በአሙሩ ወረዳ የታሰሩ ከመቶ በላይ ሰዎች ባለፉት ሰባት ወራት ፍርድ ቤት አልቀረቡም
ሐሙስ፣ ኅዳር 5 2017በአሙሩ ወረዳ የታሰሩ ከመቶ በላይ ሰዎች ባለፉት ሰባት ወራት ፍርድ ቤት አልቀረቡም
ከሚያዚያ ወር 2016 ዓ.ም አንስቶ በሆሮ ጉደሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ የታሰሩ ከ100 በላይ ሰዎች እስካሁን ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን የታሳሪ በተሰቦች ተናገሩ፡፡ በአሙሩ ወረዳ ኦቦራ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ የታሰሩ እነዚህ ሰዎች ልጆቻቹ በአካባቢው ከሚንቀሳቀሱ ታጠቂዎች ጋር ተቀላቅለዋል ተብለው መታሰራቸውን ያነጋገርናቸው ታሳሪ በተሰቦች ለዲዳቢሊው አመልክተዋል፡፡ ለሰባት ወራት ያህል ያለምንም ፍርድ ታስረዋል የተባሉ ሰዎች አብዛኞቹ አርሶ አደሮች ናቸው ተብሏል፡፡ የወረዳው ፖሊስ ጽ/ቤት ጉዳዩ ኮማንድ ፖስትን ይመለከታል በማለት በጉዳዩ ላይ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም፡፡
የታጠቂዎች እንቅስቃሴ በስፋት ከሚስተዋልባቸው የወለጋ አካባቢዎች አንዷ ከሆነችው የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ ከሚያዚያ 4/2016 ዓ፣ም አንስቶ በርካታ ሰዎች ልጆቻቹ ታጥቆ ጫካ ይንቀሳቀሳሉ ተብለው መታሰራቸው ተነግረዋል፡፡ አቶ ቶሎሳ የተባሉ አባታቸው የዛሬ 7 ወራት ገደማ መታሰራቸውን የነገሩን ወጣት ስለሺ በአካባቢው ከታጣቂዎች ጋር የተቀላቀሉ ልጆችን እስኪመጡ ድረስ ታስራችሁ መቆየት አለባችሁ ተብለው አባታው በፖሊስ መታሰራቸውን አመልክተዋል፡፡ ከታሰሩት ጊዜ አንስቶም ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን በመግለጽ በወረዳው ፖሊስ ጣቢያ ከ100 በላይ ሰዎች በተመሳሳይ ጉዳይ ታስረው እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
በሆሮ ጉደሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ ኦቦራ ከተማ አባታቸው ከታሰሩት መካከል ሌላው ወጣት ተስፋዬ ደበላ የሚባሉ ነዋሪ አንዱ ሲሆን አባታቸው አቶ ደበላ ከታሰሩት ከሰባት ወራት በላይ እንደሆናቸው አመልክተዋል፡፡ አቶ ደበላም አንድ ልጃቸው ወደ ታጣቂዎች ተቀላቅለዋል መባሉንና ልጃቸውን እንዲያመጡ ተብለው መታሰራቸውን አብራርተዋል፡፡ ከቤሰተብ ጋር ከተለያዩ ረጅም ጊያዜያትን ያስቆጠረውና የት እንዳለ የማያውቁትን ልጃቸውን እንዲያመጡ መጠየቃቸውን በመግለጽ ጉዳያቸው ታይቶ ከእስር እንዲለቀቁ ለማድረግ ከወረዳው እስከ ፌዴራል ቢንቀሳቀሱም መፍትሄ ማግኘት እንዳልቻሉ ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም ባለፈው ሳምንት አሙስ እናታቸው በእዛው ፖሊስ ጣቢያ መታሰራቸውን አክለዋል፡፡
130 ሰዎች ታስሮ እንደሚገኙ ጥቆማ እንደደረሰው ኢሰመጉ ገልጸዋል
በአሙሩ ወረዳ ከሰባት ወራት በፊት ታስረዋል የተባሉና ፍርድ ቤት አለመቅረባቸው የተነገረውን ሰዎች አስመልክቶ ማብራሪያ የጠየቅናቸው የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኮማንደር ዳባሳ ጉዳዩ በወረዳው የተቋቋመውን ኮማንድ ፖስት የሚመለከት ነው በማለት ስልካቸውን ዘግተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በበኩሉ በጉዳዩ ላይ ጥቆማ እንደደረሰው ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የጅማ ቅርንጫፍ ኃላፊ አቶ በዳሳ ለሜሳ 130 ሰዎች በጸጥታ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በአሙሩ ወረዳ ለሰባት ወራት መታሰራቸውንና ክትትል እያደረጉ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
‹‹ ጥቆማ ቀርቦልናል ጉዳዩን ተቀብለን እየተከታተልን እንገኛለን፡፡ የአሙሩ ወረዳን አስመልክቶ 130 ሰዎች ለ7 ወራት ታስሮ ይገኛሉ የሚል ጥቆማ ደርሶናል፡፡ በሚቀጥለው ሰኞ በጉዳዩ ላይ ከዞን አስተዳደር ጋር ቀጠሮ ተይዘዋል፡፡ ዝርዝር መረጃዎችን ከሰኞ በኃላ ይሰጣል፡፡» በአሙሩ ወረዳ በታጣቂዎችና መንግስት ጸጥታ ሐይሎች መካከል ከዚህ ቀደም ለረጅም ጊዜያት ግጭቶች ሲከሰቱ ቆይተዋል፡፡ ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያይዘውም በርካታ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት ሲደርስ እንደነበር በተደጋጋሚ ተዘግበዋል፡፡
ነጋሳ ደሳለኝ
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