላው ዓለም የሰዎችን መረጃ በመጥለፍ ገንዘብ በመመንተፍ ስራ ላይ እንዲሰማሩ ስልጠና እንደሚሰጣቸው የምታናገረው እመቤት ወንድሟ ከገባበት አስቸጋሩ ሁኔታ ለመውጣት ሶስትሺ የአሜሪካ ዶላር መክፈል እንዳለበት እንደተነገረው ትገልጻለች።
«ቤቱ መረጃ መመንተፍ ነው ታይፒንግ የተባለው ስራም ውሸት ነበር። ለአንድ ሳምንት ስልጠናውን ትጀምራላችሁ ተብለናል አልፈልግም የምትሉ ከሆነ ግን ሶስት ሺ የአሜሪካ ዶላር ከፍላችሁ በሱ ስለሆነ የገዛናችሁ  ስለዚህ ይህን መክፈል ይኖርባችኋል አለበለዚያ ኮንትራታችሁን ፈርሙ ተባሉ ማለት ነው »

ሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የድረሱልን ተማጽኖ
ኢትዮጵያውኑን እርስ በእርስ እያጠላለፈ በሚወስደው የደቡባዊ ኢስያ ሃገራት የህገ ወጥ ኩባንያዎች የወንጀል መረብ ምን ያህል ኢትዮጵያውያን ተታለው እንደተወሰዱ የተረጋገጠ መረጃ የለም ። ነገር ግን ወንድሙ በተመሳሳይ መንገድ የተወሰደበት አቤል እንደሚለው ከሆነ ማይናማር ውስጥ ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ሊወጡት በማይችልበት ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ ።
« ማይናማር ውስጥ በሚገኘው አንዱ ቅርጫፍ ብቻ ከ150 በላይ ኢትዮጵያውያን ወንዶች 9 ወይም 10 የሚሆኑ ሴቶች እንዳሉ ነው የማውቀው። አንዱ ቅርጫፍ ላይ ብቻ »
ወጣቶቹ እስር ቤት በሚመስል ሁኔታ ውስጥ በቀን ለ16 ሰዓታት በኮምፒውተር ላይ እንደሚያሳልፉ ጭምር ነው አቤል ከወንድሙ የተረዳው ።
« ሰዎችን መፈለግ ነው 16 ሰዓት ቁጭ ብለህ ኮምፒዉተር ላይ ልምድ ከሌለህ ከባድ ነው ለአይንህም ለጤንነትህም አስጊ ነው ፣ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነው መረጃ የሚመነተፍ ሰው ሲያስሱ የሚውሉት»

በማላዊ የኢትዮጵያውያን ስደተኞች አበሳ
ይህ አዲሱ የደቡባዊ እስያ በስራ ዕድል ስም ለኢትዮጵያውያን የተደገሰ ሌላ የመከራ ድግስ ነው ። 

እመቤት እንደምትለው ወንድሟ እና ጓደኛውን ከገቡበት አስቸጋሪ ሁኔታ ለማስወጣት አድርጉ የተባሉትን ከማድረግ ውጭ ሌላ ምርጫ አልነበራቸውም። 
« እና በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ብዙ የሚመታ ሰው አለ የሚያዩት ፤ አልፈልግም ማለት አትችልም ። እኛ ራሱ የጊዜ ገደብ ተሰጥቶናል ። አሁን አጋጣሚ በጣም እያስቸሯቸው ሲመጡ ከፈልን ። እኔ እና የወንድሜ ጓደኛ ቤተሰቦች ከፈልን ፤ ሶስት ሶስት ሺ ዶላር ፤ ባይናንስ በሚባል አካውንት አስተላለፍንላቸው ።»
ወጣት መላኩ ደግሞ ቲክቶክን በመጠቀም ወደ ታይላንድ መሰል ሃገራት የሚደረጉ ህገ ወጥ ጉዞዎች አስከፊ ገጽታን በተመለከተ የጥንቃቄ መረጃ ያጋራል ። በመረጃ መንታፊዎቹ እጅ ከወደቀ በኋላ ታይላንድ ውስጥ ለጥቂት ያመለጠ አንድ ወጣት ማነጋገሩን የሚገልጸው መላኩ በርካታ ኢትዮጵያውያን የችግሩ ሰላባ መሆናቸው አሳሳቢ ነው ይላል። 

