1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአፍሪቃ (ሕብረት) አንድነት ድርጅት 60ኛ ዓመት

ሐሙስ፣ ግንቦት 17 2015

አፍሪካ ሕብረት ከጊዜ ወደ ጊዜ የተለጠጠ እቅድ በመያዙ ምክንያት ውጤታማ ሥራዎችን ማከናወን ተስኖት የእርስ በርስ ጦርነት እና ግጭት ፣ የመንግሥታት ግልበጣዎች፣ ሙስና ፣ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ውህደት መፍጠር እንደተሳነው እየተደጋገመ ይነሳል

https://p.dw.com/p/4Ros2
Äthiopien 60. Jahrestag der Afrikanische Union (AU)
ምስል Solomon Muchie/DW

የአፍሪቃ (ሕብረት) አንድነት ድርጅት ስኬትና ዉድቀት

ባሁኑ ወቅት የአፍሪቃ ሕብረት ተብሎ የሚጠራዉ የአፍሪቃ መንግስታት የጋራ ማሕበር የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት (አአድ) በሚል ስም አዲስ አበባ ላይ ከተመሰረተ ዘንድሮ ግንቦት  60ኛ ዓመቱን ደፍኗል።ድርጅቱ ወይም ሕብረቱ የተመሠረተበት በዓል ዋና ፅሕፈት ቤቱ በሚገኝበት አዲስ አበባ በተለያዩ ድግስና ሥርዓቶች ዛሬ እየተከበረ ነዉ።የሕብረቱ ከግማሽ ክፍለ ዘመን የተሻገረ እንቅስቃሴ የተመሠረተበትን በተለይ ቅኝ አገዛዝን የመታገል ግብ ማሳካቱን የሕብረቱ መሪዎችም፣ ያነጋገርናቸው የፖለቲካ ተንታኝም ገልፀዋል።

ይሁንና አፍሪካ ሕብረት ከጊዜ ወደ ጊዜ የተለጠጠ እቅድ በመያዙ ምክንያት ውጤታማ ሥራዎችን ማከናወን ተስኖት የእርስ በርስ ጦርነት እና ግጭት ፣ የመንግሥታት ግልበጣዎች፣ ሙስና ፣ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ውህደት መፍጠር እንደተሳነው እየተደጋገመ ይነሳል።በዛሬው የሕብረቱ 60ኛ ዓመት የምሥረታ ሥነ ሥርዓት ላይ አፍሪካ በተባበረት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና እንዲኖረው፣ ጂ 7 እና ጂ 20 በሚባሉት የበለፀጉት ሀገራት ስብስቦች ውስጥም ተሳትፎ እንዲኖረው ተጠይቋል።

Äthiopien 60. Jahrestag der Afrikanische Union (AU)
ምስል Solomon Muchie/DW

በግሪጎሪያኑ መስከረም 1999 ዓ.ም ሊቢያ ሲርት ከተማ ውስጥ በተደረሰ የስምምነት ስያሜው ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪካ ሕብረት የተለወጠው አህጉራዊው የአንድነት ድርጅት ዛሬ የተመሰረተበት 60 ኛ ዓመት አዲስ አበባ ሳርቤት በሚገኘው ዋናው መሥሪያ ቤቱ የሕብረቱ መሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ሌሎችም እንግዶች በተገኙበት ተከብሯል።

አፍሪካዊ አንድነትን በማቀንቀን አዲስ አበባ ውስጥ የተቋቋመው ይህ ድርጅት ከበርሊን አፍሪካን የመቀራመት ጉባኤ ማግስት የተፈጠረውን ቅኝ አገዛዝ የመጣል፣ የአፓርታይድ እና የነጭ የበላይነት የሰፈነበትን የኢምፔሪያሊዝም ሥርዓት የመታገል ግብ ይዞ የተቋቋመ ነበር።
60ኛው የምሥረታ በዓሉ ሲከበርም ድርጅቱን የመሠረቱት የአህጉሩ አባት የሚባሉት መሪዎች ተመስግነውበታል።

የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት መስራቾች በከፊል
የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት መስራቾች በከፊልምስል Solomon Muchie/DW

