1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችኢትዮጵያ

በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘም ፋይዳ

እሑድ፣ የካቲት 3 2016

ባለፈው ሳምንት ዓርብ ዕለት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአማራ ክልል የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለቀጣይ አራት ወራት እንዲራዘም በአብላጫ ድምፅ ወስኗል። የሰብአዊ መብት ተቋማትን ጨምሮ ብዙዎች የድንጋጌው መራዘም የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶችና ጥቃቶች እንዲቀጥሉ እንዳያደርግ ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።

https://p.dw.com/p/4cEor
የኢትዮጵያ ፓርላማ
የኢትዮፕያ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዲስ አበባምስል Solomon Muche/DW

በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘም ፋይዳ

 

ባለፈው ሳምንት ዓርብ ዕለት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአማራ ክልል የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለቀጣይ አራት ወራት እንዲራዘም በአብላጫ ድምፅ ወስኗል። የሰብአዊ መብት ተቋማትን ጨምሮ ብዙዎች የድንጋጌው መራዘም የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶችና ጥቃቶች እንዲቀጥሉ እንዳያደርግ ስጋታቸውን እየገለጹ ነው። ለስድስት ወራት በአዋጁ ምክንያት በክልሉ የኅብረተሰቡ የየዕለት ዘርፈ ብዙ ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ከመገደቡ ባሻገር በመንግሥትና በፋኖ ታጣቂ ኃይሎች መካከል ውጊያው ተባብሶ መቀጠሉ ሲነገር ከርሟል። በተደጋጋሚ በተፈጸሙት የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃቶች ቁጥራቸው በትክክል ያልታወቀ ዜጎች መገደላቸው፣ በከተሞችና የእምነት ተቋማት ሳይቀር በየስፍራው ያልታጠቁ ወገኖች መግደልና ማንገላታትና የሰብአዊ መብቶች ጥሰት መድረሱን የሰብአዊ መብት ተቋማት ሳይቀሩ ይፋ አድርገዋል። ታጣቂዎቹም እንዲሁ በአንጻሩ በሚወስዷቸው እርምጃዎች ጉዳት መድረሱን መረጃዎች ያሳያሉ። በኢንተርኔት መዘጋትና በስልክ አገልግሎት መቆራረጥ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት አስቸጋሪ በሆነበት የአማራ ክልል በድጋሚ ለአራት ወራት የአስቸኳይ ጊዜ ማራዘም ችግር ውስጥ የሚገኘውን የክልሉን ማኅበረሰብ ኑሮ ይበልጥ ያከብደው ካልሆነ መፍትሄ አይሆንም የሚሉ ድምፆች እየተሰሙ ነው። መንግሥት በበኩሉ አዋጁ ባለፉት ስድስት ወራት የክልሉን የፀጥታ ሁኔታ ለማሻሻል እንደረዳው ይገልጻል።

ፎቶ ከማኅደር፤ በጭና ተክለሃይማኖት መንደር የአካባቢው ነዋሪዎች
በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜው መራዘም ተጨማሪ የሰብአዊ መብቶች ጥሰትና ችግሩ እንዲባባስ እንዳያደርግ ስጋታቸውን የሚገልጹ ጥቂት አይደሉም። ፎቶ ከማኅደር፤ በጭና ተክለሃይማኖት መንደር የአካባቢው ነዋሪዎች ምስል AP/picture alliance

በተቃራኒው ኅብረተሰቡ እንቅስቃሴው መገደቡን፤ ንግዱ መቀዛቀዙን፤ ትምህርት ቤቶች እና የጤና ተቋማት መደበኛ ሥራቸው በአብዛኛው መስተጓጎሉን በመግለጽ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለማረጋጋት እንዴት ነው መፍትሄ የሚሆነው ሲሚል ይጠይቃል። የአስቸኳይጊዜው በተራዘመ ማግሥት ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ በሀገሪቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው  በሰጡት ማብራሪያ ሥርዓተ አልበኝነት መንገሡን ቢያረጋግጡም በአማራ ክልል አሁን የሚታየውን ግጭት ጦርነት የቀሰቀሰው ዋና ጉዳይ የልማት ጥያቄና የሕገ መንግሥት ለውጥ ነው አይነት አንድምታ ያለው ነው። ጉዳዩ ይመለከተናል የሚሉ ወገኖች በበኩላቸው ምንም እንኳን የተጠቀሱት ችግሮች ቢኖሩም ነፍጥ ለማንሳት ያስገደዳቸው የመኖር ያለመኖር የህልውና ጥያቄ እንደሆነ ይናገራሉ። በሀገሪቱም በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለማካሄድ ምቹ አውድ እንደሌለ ለዚህ ማሳያውም በየጊዜው በዘፈቀደ ወደ ወህኒ የሚላኩ ዜጎች መሆናቸውንም በመግለጽ ለውሳኔያቸው መረጃ ያቀርባሉ። በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘምና ፋይዳው የዕለቱ የመዋያያ ርዕሳችን ነው። ሙሉውን ውይይት የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ሸዋዬ ለገሠ