1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመናዊዉ ሂዮብ ሉዶልፍ፤ የኢትዮጵያ ጥናት አባት 400 ኛ ዓመት

ሐሙስ፣ መስከረም 23 2017

የጀርመኑ ምሁር የኢትዮጵያ ጥናት፤ አባት ሂዮብ ሉዶልፍ፤ ኢትዮጵያዊዉን ምሁር አባ ጎርጎርዮስን በዝያ ዘመን ባይተዋወቁ ኖሮ ግዕዝን ባልተማሩ ነበር። የኢትዮጵያ ጥናት በጀርመን የጀመረዉ በ1655 ዓ.ም ነዉ። ሁለቱ ምሁራ የተዋወቁት አባ ጎርጎርዮስ በካቶሊክ እምነታቸዉ ወደ ጣልያን ቫቲካን ተሰደዉ ሳለ ነዉ።

https://p.dw.com/p/4lNZE
ፎቶ ፤ በጎታ ኤርፎርት የሂዮብ ሉዶልፍ 400ኛ ዓመት ልደት በዓል ጉባኤ ላይ በጀርመናዊዉ የታሪክ ተመራማሪ እና የኢትዮጵያ ጥናት ፕሮፌሰር ወልበርት ሽሚድት የቀረበ
ጀርመናዊዉ ሂዮብ ሉዶልፍ፤ የኢትዮጵያን ጥናት አባት 400 ኛ ዓመት ታሰበምስል Azeb Tadesse Hahn/DW

ጀርመናዊዉ ሂዮብ ሉዶልፍ፤ የኢትዮጵያን ጥናት አባት 400 ኛ ዓመት

«ዘንድሮ 400 ኛዉን ዓመት የኢትዮጵያን ጥናት አባት ተብለዉ የሚጠሩትን የሂዮብ ሉዶልፍን 400ኛ ዓመት የልደት በዓል በማስመልከት ነዉ ያዘጋጀነዉ።» ይህን ያሉት፤ በጀርመን ታዋቂ የሆኑት ደራሲ እና የአፍሪቃ እና የመካከለኛዉ ምስራቅ ጉዳዮች አማካሪ፤ እንዲሁም የታሪክ ምሁሩ ልዑል ዶ/ር አስፋ ወሰን አስራተ ናቸዉ።

በልዑል ዶ/ር አስፋ ወሰን አስራተ የተመሰረተዉ እና ዘንድሮ 23 ኛ ዓመት የሆነዉ ዉርሰ ኢትዮጵያ የተባለዉ ማኅበር በባለፈዉ ሳምንት መጨረሻ ፤ የኢትዮጵያ ጥናት አባት እየተባሉትን የጀርመናዊዉን የታሪክ ተመራማሪ የሂዮብ ሉዶልፍን 400ኛ ዓመት በተለያዩ ዝግጅቶች አክብሯል። ሂዮብ ሉዶልፍ በማስመልከት ምሁሩ በኢትዮጵያ ባህል፤ ቋንቋና ታሪክ ላይ ያደረጉትን የምርምር ሥራ እና ያበረከቱን አስተዋፅኦ በተመለከተ ለሦስት ቀናት በዘለቀ ጉባዔ ምሁሩ ባበረከቱት አስተዋፅኦ ላይ የተለያዩ የጥናት ፅሑፎችን በማቅረብ ተወያይቷል።  ዘንድሮ 400ኛ የልደት በዓላቸዉ በተለያዩ ዝግጅቶች በጀርመን እና በዉጭ ሃገራት በሚገኙ የጀርመን የባህል ተቋማት የታወሰዉ ጀርመናዊዉ ተመራማሪ ሂዮብ ሉዶልፍ፤ የጥንታዊዉ ቋንቋ የመጀመርያ መዝገበ ቃላት፤ Aethiopico-Latinumx ን ፤ መዝገበ ቃላት  Amharico-Latinum፤ እንዲሁም Historia Aethiopica፤ የተሰኙ ህትመቶቻቸዉ፤ ለታሪክ ለባህል እና ቋንቋ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳላቸዉ የተለያዩ ምሁራን በጉባዔዉ ላይ ባቀረብዋቸዉ የጥናት ጽሁፎቻቸዉ ገልፀዋል። ጀርመናዊዉ የታሪክ ተመራማሪ የሂዮብ ሉዶልፍ በቋንቋ እና ታሪክ ላይ ብቻ ሳይሆን ስለ ኢትዮጵያ ሃይማኖት እና ጥበብ ስለአገሪቱ እፅዋት እና እንስሳትም መጻፋቸዉ በጉባዔዉ ላይ ተነግሯል። ሂዮብ ሉዶልፍ የኢትዮጵያን የእጅ ጽሁፎች እና ጥንታዊ ድርሳናትንም ሰብስበዉ ተርጉመዋል።