በጀርመን ብዝኃነት ውስጥ የአፍሪቃውያን ሞያተኞች ሚና
« አጋጣሚ ሆኖ በውስጥ ኢንቦክስ ላይ ላይ ላክልኝ ብሎኝ ከታይላንድ ተደወለልኝ ። መሌ በጣም ነው የምናመሰግነው ለመረጃው፤ በጣም ብዙ ሰው እየተጎዳ ነው እባክህ አሁንም ጩህ ፤ በቁጥር ልገልጸው የማልችለው ኢትዮጵያውያን ነን ያለነው። በጣም ስቃይ እና እንግልት ላይ ናቸው ብሎ  ከዚያው ቀጥታ ካመለጠ ልጅ መረጃው ሲደርሰኝ እኔም መረጃውን ማጋራት ገፋሁበት »
ለመሆኑ ወደ ደቡባዊ የኢስያ ሃገራት ተታለው በገፍ እየተወሰዱ ያሉ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግስት መረጃ ይኖረው ይሆን ስንል የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቃባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላን ጠይቀን ነበር። አምባሳደሩ እንዳሉት በታይላንድ ተመሳሳይ ችግር ውስጥ የነበሩ ዋጣቶችን ከሀገሪቱ መንግስት ጋር በመነጋገር ማስመለስ መቻሉን ገልጸው ነገር ግን በማይናማር አሁንም ድረስ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ወጣቶችን በተመለከተ  ጥረቱ መቀጠሉን አመልክተዋል። 

በዓለማቀፍ የስደተኞች ማዕከል የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች
ፎቶ ማህደር ፤ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስራ ፈላጊዎች ወደ መካከለኛው ምስራቅ እና ወደ አውሮጳ ለመግባት ለአመታት የተከተሉት የህገ ወጥ መንገድ በርካቶችን ለህልፈት መዳረጉ ይታወቃል ።ምስል Michele Spatari/AFP


« አንዳንድ ወጣቶች ባንኮክ ላይ ስራ አለ በሚል  በተሳሳተ ወይም ህገ ወጥ በሆነ መንገድ ወደ ባንኮክ እንዲሄዱ ከተደረገ በኋላ ከባንኮክ ደግሞ በፎርጂድ ቪዛ ወደ ማይናማር  እንዲገቡ ተደርጎ ያን ቪዛ እያራዘሙላቸው እዚያ አካባቢ አንዳንድ ህገ ወጥ ስራዎች እንዲሰሩ እንዲቸሩ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ነው ያሉት እና ይህን መሰረት አድርገን ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩልህ የእኛም ተቋም ክትትል ሲያደርግ ነበረ፤  በተለይ ባንኮክ አካባቢ በዚህ ሁኔታ ተታለው የሄዱ ጥቂት ኢትዮጵያውያንን ኤምባሲያችን ከታይላንድ መንግስት ጋር በመነጋገር ማስመለስ ችሏል። ሆኖም ግን ወደ ማይናማር የተሻገሩት ትንሽ አስቸጋሪ ነው ። ያው ጉዳዩን ግን በኤምባሲያችን በኩል ከማይናማር መንግስት ጋር እየተነጋገርን ነው።
»

የመን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ይዞታ
በርካታ ኢትዮጵያውያን ስራ ፈላጊዎች ወደ መካከለኛው ምስራቅ እና ወደ አውሮጳ ለመግባት ለአመታት የተከተሉት የህገ ወጥ መንገድ በርካቶችን ለህልፈት መዳረጉ ይታወቃል ። አሁን ደግሞ በህጋዊ ሽፋን ወደ ደቡባዊ የኤስያ ሃገራት የሚደረጉ ጉዞዎች አደገኝነታቸው ጎልቶ ታይቷል። በተዘባ መረጃ ወደ ታይላንድ ለስራ የሚደረጉ ጉዞዎች ከመደረጋቸው በፊት ተገቢውን መረጃ ማግኘት አስፈላጊ መሆኑን አምባሳደር ነቢዩ ተድላ ተናግረዋል።


ታምራት ዲንሳ
እሸቴ በቀለ