1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፌስቡክ እና ተለዋዋጭ ስልተ-ቀመሮቹ

ረቡዕ፣ ግንቦት 2 2015

በጎርጎሪያኑ 2004 ዓ/ም ማርክ ዙከርበርግን ጨምሮ በአራት ሀርቫርድ ዩንቨርሲቲ ተማሪዎች አሜሪካ ውስጥ የተመሰረተው ፌስቡክ፤በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ 2.7 ቢሊዮን ሰዎች በየወሩ ይታደሙታል።ያም ሆኖ ፌስቡክ ተፈላጊ ሆኖ ለመቆየት በየጊዜው የስልተቀመር ማሻሻያዎችን በማድረግ ላይ ይገኛል።

https://p.dw.com/p/4R8Py
Facebook
ምስል Richard Drew/AP/picture alliance

የቲክቶክ ተቀባይነት በፌስቡክ ስልተ-ቀመር ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል



በጎርጎሪያኑ 2004 ዓ/ም ማርክ  ዙከርበርግን ጨምሮ በአራት  ሀርቫርድ ዩንቨርሲቲ  ተማሪዎች  አሜሪካ ውስጥ የተመሰረተው ፌስቡክ፤በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ  2.7 ቢሊዮን ሰዎች በየወሩ  ይታደሙታል። በትሪሊዮን የሚቆጠሩ ይዘቶችም በዚሁ  አውታረ መረብ  ላይ ይለጥፋሉ። ይህ ቁጥር  ይዘቶቻቸውን ለታዳሚያን ለሚያቀርቡ የመረጃ ምንጮች እና የመዝናኛ ሰዎች፤ እንዲሁም ምርት እና አገልግሎቶቻቸውን ማስተዋወቅ ለሚፈልጉ የንግድ ሰዎችም ቢሆን በቀላሉ የሚታይ አይደለም። 
ነገር ግን፣ የሚፈለገው ታዳሚ ዘንድ ለመድረስ የፌስቡክ ስልተ ቀመርን /Algorithim/መገንዘብ ትልቁ ጉዳይ ነው። የሶፍትዌር ባለሙያው አቶ ሶሎሞን አይዳኝ እንደሚሉት የፌስቡክ ስልተ ቀመር ተጠቃሚዎች በፌስቡክ ገፆቻቸው የሚያዩትን ይዘት የሚወስኑ ህጎች እና ቀመሮች ስብስብ ነው።
የበይነመረብ / ኢንተርኔት/ መምጣትን ተከትሎ በጎርጎሪያኑ 1997 ዓ/ም አንድሪው ዋይንሪች በተባለ ሰው «ሲክስ ዲግሪስ» የተባለው የመጀመሪያው የትስስር ገፅ ተፈጥሯል።ይህ ገፅ እስከ 20003 ዓ/ም ታዋቂ የነበረ ሲሆን፤ ከነሀሴ 2003 ዓ/ም ጀምሮ ግን «ማይ ስፔስ» የተባለው የትስስር ገፅ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቴክኖሎጅ እና በፖፕ የሙዚቃ ባህል ትልቅ ተፅዕኖ አሳድሯል።ይህ የትስስር ገፅ እስከ 2017 ዓ/ም ገኖ የዘለቀ ቢሆንም ፌስቡክ የተጠቃሚዎችን ትክክለኛ ስምና ፎቶ በመያዝ የተለዬ መስተጋብር  በመፍጠር አሸናፊ ሆኖ ወጥቷል።
በአሁኑ ወቅት ደግሞ ፌስቡክን የሚገዳደሩ በርካታ የማህበራዊ ትስስር ገፆች አሉ።ከዚህ አኳያ ፌስቡክ ተፈላጊ ሆኖ ለመቆየት በየጊዜው የስልተቀመር ማሻሻያዎችን በማድረግ ላይ ይገኛል።
የዚህ ስልተቀመር ዓላማም ከእያንዳንዱ ተጠቃሚ በተሰበሰበው መረጃ መሰረት የትኛው ይዘት ለየትኛው የፌስቡክ ተጠቃሚ ይሆናል የሚለውን በመወሰን  ለተጠቃሚው  በጣም አስፈላጊ ናቸው ያላቸውን ልጥፎች በከፍተኛ ሁኔታ እንዲታዩ ማድረግ ነው።ይህም በአብዛኛው በሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ ተመስርቶ  የተጠቃሚዎችን ፍላጎት በማጥናት የሚከናወን ነው።
