1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፈረንሳይ ከቻድ ለምን በጥድፍያ ተባረረች?

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 26 2017

የፕሬዝዳንት ኢድሪስ ዴቢ አስተዳደር ፈረንሳይ እና የአውሮጳ ኅብረት ለሀገሪቱ የምርጫ ማስኬጃ በቂ የፋይናንስ ድጋፍ ባለማድረጋቸው ቅር ተሰኝቷል። በዚህ ሰበብ ቻድ በፈረንሳይና በአውሮፓ ኅብረት ላይ እምነት አጣታለች።ከሩስያ ወይም ከሌሎች ቱርክን ከመሳሰሉ ሀገራት ጋር መቀራረቧ ፈረንሳይን አለማስደሰቱን በቻድ ጉዳይ ጣልቃ እንደመግባት ቆጥራዋለች

https://p.dw.com/p/4oo30
የፈረንሳይ ወታደሮች ከሁለት ዓመት በፊት በቻድ ጎዳናዎች
የፈረንሳይ ወታደሮች ከሁለት ዓመት በፊት በቻድ ጎዳናዎች ምስል Aurelie Bazzara-Kibangula/AFP/Getty Images

ፈረንሳይ ከቻድ ለምን በጥድፍያ ተባረረች

ፈረንሳይ ቻድ የሚገኘውን የመጀመሪውን የጦር ሰፈሯን ለቻድ ለማስተላለፍ ካቀደችበት ከሳምንታት አስቀድማ ለቻድ አስረክባለች። የፈረንሳይ ወታደሮች ሰሜን ቻድ ፋያ ላርጎ በተባለው ስፍራ የሚገኘውን የመጨረሻውን የፈረንሳይ ወታደሮች የሳህል ይዞታ በጥድፍያ ለቀው እንዲወጡ ተደርገዋል።  የቻድ ባለሥልጣናት  የፈረንሳይ ወታደሮች እንጃሚና የሚገኘውን የጦር ሰፈራቸውን እስከ ጎርጎሮሳዊው ታኅሳስ 31 2024 ዓ.ም.ለቀው እንዲወጡ ያዘዙት ከአውሮጳውያኑ የልደት በዓል በፊት ነበር። 


ቻተም ሀውስ በተባለው የጥናት ተቋም የአፍሪቃ መርሀ ግብር ሃላፊ አሌክስ ቪንስ ለዶቼቬለ እንደተናገሩት ፈረንሳይ ከቻድ ቀስ በቀስ ለመውጣት ነበር ያሰበችው። ግን በጥድፍያ እንድትባረር ነው የተደረገው። «ፈረንሳይ ከቻድ የወጣችበት ፍጥነት አስገርሟታል። የጠበቀችው አልነበረም። ቀስ በቀስ ለሚካሄድ አወጣጥw ነበር የተዘጋጀችው ። ምናልባትም በቻድ በአነስተኛ ደረጃም ቢሆን እዚያ ለመቆየት የሚያስችላት ስምምነት ላይ እደርሳለሁም የሚል ተስፋም ነበራት። ሆኖም ያያኔው የቻድ መንግሥት መውጣትዋ የግድ መሆኑን አሳወቀ። እናም ፓሪስ በፈጣኑ መንገድ መውጣት ነበረባት» 

የቻድ ጦር ኃይል እንደሚለው የፈረንሳይ ወታደሮች 780 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው ዋና ከተማ እንጃሚና በመኪናዎች ነው የሄዱት። ይህ የሆነውም የመከላከያ ስምምነቱ ከማብቃቱ በፊት ነው። ፈረንሳይ በቻድ በተለይም በምሥራቃዊቷ ከተማ አቤቼና እንጃሚና ከተሞች 1 ሺህ ወታደሮች ነበሯት። ከመካከላቸው 100 ወታደሮች ወደ ፈረንሳይ ሄደዋል።  አንቶኖቭ 124 አውሮፕላን፣  70 ቶን የሚመዝን ጭነት ይዞ ባለፈው ሳምንት ወደ ፈረንሳይ መሄዱን የቻድ ጦር ኃይል አስታውቋል። የፈረንሳይ ባለሥልጣናት እንደተናገሩት ደግሞ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎቻቸው በጥር ወር በካሜሩንዋ ወደብ ዱዋላ በኩል ወደ ፈረንሳይ ያቀናሉ።