አፍሪቃ ውስጥ የእርስ በርስ ጦርነት ፣ የመንግስት ግልበጣ ፣ የትምህርት አለመስፋፋትና የከፋ ድህነት፣ የሽብር ጥቃቶች፣ የውጭ ኃያላን የገንዘብ ጥገኝነትና የቀጥታም ሆነ የተዘዋዋሪ ተጽዕኖ ሰልባ መሆን አህጉሩ እየተፈተነበት የሚገኙ ችግሮች መሆናቸው በዛሬው ክብረ በዓል ላይ ተነግሯል።
የሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህመትም ይህንን አልሸሸጉም። ይልቁንም አፍሪካ በ2020 የጥይት ድምፅ የማይሰማበት እንዲሆን ይደረጋል በሚል ተለጥጦ የታቀደውን ግብ ሕብረቱ መፈፀም ተስኖት እቅዱ ስለመከለሱ አብራርተዋል።
"ዛሬ እዚህ የሕብረቱ ኔልሰን ማንዴላ አዳራሽ ውስጥ በተሰባሰብንበት ወቅት ብዙዎቹ የሕብረቱ አባል ሀገሮቻችን በውስጥ ግጭት ምክንያት ቀውስ ውስጥ ናቸው። አግባብነት የሌላቸው የስልጣን ጥያቄዎች የበርካቶችን ሕይወት እየቀጠፉ ነው።" ብለዋል።
የፖለቲካ እና ማህበራዊ ጉዳይ መከፋፈሎች አደጋ ደቅነዋል ያሉት ሊቀመንበሩ የሽብርተኝነት መስፋፋት፣ የታጠቁ ኃይሎች መበራከት ከተፈጥሮ አደጋዎች ጋር ተዳምረው አህጉሩን እየፈተኑት መሆኑን ገልፀዋል።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የዓለም አቀፍ ሕግ እና የፖለቲካ ጉዳዮች ዐዋቂ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት  የቀደመውን ይዞት የተነሳውን ግልጽ ዓላማውን አሳክቷል ይላሉ።
ይህ ሲባል ግን አህጉራዊ ተቋሙ በተለይ ባለፉት 24 ዓመታት የአፍሪካ ሕብረት ከተባለ ወዲህ ለ 2063 አሳካለሁ ብሎ የነደፋቸው የተለጠጡ እቅዶቹ ስኬታማነቱን እንገቱት፣ እቅዶቹንም በአግባቡ የማይፈጽም እና ከውጪ ጥገኝነት ያልተላቀቀ እንዲሆን አድርጎታል በማለት ተቋማዊ አቅሙ ደካማ መሆኑን ተናግረዋል።
አፍሪካ በተባበረት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና እንዲኖረው፣ ጂ 7 እና ጂ 20 በሚባሉት የበለፀጉት ሀገራት ስብስቦች ውስጥም ተሳትፎ እንዲኖረው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጠይቀዋል። በፍጥነት እየተለዋወጠ በሚገኘው የዓለም ሥርዓተ ትድድር ውስጥ አንድነት የመኖር እና ያለመኖር የህልውና ጉዳይ ነው የሚል መልእክትም አስተላልፈዋል።
"ለአፍሪካ ትኩረት መስጠት ማለት በ2050 ለአንድ ተመሳሳይ ሕዝብ መኖሪያ ለሚሆን አህጉር ትኩረት መስጠት ማለት ነው"
ነው ያሉት 
በቻይና መንግሥት ድጋፍ የታነፀው የአፍሪካ ሕብረት ዋና መሥሪያ ቤት ሽቅብ 99.9 ሜትር ይረዝማል።ቁጥሩ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ስያሜ ወደ አፍሪካ ሕብረት የተለወጠበት ድንጋጌ የፀደቀበትን በ1999 በሊቢያዋ ሰርት ከተማ የተፈረመውን ድንጋጌ ወይም ዲክላሬሽንን ታሳቢ ያደረገ ነው። 

የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት መስራቾች በከፊል
የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት መስራቾች በከፊልምስል Solomon Muchie/DW

 ሰለሞን ሙጬ 

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