ይህንን ለማድረግም እያንዳንዱን ይዘት ይመረምራል ፣ይመዝናል  በደረጃም ያስቀምጣል።በዚህ ሁኔታ  የማሽን መማርን  /Machine Learning/ጨምሮ የተለያዩ ስልተቀመሮችን በመጠቀም፤ ለእያንዳንዱ ተጠቃሚ  ጠቃሚ ይሆናል የሚለውን ይዘት ይገምታል ይላሉ የሶፍትዌር ባለሙያው ኢንጅነር ይግረማቸው እሸቱ ።  
በዚህ ሁኔታ ፌስቡክ ከጎርጎሪያኑ 2017 ዓ/ም ጀምሮ በይዘቶች ደረጃ እና ስርጭት ላይ ጉልህ ለውጦችን በስልተ ቀመር ላይም ማሻሻያዎችን አድርጓል። በቀጣዩ ዓመት  በ2018 ዓ/ም የመስተጋብር ማሻሻያ  ያካሄደ ሲሆን፤  የዚህ  ዝማኔ ስልተቀመር  አንድ ተጠቃሚ ከጓደኞቹ  ጋር ስለየትኞቹ ልጥፎች መነጋገር እንደሚፈልግ የሚተነብይ እና እነዚህን ልጥፎች በተጠቃሚዎች ገፅ ላይ በከፍተኛ ድግግሞሽ በማሳየት  እንዲታዩ የሚገፋፋ  ነው። እነዚህ ልጥፎችም ተጠቃሚዎች እንዲያጋሩቸው  ምላሽ እንዲሰጡባቸው እና ውይይት እንዲያደርጉ የሚያነሳሱ ናቸው።
ሌላው የፌስቡክ የስልተቀመር ወይም /Algorithim/ ማሻሻያ በ 2019 ዓ/ም የተደረገ ሲሆን፤  ይህ ዝማኔ ተጠቃሚዎች የፈለጓቸውን እና መልስ የሚሰጡባቸውን እንዲሁም ተጠቃሚዎች  በአንድ ጊዜ  ከአንድ ደቂቃ በላይ የተመለከቱትን የቪዲዮ ልጥፎችን የበለጠ እንዲታዩ  የሚያበረታታበት ነው።  እነዚህ ቪዲዮዎች ቱባ ፈጠራዎች እና እንደገና ጥቅም ላይ ያልዋሉ ይዘቶች ያሏቸው እንዲሆኑም ይጠበቃል።
በ2020፣ ደግሞ ፌስቡክ  ትክክለኛ እና ተአማኒነት ላላቸው የዜና ምንጮች የበለጠ ክብደት ለመስጠት በሚል  በመስተጋብር ላይ የተመሰረተ ለተጠቃሚዎች የበለጠ ግላዊነትን የተላበሱ መመሪያወችን ለመፍጠር ስልተቀመሩን  እንደገና አሻሽሏል።በዚሁ አመትም «ፌስቡክ ሪልስ» የሚል ቪዺዮ ላይ የሚያተኩር ስልተቀመር አስተዋውቋል።ለዚህም እንደ ኢንጅነር ይግረማቸው የቲክቶክ በከፍተኛ ሁኔታ ተቀባይነት ማግኘት ተፅዕኖ አሳድሯል።
ምንም እንኳ ፌስቡክ በዚህ ሁኔታ የተለያዩ ማሻሻያዎችን ቢያደርግም  በአሁኑ ወቅት ቲክቶክ ከፌስቡክ የበለጠ ተጠቃሚን የመሳብ አዝማሚያ አለው። ለዚህም ባለሙያው መሰረታዊ ያሏቸውን ባህሪያት ያነሳሉ።
ያከሆነ ፌስቡክ ሙሉ በሙሉ የቲክ ቶክን መንገድ ይከተል ይሆን? ኢንጅነር ይግረማቸው እንደሚሉት ፌስቡክ እና ቲክቶክ መሰረታቸው የተለያዬ በመሂኑ ያ ሊሆን አይችልም። ነገር ግን ሜታ ተጠቃሚዎችን ለመሳብ ተለያዩ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በ2021 ፌስቡክ የተጠቃሚዎችን ገጽ የሚወስነው ስልተ ቀመር ተጠቃሚዎች በሚያዩት ነገር ላይ ያላቸውን የቁጥጥር መጠን ጨምሯል።30 የሚደርሱ ጓደኞችን እና ገጾችን በመምረጥም ልጥፎቻቸው በደረጃ  እንዲታዩ ለማድረግ የሚያስችል ዕድል ፈጥሯል። 
 በ2022 ዓ/ም  ስልተ ቀመሩን  ይበልጥ በማሻሽል  የተራቀቀ የሰው ሰራሽ አስተዉሎት አጠቃቀሙን ጨምሯል። በዚህም ተጠቃሚዎች በሚያዩት  በእያንዳንዱ ልጥፍ ላይ  ፍላጎቶቻቸውን ለመለየት የሚያስችል «የበለጠ ማየት እፈልጋለሁ» ወይም «ማየት አልፈልግም» የሚሉ አወንታዊ እና አሉታዊ ግብረመልስ እንዲሰጡ የሚያደርግ አማራጮችን አቅርቧል።ይህም የአንድን ልጥፍ  በተጠቃሚው ገፅ ላይ የመታየት እድል እንዲቀንስ እና እንዲጨምር ያደርጋል።
