1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሰላምና ደኅንነትን ለማስፈን ጉልህ ጥሪ የቀረበበት የአፍሪቃ ኅብረት ጉባኤ

ሰኞ፣ የካቲት 11 2016

ሰላምና ደኅንነትን ለማስፈን ጉልህ ጥሪ የቀረበበት የአፍሪቃ መሪዎች ጉባኤ እሑድ ምሽቱን ተጠናቋል። የአፍሪቃ ሕብረት የሰላምና ደኅንነት ኮሚሽን አፍሪቃ ውስጥ ያለው የሰላም እና የፀጥታ ሁኔታ እንዲሁም የፖለቲካ አስተዳደር አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ይገኛል ብሏል።

https://p.dw.com/p/4cZbk
37ተኛው የአፍሪቃ ሕብረት ጉባኤ
አዲሱ የሕብረቱ ሊቀመንበር የሞሪታኒያው ፕሬዝዳንት ሞሃመድ ዑልድ በአፍሪቃ ሰላምን ለማስፈን እና አለመግባባቶችን ለመፍታት ጥረታችንን አጠናክረን መቀጠል አለብን ብለዋል።ምስል MICHELE SPATARI/AFP

የተጠናቀቀው የአፍሪቃ ሕብረት ጉባኤ

አፍሪቃ ውስጥ ያለው የሰላም እና የፀጥታ ሁኔታ እንዲሁም የፖለቲካ አስተዳደር አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ይገኛል ሲል የአፍሪቃ ሕብረት የሰላምና ደኅንነት ኮሚሽን ትናንት ማምሻውን ገለፀ። 37ኛው የአፍሪቃ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ሲጠናቀቅ በክፍለ ዓለሙ ሽብርተኝነት፣ ጽንፈኝነት፣ አክራሪነት፣ ድንበር ተሻጋሪ ዓለም አቀፍ የተደራጀ ወንጀል፣ አመፀኝነት እና መሰል ሥርዓት አልበኝነቶች ዳግም በማንሰራራት ላይ መሆናቸው ተጠቅሳል። አዲሱ የሕብረቱ ሊቀመንበር በአፍሪቃ ሰላምን ለማስፈን እና አለመግባባቶችን ለመፍታት ጥረታችንን አጠናክረን መቀጠል አለብን ብለዋል።

የአዲሱ የሕብረቱ ሊቀመንበር ተጨባጭ የሰላም ጥሪ

ትናንት የካቲት 10 ቀን 2016 ዓ.ም ከእኩለ ሌሊት በኋላ የተቋጨው 37 ኛው የአፍሪቃ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ አዲሱ የሕብረቱ ሊቀመንበር የሞሪታኒያው ፕሬዝዳንት ሞሃመድ ዑልድ ሰላምና ደኅንነትን በተመለከተ ከንግግር ባለፈ ተጨባጭ ሥራ እንደሚያስፈልግ በገለፁበት አጭር መግለጫ ተጠናቋል። «ሰላምን ለማስፈን እና አለመግባባቶችን ለመፍታት ጥረታችንን አጠናክረን መቀጠል አለብን። አህጉራችን በአለም አቀፍ ደረጃ ውክልና እንዲኖረው ማድረግን በማጠናከር እና በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖረው ብሎም የዓለም አቀፍ የሰላም ቅርጽ ማሻሻያን ማረጋገጥ፣ ፍትኃዊ ሥርዓት እንዲኖር ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው። ሁላችንም የምንፈልገው አፍሪቃ ማለትም ሰላምና መረጋጋት፣ ሰብዓዊ መብቶች፣ መልካም አስተዳደር፣ እና ዘላቂ ልማት ያለው እንዲሁም የራሷን እጣ ፈንታ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚኖራት ማድረግ ከምርጫዎች መካከል ያለ ምርጫ ብቻ አይደለም። ይልቁንም አስፈላጊና የህልውና ጉዳይ እንጂ።» በማለት ተናግረዋል።

