1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በተራዘመው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስተያየት

ሰኞ፣ ጥር 27 2016

በአማራ ክልል ለተጨማሪ አራት ወራት የተራዘመው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ የውስጥ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱበት ሁኔታ አለመመቻቸቱን እንደሚያሳይ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ተናገሩ። የድንጋጌው መራዘም የሕዝቡን ችግር እንደማይቀርፍ ሌሎች ያነጋገርናቸው የፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎችም ይናገራሉ።

https://p.dw.com/p/4c37e
የተወካዮች ምክር ቤት
የተወካዮች ምክር ቤት በአማራ ክልል የአስቸኳ ጊዜ አዋጅ ጊዜን መጠናቀቅ ተከትሎ ባደረገው ልዩ ስብሰባ አዋጁ ለሌላ አራት ወራት እንዲራዘም ዉሳኔ አስተላልፏል፡ምስል Solomon Muchie/DW

የፖለቲካ ፓርቲዎች አስተያየት

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሳምንቱ መጨረሻ ባደረገው ልዩ ስብሰባ በአማራ ክልል ለ ስድስት ወራት ተደንግጎ የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለአራት ወራት እንዲራዘም በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል። የድንጋጌው መራዘም ችግር ያባብስ ካልሆነ በስተቀር የሕዝቡን ችግር እንደማይቀርፍ የገለፁ ሌሎች ያነጋገርናቸው የፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎች መንግሥት ራሱን ለውይይት እና ድርድር ቢያዘጋጅ እንደሚሻል ገልፀዋል።  መንግሥት ዐዋጁን ማራዘም ያስፈለገው ቀሪ ያላቸው ሥራዎችን ለማጠናቀቅ እና በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የፀጥታ ሥጋት አዝማሚያዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑን አስታውቋል።

"ችግሩ በውይይት እንጂ በዐዋጅ አይፈታም"

በቅድሚያ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ደስታ ዲንቃ ናቸው። 
«ሁለት ነገሮችን ያሳያል። አንደኛ መንግሥት እዚያ [ አማራ ክልል ] አካባቢ ያለውን ነገር በመደበኛ የመንግሥት አሠራር የመፍታት ደረጃ ላይ አለመድረሱን ያሳያል። ሁለተኛ ደግሞ በሀገር ደረጃ ያሉት የውስጥ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱበት ሁኔታ አለመመቻቸቱን ያሳየናል።»

የደሴ ከተማ
የደሴ ከተማምስል Tiksa Negeri/REUTERS

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ( አብን ) ሊቀመንበር በለጠ ሞላ የፓርቲውን አቋም እንዲገልፁ ቢደወልላቸውም ምላሽ አይሰጡም። የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ምክትል ፕሬዝዳንት ሙላቱ ገመቹ በአንፃሩ «ችግሩ በውይይት እንጂ በዐዋጅ ብቻ የሚፈታ አይደለም» ብለዋል። 

«ይህን የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ በሀገሪቷ ውስጥ ማወጅም ጠቃሚነት የለውም። ሕዝብ በጠቅላላው በየአካባቢው ችግሮች ተፈጥረዋል። ችግሮች በውይይት የሚፈቱ እንጂ በዐዋጅ ብቻ የምንፈታው አይደለም። ስለዚህ ዐዋጁ ረዘመም አጠረም አሁን ያለው ችግር አልተቀረፈም።»

መንግሥት አራት ወራቱን ለውይይት እና ድርድር እንዲያውል መጠየቁ 

የሕብር ኢትዮጵያ ሊቀ መንበር አቶ ግርማ በቀለ። ይህ አራት ወር  ይልቁንም ለውይይትና ለድርድር ቢውል ይበጃል ብለዋል።
«በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህ ስድስት ወር ቢታወጅም ከዚያ ባነሰ ጊዜ ውስጥ ዐዋጁን እናነሳለን ብለው የገቡበት ነበር ።
እንዳየነው ነገሮች ከዕለት ወደ ዕለት እየከፉ እና እየባሱ እየከረሩ የመጡበት ሁኔታ ነውና ያለው ይሄ የሚያሳየው ነገሮችን በኃይል በማፈን መፍታት እንዳልተቻለ ነው።» 
ቀሪ ያላቸው ሥራዎችን ለማጠናቀቅ እና በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የፀጥታ ሥጋት አዝማሚያዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለማራዘም ውሳኔ ላይ መደረሱን መንግሥት አስታውቋል። አቶ ሙላቱ ገመቹ ዐዋጁ አማራ ክልል ይባል እንጂ አድማሱ ሰፊ መሆኑን በማሳያ ጭምር ይገልፃሉ። አቶ ግርማ በቀለም ተመሳሳይ አስተያየት አላቸው።

ዐዋጁ በጎ ተጽእኖ አላመጣም- የምክር ቤት አባል

መነጋገር ፣ መደራደር፣ የሕዝብን ጥያቄ መፍታት እንጂ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አያስፈልገንም ብለን ነበር። ሆኖም በወቅቱ ሰሚ አልነበረንም ያሉ የምክር ቤት አባል «የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምንም በጎ ተጽዕኖ አላመጣም። እውነተኛ ድርድር እና ውይይት እየተደረገ አይደለም፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አጠቃላይ የሀገሪቱን ልማት ወደኋላ ነው የመለሰው» በሚል የሕጉን መራዘም ተቃውመው ነበር። የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢም መፍትሔው ውይይትና ድርድር ነው ይላሉ። 

ድንጋጌው የፈጠረው ሥጋት

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የበላይ ኃላፊ ዶክተር ዳንኤል በቀለ ከአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ መራዘም አስቀድመው የዐዋጁ  መራዘም አሳሳቢ መሆኑን ገልፀው ነበር። በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲም የአዋጁ መራዘም እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ገልጿል።
 

ሰለሞን ሙጬ
ልደት አበበ
ሸዋዬ ለገሠ