ያም ሆኖ ይህ ስልተቀመር የተጠቃሚውን ፍላጎት ፣ባህል ፣ ስሜት ፣ የቋንቋ አጠቃቀም እና ትርጉም በውል መለየትን በተመለከተ የራሱ የሆኑ ደካማ ጎኖች ያሉት በመሆኑ፤ የፌስቡክ እናት ኩባንያ ሜታ በተለያዩ ጊዜዎች ክስ እና ወቀሳ ሲቀርብበት ቆይቷል።
 በ2023ም የፌስቡክ ስልተቀመር የሰው ሰራሽ አስተውሎት እና እንደ ማሽን ትምህርት/ Machine Learnig/ ያሉ አዳዲስ እና ውስብስብ ቴክኖሎጂዎች  በመታገዝ  ተጠቃሚን ያማከለ  ተስማሚ  ይዘት ለማቅረብ በሚል ሌላ ለውጥ አድርጓል።በዚህ ማሻሻያ መሰረትም በፌስቡክ ስልተቀመር ላይ  ተፅዕኖ የሚያሳድሩ አራቱ ወሳኝ ነገሮች የአንድ ይዘት የክምችት መጠን፣የፍላጎት ጠቋሚ ምልክቶች፣ትንበያ እና የተፈላጊነት ደረጃ  ናቸው።ባለሙያው እንደሚሉት እነዚህን መሰረት አድርጎ ለተጠቃሚው መረጃ ያቀብላል።በዚህ መሰረት በ2023 የአጫጭር ቪዲዮዎች ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን አቶ ሰለሞን ያስረዳሉ።
የፌስቡክ ስልተ ቀመር በዚህ ሁኔታ እየተራቀቀ እና በየጊዜው እየተሻሻለ በመምጣቱ በአጠቃላይ ይዘትን ተፈላጊ ለማድረግ በየጊዜው የሚደረጉ የስልተቀመር ማሻሻያዎችን መገንዘብ ያስፈልጋል።ከዚህ አኳያ ታዳሚዎችዎን ግምት ውስጥ ያስገባ እና ቀረቤታ ያላቸውን ይዘቶች መለጠፍ ፣ተጠቃሚዎች ተሳትፎ እንዲያደርጉ ማበረታታት፣ አጠር ያሉ ቁልፍ ቃላትን መጠቀም ጠቃሚ መሆኑን የሶፍትዌር መሀንዲሱ አቶ ይግረማቸው አስረድተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ አጫጭር ይዘቶችን መለጠፍ ፣ይዘትን በድምፅ እና በምስል የታገዘ ማድረግ፣አጭጭር እና ገላጭ ርዕሶችን መጠቀም፣የተጠቃሚዎችን ጊዜ ታሳቢ በማድረግ ልጥፎችን  ቶሎቶሎ መቀያየር  ወሳኝ መሆኑንም ባለሙያው አመልክተዋል።

USA Technologieunternhmen Meta - Logo
ምስል Yves Herman/REUTERS
Logos von Facebook und TikTok nebeninander
ምስል Jakub Porzycki/NurPhoto/picture alliance
Symbolbild Facebook
ምስል Joel Saget/AFP/Getty Images/Newscom/picture alliance
Intelligente Technologie, künstliche Intelligenz und Datensicherheit
ምስል rook/YAY Images/IMAGO
Zuckerberg Hits Back At Facebook Whistleblower Claims
ምስል Cris Faga/ZUMA/picture alliance
USA Justiz l Cambridge Analytica Facebook - Skandal wegen Datenmissbrauch l Logo
ምስል Andrew M. Chang/ZUMA Wire/imago images

 

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሀይ ጫኔ
ሽዋዬ ለገሰ