1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፅናት፤ የጾታዊ ጥቃት ሰለባዋ አዳጊ ወጣት

ዓርብ፣ ጥር 13 2014

ወጣት ሴቶች በሕይወታቸው ከሚያጋጥሟቸው ችግሮች አንዱ የአስገድዶ መደፈር ጥቃት ነው። በወላጅ አባቷ የመደፈር ጥቃት የደረሰባት አዳጊ ወጣት ፅናት ከደረሰባት የስነ ልቦና ጉዳት አገግማ አዲስ ሕይወት በመጀመር ሂደት ላይ ትገኛለች።

https://p.dw.com/p/45t8Z
Äthiopien Rehabilitationszentrum für Vergewaltigungsopfer in Hawassa
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የወጣቶች ዓለም

በሀዋሳ ከተማ የሚገኘው የሴቶች ማረፊያና ልማት ማሕበር የጾታዊ ጥቃት ሰላባ የሆኑ ሴቶችን ተቀብሎ እያስተናገደ ይገኛል። በዚህ ማዕከል ተጠልለው ከሚገኙት መካከል አብዛኞቹ በታዳጊ ወጣትነት የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሴቶች ናቸው። በማገገሚያ ማዕከሉ የተሰባሰቡት ሴቶች የአስገድዶ መደፈርን ጨምሮ የተለያዩ ጾታዊ ጥቃቶች ሰለባዎች ናቸው።

ከእነኝሁ ተጠቂዎቹ መካከል በወላጅቷ አባቷ የተደፈረችውና ለዚህ ዘገባ ሲባል ስሟ የተቀየረው የ14 ዓመቷ ፅናት መንግሥቱ እንዷ ናት። ፅናት ወደ ማዕከሉ ስትገባ በደረሰባት ጥቃት በከፍተኛ ፍርሃት እና የመረበሽ ስሜት ውስጥ እንደነበረችና አሁን ላይ ግን ባገኘችው የህክምና፣ የስነ ልቦና ድጋፍ እና ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች የወደቀው ስነ ልቦናዋ መስተካከሉን ትናገራለች።

Äthiopien Rehabilitationszentrum für Vergewaltigungsopfer in Hawassa
የጾታ ጥቃት ሰለባዎች ማገገሚያ ማዕከል ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

አያይዛም «እሁን እኔ በተመሳሳይ ችግር ውስጥ በሚገኙ ሴቶች ዘንድ እንደ ጀግኒት ነው የምታየሁ። ምክንያቱም በመጀመሪያ ከደረሰብኝ ጥቃት በቶሎ ከማገገሜም በላይ ጥቃቱን በፈጸመበኝ አባቴ ላይ ክስ በመመስረትና ጉዳዩን ለሕግ በማስረዳት በ10 ዓመት እስራት እንዲቀጣ አስደርጊያለሁ። አሁን ደግሞ በማዕከሉ በነበረኝ ቆይታ ባገኘሁት የልብስ ስፌት ስልጠናና የመነሻ ገንዘብ ከማዕከሉ በመውጣት አዲስ ህይወት ለመጀመር በዝግጅት ላይ እገኛለሁ» ብላለች ።

የሴቶች ማረፊያና ልማት ማሕበር የሀዋሳ ቅርንጫፍ አስተባባሪ ወይዘሮ ራሄል መስፍን በበኩላቸው ማሕበራቸው እንደ ፅናት ለመሳሰሉ ጾታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች የህክምና ፣ የሰነልቦና እና የሕግ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ይናገራሉ።

«አብዛኞቹ ተጠቂዎች ወደ ማዕከሉ ሲገቡ ብቻኝነት፤ ፍረሃትና የለቅሶ ስሜት ይስተዋልባቸዋል። መረጋጋት የሚያስችላቸውን የስነ ልቦና ድጋፍ ካደረግንላቸው በኋላ የደረሰባቸውን በሙሉ አውጥተው ይነግሩናል። በዚህ መነሻም የህክምና፣ የስነ ልቦና ድጋፍ፣ የሕግ አገልግሎት እና ተያያዥ እገዛዎችን እንሰጣቸዋለን» ብለዋል ወይዘሮ ራሄል።

Äthiopien Rehabilitationszentrum für Vergewaltigungsopfer in Hawassa
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

በእርግጥ ፅናት መንግሥቱ ከደረሰባት ጾታዊ ጥቃት አገግማ የድርጊቱን ፈጻሚ በሕግ እስከማስቀጣት ብትደርስም በበርካታ አካባቢዎች የሚፈጸሙ ተመመሳይ ጥቃቶች ተሸፋፍነው ሊቀሩ እንደሚችሉ በቀላሉ መገመት ይቻላል። ወይዘሮ ፍሬህይወት ገብረ ጻዲቅ በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የሕጻናት፣ የሴቶችና የወጣቶች ጉዳይ መምሪያ ሃላፊ ናቸው።  ኃላፊዋ እንደሚሉት ታዳጊ ሴቶች ጥቃት የሚያደርሱባቸው ግለሰቦችን ለሚመለከታቸው አካላት የማሳወቁ ጉዳይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መሻሻል እየታየበት ይገኛል። ይሁንእንጂ ከችግሩ ስፋት አንፃር አሁንም ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ተባባሪ እና አጋዥ ሊሆን እንደሚገባ ነው ወይዘሮ ፍሬህይወት የጠቆሙት።  

Äthiopien Rehabilitationszentrum für Vergewaltigungsopfer in Hawassa
የጾታ ጥቃት ሰለባዎች ማገገሚያ ማዕከል ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል የሁሉም ማኅበረሰብ ተሳትፎ ያስፈልጋል በሚለው የወይዘሮ ፍሬህይወት አስተያየት የሚስማሙት የሴቶች ማረፊያና ልማት ማሕበር የሀዋሳ ቅርንጫፍ አስተባባሪዋ ወይዘሮ ራሄል መስፍን ከዚህ በተጨማሪ ግን አስተሳሰብ ለውጥ ላይ በስፋት መሥራት የጎላ ጠቀሜታ አለው በማለት አስተያየታቸውን አጠቃለዋል። ሙሉ ቅንብሩን ከድምፅ ማዕቀፉ ያድምጡ።

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ሸዋዬ ለገሠ