በማዕድን ማውጫ ውስጥ የተቀበሩ ሰዎች እስካሁን መውጫ አላገኙም
ረቡዕ፣ የካቲት 6 2016
በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ወገል ጤና ከተማ አቅራቢያ በባህላዊ መንገድ የኦፓል ማዕድን በማውጣት ላይ በነበሩ ሰዎች ላይ መሬት ከተደረመሰባቸው ሳምንት ሊሞላቸው ነው። በማዕድን ማውጫ ስፍራ ተቀብረው የሚገኙ ወጣቶችን ለማውጣት የሚደረገው ጥረትም እስካሁን አለመሳካቱን ቤተሰቦቻቸው ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ዘመናዊ መሳሪያ ተጠቅሞ ማዕድን አውጭዎችን ለመታደግ የመልክዓ ምድሩ አቀማመጥ አስቸጋሪ ማድረጉን የአካባቢው አስተዳደር አስታውቋል።
በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ወገል ጤና ከተማ አቅራቢያ በባህላዊ መንገድ የኦፓል ማዕድን በማውጣት ላይ በነበሩ ሰዎች ላይ መሬት ከተደረመሰባቸው ሳምንት ሊሞላቸው ነው። በማዕድን ማውጫ ስፍራ ተቀብረው የሚገኙ ወጣቶችን ለማውጣት የሚደረገው ጥረትም እስካሁን አለመሳካቱን ቤተሰቦቻቸው ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ዘመናዊ መሳሪያ ተጠቅሞ ማዕድን አውጭዎችን ለመታደግ የመልክዓ ምድሩ አቀማመጥ አስቸጋሪ ማድረጉን የአካባቢው አስተዳደር አስታውቋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች ዛሬ ለዶይቼ ቬሌ እንደተናገሩት ካለፈው ሐሙስ ሌሊት ጀምሮ የኦፓል ማዕድን ቁፋሮ ለማድረግ 700 ሜትር ያህል ርዝመት ባለው ዋሻ ውስጥ በቁፋሮ ላይ እንዳሉ 20 ያህል ወጣቶች በናዳ ተቀብረዋል፡፡ ወጣቶቹን በቁፋሮ ለማውጣት እየተደረገ ያለው ስራም እስካሁን ውጤት እያስገኘ እንዳልሆነ ከተጎጂ ቤተሰቦች የአክስታቸው ልጅ በናዳው ጉዳት የደረሰባቸው አስተያየት ሰጪ አመልክተዋል፡፡
በቁፋሮው ወቅት ሌላ ናዳ እየተፈጠረና በሰዎች ላይ ሌላ ጉዳት ሊያስከትል በመሆኑ ቁፋሮው ትናንት ከሰዓት በኋላ ጀምሮ ተቋርጠዋል ብለዋል። በነፍስ አድን ስራው የመንግስት ሚና አልታየም ሲሉም ይከስሳሉ፡፡
“በሰው ኃይል ገብቶ የማውጣት ተስፋ ነበረ፣ ግን አልተቻለም፣ ቤተሰቡ የተዳፈነበት ሰው ፣ ከዚህ በፊት በቁፋሮ ላይ የነበሩና ቦታውን የሚያውቁትና የአካባቢው ሰው ነው ተጎጂዎችን ለማትረፍ እየቆፈረ የነበረ፣ እስካሁን ከመንግስት አካል ያገኘነው ድጋፍ የለም፣ ዘመናዊ መሳሪያ አስገብቶ የነብስ አድን ስራ ለማድረግ አይቻልም ቦታው አስቸጋሪ ነው” ብላዋል፡፡
