1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፍትሕ ለትግራይ ሴቶች፥ ሰልፍ በመቐለና ሌሎች ከተሞች

ማክሰኞ፣ ሰኔ 18 2016

በትግራይ ክልል ሴቶች ላይ የሚደርሰው አሳሳቢ ጾታዊ ጥቃት እና ግድያ ብርቱ ቁጣን ቀስቅሷል ። የሴቶች መደፈር፤ መታገት ብሎም ግድያን በመቃወም ዛሬ በመቐለ ሰልፍ ተካሂዷል።

https://p.dw.com/p/4hUAF
 IDPs in Tigray held protests  across six cities in the region
ምስል Million Hailesilassie/DW

«ፆታ ተኮር ጥቃት ይቁም» የሚል መፈክር ተስተጋብቷል

በትግራይ ክልል ሴቶች ላይ የሚደርሰው አሳሳቢ ጾታዊ ጥቃት እና ግድያ ብርቱ ቁጣን ቀስቅሷል ። የሴቶች መደፈር፤ መታገት ብሎም ግድያን  በመቃወም ዛሬ በመቐለ ሰልፍ ተካሂዷል። ህፃናት፣ ወጣቶች እና እናቶች ሰልፉ ላይ በመገኘት በትግራይ ክልል በሴቶች ላይ እየደረሰ ነው ያሉትን በደል አውግዘዋል ። የጥቃቱ ሰላባ ቤተሰቦችም ፍትሕ ጠይቀዋል።

«ፍትህ ለትግራይ ሴቶች» ፣ «ፆታ ተኮር ጥቃት ይቁም» ፣ "የሴቶች ድህንነት የሚያረጋግጥ የመንግስት ተቋማት ይፍረሱ" የሚሉና ሌሎች መፈክሮች በስፋት የተስተጋቡበት ዛሬ በመቐለ የተካሄደው ሰልፍ፥ የጥቃቱ ሰለባ ቤተሰቦች፣ ህፃናት ሴት ተማሪዎች እንዲሁም የጥቃቱ አሳሳቢነት ለመቃወም የመጡ በርካቶች ተገኝተውበታል።

በሰልፉ ፍትህ የሚጠይቁ በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች የተሳተፉ ሲሆን፥ በቅርቡ ብቻ በተለያዩ ከተሞች የታገቱ፣ የተገደሉ ሴቶች ስም እያነሱ ፍትህ ጠይቀዋል፣ የመንግስት ቸልተኝነት ወቅሰዋል። ከሰልፈኞቹ መካከል የተወሰኑት አነጋግረናል።

አስታየትዋ የሰጠችን የሰልፉ ተሳታፊ ሚልዮን ገብረማርያም "በጦርነቱ ግዜ በርካታ ሴቶች ተደፍረዋል፣ ተገድለዋል። አሁን ላይ ይህ ይቆማል ብለን ስንጠብቅ በራሳችን ወንድሞች እየተጠቃን ነው። ሴቶች ወጥቶ መግባት የማይችሉ ሁኔታ እየታየ ነው" ብላለች። ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ሳሮን ሃይለስላሴ በበኩልዋ "መንግስት እርምጃ እየወሰደ አይደለም፣ ለውጥ እያየን አይደለም። ፍትህ እንፈልጋለን" ብላለች።

ሰልፈኞቹ ከመቐለ ሮማናት አደባባይ ተነስተው ጥያቄአቸው ለማቅረብ ወደ ፕሬዝደንት ጽሕፈት ቤት አቅንተዋል
ሰልፈኞቹ ከመቐለ ሮማናት አደባባይ ተነስተው ጥያቄአቸው ለማቅረብ ወደ ፕሬዝደንት ጽሕፈት ቤት አቅንተዋልምስል Million Hailesilassie/DW

ሰልፈኞቹ ከመቐለ ሮማናት አደባባይ ተነስተው ጥያቄአቸው ለማቅረብ ወደ ፕሬዝደንት ጽሕፈት ቤት ያቀኑ ሲሆን በቦታው ከአስተዳደሩ ተወካይ ምላሽ ተሰጥቷቸዋል። ለሰልፈኞቹ የተናገሩት የትግራይ ፍትህ ቢሮ ሐላፊ አቶ ሓዱሽ ተስፋ አስተዳደራቸው በትግራይ እየተታዩ ያሉ ፆታ ተኮር ጥቃቶች እንደሚያወግዝና ርምጃዎች እየወሰደ መሆኑ ገልፀዋል።  ሐላፊው "የተወሳሰበ ችግሮች እንኳን ቢኖሩብን፣ የሴቶች ጥቃት ግን ለነገ የሚባል፣ ይቆይ የሚባል አይደለም። ይህ ጥቃት ለማስቆም የሚያስችል የተለያዩ ውሳኔዎች መንግስት ወስኖል። በቅርቡ ደግሞ የዚህ ማሳያ የሚሆን እርምጃዎች ይገልፃሉ። ያቀረባችሁት ጥያቄ ልክ ነው፣ እየደረሰ ያለው ጥቃት ግልፅ ነው። ፍፁም ተቀባይነት የለውም። እንደ መንግስት ጥያቄአችሁ ምሬታችሁ ተቀብለናል" ብለዋል።

በቅርቡ ብቻ በመቐለ፣ ዓድዋ፣ ዓዲግራት እና ሌሎች ከተሞች ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ሴቶች መደፈራቸው፣ መታገታቸው እንዲሁም በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለው መገኘታቸው በማንሳት በርካቶች ይህን ወንጀል መንግስት እንዲያስቆም ጫና በመፍጠር ላይ ናቸው።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