 በጎርጎሮሳዊው ህዳር መጨረሻ ቻድ ከቀድሞዋ ቅኝ ገዥ ፈረንሳይ ጋር የነበራት ወታደራዊ ትብብር ያከትማል። ይህ ቻድ ሙሉ ሉዓላዊነቷን የምታረጋግጥበት ጊዜ ነው ያሉት የቻድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብደራማን ኩዋላማላህ የእከዛሬውን ስምምነት ፍጹም ጊዜ ያለፈበትና ከአሁኑ ፖለቲካዊና ስልታዊ አቀማመጥ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አብሮ የማይሄድ ብለውታል። የፈረንሳይና የቻድን ሁኔታ የሚከታተሉ ታዛቢዎች እንደሚሉት ቻድ እዚህ ውሳኔ ላይ እንድትደርስ የገፋፏት አንዳንድ ከፈረንሳይ ጋር የተፈጠሩ አለመግባባቶች ናቸው። 
የፕሬዝዳንት ኢድሪስ ዴቢ አስተዳደር ፈረንሳይ እና የአውሮጳ ኅብረት ለሀገሪቱ የምርጫ ማስኬጃ በቂ የፋይናንስ ድጋፍ ባለማድረጋቸው ቅር ተሰኝተዋል። የቅርብ ጊዜው ምርጫ ከቀድሞው ፕሬዝዳንት  ሞት በኋላ የነበረውን የሦስት ዓመት የሽግግር ጊዜ ከፍጻሜ አድርሷል። ሳክሬ ፑር ላ ሪፐብሊክ የተባለው ፓርቲ ፕሬዝዳንት ፍራንሷ ጄኮምቤ ለመጨረሻው ምርጫ የአውሮጳ ኅብረት የገንዘብ ድጋፍ አለማድረጉን ወደፊትም ያረጋል ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል። ቻድ በፈረንሳይና በአውሮፓ ኅብረት ላይ መተማመን እንደሌላትም ገልጸዋል። ቻድ ከሩስያ ወይም ከሌሎች ቱርክን ከመሳሰሉ ሀገራት ጋር መቀራረቧ ፈረንሳይን እንደማያስደስትም ነው የተናገሩት። በዚህ ጉዳይ ላይም ፈረንሳይ ማብራሪያ ጠይቃለች። ይህ ደግሞ በቻድ ጉዳይ ጣልቃ እንደመግባት ተደርጎ ነው የታየባት።   

የቻድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብድራማን ኩዋላማላህ
የቻድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብድራማን ኩዋላማላህ ምስል FRANCK FIFE/AFP/Getty Images


ርያን ካሚንግ ሲግናል ሪስክ የተባለ በአፍሪቃ ላይ ያተኮረ ቀውስን መቋቋሚያ ላይ ትንተና የሚሰጥ ድርጅት ሃላፊ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ከጸቦቹ መካከል የሚያመዝነው ከጎርጎሮሳዊው ሚያዚያ 2023 ዓም አንስቶ በሚካሄደው የሱዳን የርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ቻድ ጣልቃ መግባቷን ፈረንሳይ መተቸቷ ነው።  «ከፈረንሳይና ከቻድ ጸብ አብዛኛው ፣ፈረንሳይ ቻድ በሱዳኑ ግጭት ውስጥ ተሳታፊ እና በተለይም ወደ የሱዳንን ጦር ወደሚወጋው ወደ ፈጥኖ ደራሹ ኃይል አርኤስኤፍ ይሄዱ ለነበሩ የኢሚሬትስ የጦር መሳሪያዎች መተላለፊያ መሆንዋን ፈረንሳይ መተቸትዋን ማዕከል ያደረጉ ነበሩ። ፈረንሳይ ከሌሎች ምዕራባውያን ሀገራት ጋር የሱዳን ጦር ኃይልንና የፈጥኖ ደራሹን ኃይል ግጭት በድርድር ለማስቆም ጥረት በማድረግ ላይ ነበረች። ሆኖም ፈጥኖ ደራሹ ኃይል እንደ የተባበሩት አረብ ኤሜሪቶች ከመሳሰሉ አገራት በቻድ በኩል  በሚያገኝው የጦር መሳሪያና ሌሎችም ወታደራዊ ድጋፎች ጦርነቱ ቀጥሏል። ግልጽ ነው ቻድ ፈጥኖ ደራሹን ኃይል በግልጽ ትረዳለች ።ምክንያቱም በርካታ የቻድ ዝርያ ያላቸው የመሀመድ ዴቢ አገዛዝ ተቃዋሚዎች በሱዳን ጦር  ላይ ጦር ሰብቀዋል።» 