የአፍሪቃ ሕብረት አርማ
የአፍሪቃ ሕብረት አርማምስል Ludovic Marin/AFP/Getty Images

የሕብረቱን የሰላምና ደኅንነት ኮሚሽን ያሳሰበው የሰላም ጉዳይ 

ከዚህ አስቀድሞ የአሕጉሩን ሰላምና ደኅንነት በተመለከተ መግለጫ የሰጡት የሕብረቱ የፖለቲካ ፣ የሰላም እና ደኅንነት ኮሚሽነር ባንኮሌ አዶዬ አሳሳቢ የፀጥታ ችግር መኖሩን አመልክተዋል።

«በአፍሪቃአህጉር ያለው የሰላም እና የፀጥታ ሁኔታ፣ የፖለቲካ አስተዳደር አሳሳቢ ነው። አልፎ ተርፎም የሽብርተኝነት ፣ የጽንፈኝነት ፣ የአክራሪነት ፣ የድንበር ተሻጋሪ አለም አቀፍ የተደራጁ ወንጀሎች ፣ የአመፀኝነት ዳግም ማንሰራራት በአህጉሩ ተስፋፍቷል። እናም እነዚህ ስጋቶች እና ውጥረቶ በበርካታ የአህገሩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ በመሆኑ መፍታት አስፈላጊ ነው ።»

 

ስለ ጉባኤው የአለም አቀፍ ሕግና የዲፕሎማሲ ጉዳዬች ተንታኝ አስተያየት

ራሳቸውን ኢ- ዴሞክራሲያዊ አካሄድ ውስጥ ከተዋል የተባሉ ስድስት ሃገራት ከሕብረቱ መታገዳቸው በመሪዎቹ ጉባኤ ማብቂያ ላይ ተገልጿል። ይህ ብቻውን መፍትሔ አንዳልሆነ የሚከራከሩት ስማቸውን ትተን ሀሳባቸውን እንድንጠቅስ የጠየቁን አንድ የዓለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ተንታኝ የሕብረቱ አካሄድ ላይ ጥያቄ ያነሳሉ።

ተንታኙ አክለውም አፍሪካ ከኢኮኖሚ ዕድገት አስቀድሞ ሰላምና ድኅንነቱን ማስጠበቁ የላቁ እንደሚበጀው ገልፀው አሕጉሩ ተጨባጭ የፀጥታ ችግር ውስጥ ሆኖ ሳለ መሪዎቹ በየዓመቱ ከመሰብሰብ ባለፈ ችግሩን የሚፈታ መፍትሔ ሲያመላክቱ አለመስተዋሉን አመልክተዋል።

የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሀሰንሼህ ሞሀሙድ በአፍሪቃ ኅብረት ጉባኤ
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼሕ ሞሐሙድ የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች ውይይቱ ወደሚካሄድበት ሥፍራ እንዳልገባ የመከልከል ሙከራ አድርገውብኛል ቢሉም ኢትዮጵያ ክሱን አስተባብላለች። ምስል MICHELE SPATARI/AFP

የሶማሊያ ክስ የኢትዮጵያ ምላሽ እና የተስተዋለው ውዝግብ 

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ያስገኝልኛል ያለችውን የመግባቢያ ስምምነት ተከትሎ ውዝግብ ውስጥ የገቡት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በዚህ የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ተጨማሪ መነጋገሪያ ሆነው ነበር። በተለይም የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼሕ ሞሐሙድ የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች ውይይቱ ወደሚካሄድበት ሥፍራ «እንዳይገቡ ለመከልከል» ሙከራ ተደርጎባቸው እንደነበር ገልፀው ክስ ያሰሙ ሲሆን ክሱ የተሳሳተ መሆኑን የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ትናንት አስታውቀዋል።

በጉባኤው መጀመርያ ዕለት የሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር በአፍሪቃ የአንድነት፣ የትብብር እና የአፍሪካዊ ስሜት መቀዛቀዝ መኖሩን ጠቁመው ነበር። የጉባኤው አስተናጋጅ ኢትዮጵያ የመሪዎቹ ጉባኤ በሰላም መጠናቀቁን አስታውቃለች። 

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