1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በማዕድን ቁፋሮ አፈር የተናደባቸዉ ከ20 በላይ ሰዎች እስካሁን አለመገኘታቸዉ

ሰኞ፣ የካቲት 4 2016

በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ወገል ጤና ከተማ አቅራቢያ በባህላዊ ማዕድን ቁፋሮ ላይ የነበሩ ከ20 እስከ 30 የሚደርሱ ወጣቶች ባለፈው ሐሙስ ሌሊት ናዳ ተደርምሶ ጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ በመግባታቸው የወጣቶቹ ህይወት ምን ላይ እንዳለ እንደማይታወቅ የአካባቢው ነዋሪዎች አመለከቱ፡፡ ወጣቶቹን በማሽን በታገዘ ቁፋሮ ማውጥት እንዳልተቻለም።

https://p.dw.com/p/4cJfA
ወሎ መስመር ኢትዮጵያ
ወሎ መስመር ኢትዮጵያ ምስል Seyoum Getu/DW

አደጋው የደረሰባቸው ከ20 እስከ 30 የሚገመት ወጣቶች ናቸው

በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ወገል ጤና ከተማ አቅራቢያ በባህላዊ ማዕድን ቁፋሮ ላይ የነበሩ ከ20 እስከ 30 የሚደርሱ ወጣቶች ባለፈው ሐሙስ ሌሊት ናዳ ተደርምሶ ጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ በመግባታቸው የወጣቶቹ ህይወት ምን ላይ እንዳለ እንደማይታወቅ የአካባቢው ነዋሪዎች አመለከቱ፡፡ ቦታው እጅግ አስቸጋሪ በመሆኑ ወጣቶቹን በማሽን በታገዘ ቁፋሮ ማውጥት እንዳልተቻለም ነዋሪዎቹ ገልጠዋል፡፡

በክልሉ ደቡብ ወሎ ዞን ወገልጤና ከተማ አቅራቢያ ልዩ ስሙ “ቆቅ ውሀ” ከተባለ አካባቢ በባህላዊ መንገድ “ኦፓል” የተባለ ማዕድን በቁፋሮ ለማውጣት ተሰማርተው የነበሩ ወጣቶች ባለፈው ሐሙስ ሌሊት የአለት ናዳ በላያቸው ላይ በመደርመሱ እስከ 700 ሜትር ጥልቀት ባለው ጉድጓድ ውስጥ መግባታቸውንና በህይወት የመኖር እጣፋንታቸው እናደማይታወቅ አንድ የወገል ጤና ከተማ ነዋሪ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡ “ ቆቅ ውሀ የሚባለው ነው፣ ከከተማዋ ዳር ገደል አለ፣ ከ 700 ሜትር በላይ የሆነ ዋሻ ነው፣ ሐሙስ እለት እየቆፈሩ እሉ ቁጥራቸው ከ20 እስከ 30 የሚገመት ወጣቶች ናቸው አደጋው የደረሰባቸው፡፡ ”
እኚሁ ቦታው ላይ የሚገኙ ነዋሪ እንደሚሉት ቦታው አስቸጋሪ በመሆኑ ቁፋሮውንና ነብስ የማዳን ሥራውን ከባድ አድርጎታል ነው ያሉት፡፡ “ ቦታው አስቸጋሪ በመሆኑና በርከት ያለ ሰው በአንዴ መቆፈር ባለመቻከሉ አሁን የተቆፈረው ከ50 ሜትር አይበልጥም፣ ... ከቦታው አንፃር ማሽን ለማስገባትም አይቻልም፣  ምናልባት አየር ሊያጥራቸው ይችላል፣ በህይወት ለማግኘት የሚደረገው ተስፋ ከበድ ይላል ”
የደቡብ ወሎ ዞን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ በማዕድን ጉድጓድ ውስጥ የገቡ ሰዎችን ቁጥር እስከ 20 እንደሚገመት ባሰራጨው ዘገባ አመልክቷል፣ አንድ ሌላ የወገል ጤና ከተማ ነዋሪ አደጋው በከተማዋ አቅራቢያ መፈጠሩን ጠቅሰው፣ በቁጥሩ ላይ አንድ ወጥ መረጃ እንደሌለ ነው የተናገሩት፣ እንደርሳቸው በጉድጓዱ ውስጥ የገቡት ከ9 ኤበልጡም፣ በእርግጥ ሰው የጠፋባቸው ሰዎች እየመጡ ሪፖርት እያደረጉ በመሆኑ ከፍ ሊል እንደሚችል ገልጠዋል፡፡ በሰው ቁፋሮ ሰዎችን ለማውጣት ከባድ መሆኑን ያመለከቱት እኚሁ ነዋሪ መንግስት ባፋጣኝ ሌላ ነብስ አድን ስራ እንዲሰራ ጠይቀዋል፣ እንደ አስተያየት ሰጪው አሁን ያለው የነብስ አድን ስራ ሌላ አደጋ ሊያመጣ ይችላል የሚል ስጋት አላቸው፡፡ቁፋሮው ሌላ ናዳን ሊያስከትል የሚችልበት አጋጣሚ መኖሩን አስረድተዋል፡፡
ሌላ በቁፋሮው ላይ የነበሩ አስተያየት ሰጪ አጠቃላይ እስካሁን የተደረገው ቁፋሮ ውጤት የሌለውና ተስፋ አስቆራጭ እየሆነ መጥቷል ብለዋል፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪው ቁፋሮው በግምት ነው የሚደረገው፣ ሰዎች ያሉበትን ትክክለኛ ቦታ የሚያሳይ አይደለም፣ ፍለጋው ተስፋ አስቆራጭ መሆኑን ነው ያመለከቱት፡፡ ህብረተሰቡ የሚችለውን እደረገ ነው፣  ይቆፈፍራል፣ ሌለው ደግሞ በየቦታው ተቀምጦ እያለቀሰ ነው ነው ያሉት፡፡
የባለቤታቸው ወንድም የአደጋው ተጠቂ እንደሆነ የሚናገሩ አንድ ሌላ አስተያየት ሰጪም አስተያየታቸውን ጠይቀናቸው ነበር፡፡ “ሰዎቹ ጉድጓድ ውስጥ እንዳሉ ቁፋሮው እየተካሄደ ነው፣ መሬቱ ወደ ታች የመንሸራተት ባሕሬ አለው፣ እስካሁን እዛው ውስት ናቸው ከገቡበት እለት ጀምሮ እስካሁን የተገኘ ነገር የለም” ብለዋል፡፡ ከዚህ በፊት በቦታው ይሰሩ የነበሩ ሰዎች የተናገሩትን “በዋሻው ውስጥ ውሀ አለ፣ በመሆኑም ውሀ እየጠጡ ህይወታቸውን ያቆያሉ” የሚል ተስፋ ተደርጎ ቁፋሮው እየተካሄደ መሆኑን ቢጠቅሱም ድምፅም ሆነ በህይወት ስለመኖራቸው የሚያመለክት አንዳችም ነገር የለም ሲሉ ነው አስተያየታቸውን የሰጡን፡፡ የደቡብ ወሎ ዞን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮችመመምሪያ እንደሚለው ወጣቶቹን ለማትረፍየፋሮ ስራ በርብርብ እየተሰራ ነው፡፡

ዓለምነው መኮንን
አዜብ ታደሰ 
እሸቴ በቀለ