የእህታቸው ልጅ የአደጋው ተጠቂ እንደሆነ የገለጡልን ሌላዋ የወገል ጤና ነዋሪ ብዙ ሰዎች የተዳፈኑ ሰዎችን በቁፋሮ ለማውጣት ጥረት ቢያደርግም እስካሁን ምንም ፍንጪ እንደሌለ ተናግረዋል፣ አሁን እየተደረገ ያለው ቁፋሮ ሌላ የናዳ አደጋ እየፈጠረ በመሆኑ በነፍስ አድን ስራው ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ቁፋሮው መቆሙን አመልክተዋል፣ መንገስት ሌላ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲያመጣም ጠይቀዋል፡፡በማዕድን ቁፋሮ አፈር የተናደባቸዉ ከ20 በላይ ሰዎች እስካሁን አለመገኘታቸዉ
የደላንታ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አያሌው በሪሁን አደጋ የደረሰበት ዋሻ ከ13 ዓመታት ጀምሮ ሲቀፈር የኖረና ከ700 ሜትር በላይ ርዝመት ያለው ዋሻ ነው ብለዋል፣ ለአደጋው መንስኤ የሆነውም በዋሻው ውስጥ ለውስጥ የላይኛውን የመሬት ክፍል እንደምሰሶ ሆነው የሚያገለግሎ ቋሚዎች በመደርመሳቸው ነው ብለዋል፡፡
“መንግስት እገዛ አላደረገም” የሚለውን ክስ የተቃወሙት አቶ አያሌው አደጋው ከደረሰበት ጊዜ ጀምሮ የአካባቢው አስተዳደር ህብረተሰቡን እያስተባበረ ሲያግዝ መቆየቱን ገልጠዋል፡፡ ላለፉት 6 ቀናት አደጋው የደረሰባቸውን ሰዎች ከጉድጓዱ ለማውጣት ጥረት ሲደረግ ቢቆይም እስካሁን የተጨበጠ ነገር የለም ነው ያሉት፣ አሁን ባለው ሁኔታ በነብስ አድን ስራው ላይ የተሰማሩ ሰዎችን ሌላ ናዳ ጉዳት ሊያደርስባቸው ይችላልና ሌላ አማራጭ ይፈለግ የሚል ትያቄ በመምጣቱ ከሚመለከተው አካል ጋር እየተነጋገርን ነው ሲሉ አመልክተዋል፡፡ አካባቢው ለቁፋሮ መሳሪያ አመቺ ባለመሆኑ ያን ማድረግ እንዳልተቻለም ተናግረዋል፡፡
“የወረዳው መንግስትም፣ ሌሎቻችንም፣ እንደሰማን ርብርብ እያደረግን ነው፣ ግን እስካሁን መውጣት አልቻሉም፣ ቦታው ምንም ዓይነት ዘመናዊ የመቆፈሪያ መሳሪያዎችን ማስገባት አይችልም፣ እየሰራን ያለን በሰው ጉልበት ነው፣ በአንዴ 50 ሰዎች ገብተው ይቆፍራሉ፣ እኛ ምግብና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን እያቀረብን ነው፣ ማህበረሰቡም ወጣቱም ተሳታፊዎች ናቸው፡፡”በለገደንቢ ወርቅ ማውጫ የጤና እክል እያስከተለ ነው የተባለው ብክለት
እንደዋና አስተዳዳሪው በናዳው ውስጥ ባሉ ወገኖች በኩል ምንም መረጃ የለም፣ ድምጽም ሆነ ሌላ የሚሰማ ነገር የለም ነው ያሉት፡፡
“አሁን በቁፋሮ ላይ እያሉ የላይኛው መሬት ጫና እያደረሰ በመሆኑ፣ ለመቆፈር ችግር ፈጥሯል፣ ሌሎች አማራጮችን ለመፈለግ ከሚመለከተው አካል ጋር እየተናጋገርን ነው፡፡” ብለዋል፡፡ “ተጎጂዎች እስካሁን ያሉበት ሁኔታ ምንም የሚታወቅ ነገር የለም፣” ሲሉም አክለዋል፡፡
ከሁለት ዓመታት በፊት በተመሳሳይ ቦታ በማዕድን ቁፋሮ ላይ የነበረ ወጣት በናዳ ተይዞ ከ11 ቀናት በኋላ በቁፋሮ በህይወት መገኘቱን አቶ አያሌው አስታውሰዋል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ታምራት ዲንሳ
እሸቴ በቀለ