ቻድ ፈረንሳይ በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ፣ምዕራባውያን እስላማዊ ብለው በሚጠሯቸው ጽንፈኛ ሚሊሽያዎች ላይ የከፈተችው ዘመቻ  አንዷ ቁልፍ አጋር ናት።   በማሊ ቡርኪናፋሶ እና ኒዠር ከተካሄዱ መፈንቅለ መንግስቶች በኃላ የፈረንሳይ ወታደሮች ከነዚህ ሀገራት ወጥተው ቻድ ብቻ ነው የቀሩት  ቻድ ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛትነት ነጻ ከወጣችበት ከጎርጎሮሳዊው 1960 በኋላ የፈረንሳይ ወታደሮች የአማጽያንን እንቅስቃሴ ለመግታት የአየር ድጋፍን ቸምሮ አስፈላጊ የሚባሉ ወታደራዊ ድጋፎችን ለቻድ ሲሰጡ ቆይተዋል።  ለስድስት ጊዜ ያህክል የፈረንሳይ ወታደሮች በቻድ ጣልቃ ገብተዋል። ሆኖም ፀረ -ፈረንሳይ ስሜት በመላው ሀገሪቱ ተሰራጭቷል። ቦኮሃራም የተባለው ጽንፈኛ ታጣቂ ቡድን 40 የቻድ ወታደሮችን ባለፈው ጥቅምት ከገደለ በኋላ በሺህዎች የሚቆጠሩ ቻዳውያን የፈረንሳይ ወታደሮች ከሀገራቸው እንዲወጡ ሲጠይቁ ነበር። የቻድ መንግስት በወቅቱ ፈረንሳይ ከጥቃቱ በኋላ ድጋፍ ባለመስጠቷ ወይም መረጃ ባለማቀበሏ የፈረንሳይ ወታደሮች ከሀገሪቱ እንዲወጡ እና ሀገሪቱ ከፈረንሳይ ጋር ያላት የመከላከያ ውል እንዲያከትም ጥያቄዎች ወደማቅረብ አመራ። ቻዳዊው የማኅበራዊ ጉዳዮች ተመራማሪ  ላዲባ ጎንዶ ለዶቼቬለ እንደተናገሩት በቻድ ፈረንሳይ ባሏት ሳተላይቶች ድሮኖች እና ሌሎች አጋሮች ጥቃቱ መድረስ አልነበረበትም። ጥቃቱን ሊያስቀር የሚችል ግልጽ ቅንጅት እና የስለላ መረጃዎችን ማጋርት መጉደሉ ግልጽ ነው ብለዋል ባለሞያው።   

የሀንጋሪው ፕሬዝዳንት ቪክቶር ኡርባን ከቻዱ መሪ ማሃማት ኢድሪስ ዴቢ ጋር  በቻድ ባለስልጣኖች አቀባበል ሲደረግላቸው
የሀንጋሪው ፕሬዝዳንት ቪክቶር ኡርባን ከቻዱ መሪ ማሃማት ኢድሪስ ዴቢ ጋር በቻድ ባለስልጣኖች አቀባበል ሲደረግላቸው ምስል VIVIEN C. BENKO/Hungarian Prime Minister/AFP


የፈረንሳይ የከቻድ መውጣት ማን ፈረንሳይን ይተካል የሚለውን ጥያቄ አስከትሏል። በግንቦት የቻድ ባለልሥልጣናት የአሜሪካን ወታደሮች ከሀገራቸው እንዲወጡ አዘዋል። አሁን ቀጣናው ፣ፊቱን ወደ ሩስያ እያዞረ ይመስላል። ቻድ የቫግነር ቡድን የተባለው የሩስያ የግል ወታደራዊ ኩባንያ በሚገኝባቸው ሀገራት ተከባለች። ላዲባ ጎንዶ እንደሚሉት ሩስያ በ ታደራዊ ድግፍም ሆነ በስለላ  ዋነኛ የቻድ አጋር መሆንዋ አይቀርም። የቻድ ፕሬዝዳንት ዴቢ በአንድ ወቅት  ከፈረንሳይ ጋር ሀገሪቱ የነበራት የመከላከያ ስምምነት ማብቃቱ ዓለም አፍ ትብብር መቃወም እንዳይደለ ተናግረዋል። ፈረንሳይ አስፈላጊ አጋራችን ነበረች ሆኖም ቻድ ስልታዊ አጋርነትን ቅድሚያ በምትሰጣቸው ብሔራዊ ጉዳዮቿ መሠረት ታካሂዳለችም ብለዋል። ቻድ ወደፊት ከአውሮፓ ኅብረት ጋር የሚኖራት ግንኙነትም አሁን ኒዠር ውስጥ እንደሚታየው ሊሆን እንደሚችል ቪንስ ጠቁመዋል።


«ቁጥሩ ወደ 300 የሚደርስ የጣሊያን ጦር አሁንም ኒዠር ይገኛል። ስለዚህ ፈረንሳይ መልቀቅ አለባት። ጀርመኖችም ከኒዠር መውጣት አለባቸው። በሁለትዮሽ ስምምነት መሠረት ጣሊያኖች በዚያ ቆይተዋል። ወደፊት ቻድም ይህን ዓይነት ፈለግ ትከተል አትከተል እናያለን። ወይስ በማሊ እንደምናየው የምዕራባውያንን ተሳትፎ ሙሉ በሙሉ በማስቀረት፣ ከቱርክ ቻያና እና ሩስያ ጋር የሚያተኩር ይበልጥ ርዕዮተ ዓለማዊ የሆነ የፀጥታ አሰራር ትጠመዳለች።»  
ለቻድ የአውሮፓ ኅብረት በውጭ ቀጥተኛ ውረታ እና ሰብዓዊ እርዳታ ረገድ ዋነኛ የኤኮኖሚ ኃይል ሆኖ ይቀጥላል ተብሎ ይታመናል። ሀንጋሪ በቅርቡ ለቻድ ልዩ ልዑክ ሾማለች። ይህም  ቪንስ እንዳሉት በቻድ ቀዳሚውን ቦታ ለማግኘት እድል የሚሰጥ ሊሆን ይችላል። ኅብረቱን ለመዘወርም እንደ መጠቀሚያ መንገድ ሊያገለግልም ይችላል። 

ኂሩት መለሰ 
ታምራት ዲንሳ