ልዑል ዶ/ር አስፋ ወሰን አስራተ
ጀርመናዊዉ ሂዮብ ሉዶልፍ፤ የኢትዮጵያን ጥናት አባት 400 ኛ ዓመት ታሰበምስል Azeb Tadesse Hahn/DW

የሂዮብ ሩዶልፍ ስራዎች የኢትዮጵያን ባህክ እና ታሪክ ለአዉሮጳዉ ዓለም ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ከነበሩበት ዘመን እስከአሁንም ድረስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱም ተነግሯል። ጀርመናዊዉ ሂዮብ ሉዶልፍ ኢትዮጵያን የተዋወቁት እና በኢትዮጵያ ላይ ፋና ወጊ የተባለ ስራቸዉን ሊያበረክቱ የቻሉት፣ አባ ጎርጎርዮስን በመተዋወቃቸዉ ነበር። የካቶሊክ እምነት ተከታይ የነበሩት አባ ጎርጎርዮስ በ 16ኛዉ ክፍለዘመን መጨረሻ የተወለዱ እና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ እንደነበሩም ይታመናል። አባ ጎርጎርዮስ በንጉስ አጼ ፋሲል ዘመን 1632 በካቶሊኮች ላይ የታወጀዉን ስደት ተከትሎ እምነቴን አልቀይርም ብለዉ የካቶሊክ እምነታቸዉን እንደያዙ ከተሰደዱ በኋላ ከጀርመናዊዉ ተመራማሪ ሂዮብ ሩዶልፍ ጋር ሮም ላይ 1649 እንደተዋወቁ የታሪክ ማህደራቸዉ ያሳያል። ጀርመናዊዉ ምሁር ሂዮብ ሩዶልፍ በኢትዮጵያ ላይ ያደረጉት ጥናቶች እና ፁሁፎች አባ ጎርጎርዮስን ባይተዋወቁ ኖሮ ለዛሬ ዘርፈ ብዙ በኢትዮጵያ ላይ ምርምር ባልበቃ ነበር። በዚህም ይላሉ ልዑል አስፋወሰን አስራተ የኢትዮጵያ ታሪክ ባህል ቋንቋ ጥናት  በጀርመን ላይፕዚግ ከተማ በሚገኝ ዩንቨርስቲ የጀመረዉ በጎርጎረሳዉያኑ 1655 ዓ.ም ነዉ። 

ዘገየ ወልደማርያም አምቦ - የታሪክ ተመራማሪ
ጀርመናዊዉ ሂዮብ ሉዶልፍ፤ የኢትዮጵያን ጥናት አባት 400 ኛ ዓመት ታሰበምስል Azeb Tadesse Hahn/DW

«የጀርመኑ ምሁር የኢትዮጵያ ጥናት፤ አባት እና ቆርቋሪ፤ ተብሎ የሚጠራዉ፤እሱ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊዉ አባ ጎርጎርዮስም የዚህ ጥናት መጀመር ዋና ማህለቅ ናቸዉ ብዬ አምናለሁ። ስለዚህም በዓለም አአፍ ደረጃ የኢትዮጵያ ጥናት መስራቾች አባታችን አባ ጎርጎርዮስ እና ጀርመናዊዉ ምሁር ሂዮብ ሉዶልፍ ናቸዉ ማለት ይቻላል። ሁለቱም ምሁራን በ 17ኛዉ ክፍለዘመን የኖሩ ናቸዉ። በሁለቱ ምሁራን መካከል የተጀመረዉ ፍቅር ፤ ሮማ ዉስጥ ነበር፤ አባ ጎርጎርዮስ የካቶሊክ ሃይማኖት ተከታይ ስለነበር፤ ወደ ሮማን ሄደዉ ቫቲካን ዉስጥ ግዕዝ ያስተምሩ ነበር፤ ሂዮብ ሉዶልፍ እዛ አገኛቸዉ፤ እሳቸዉ ለሱ ግዕዝ ሲያስተምሩት፤ እሱ ደግሞ እሳቸዉን ላቲን ያስተምራቸዉ ነበር። ሁለቱ ምሁራን በዚህ በሁለቱ ቋንቋ ነበር የሚነጋገሩት። የሁለቱ ሰዎች ግንኙነት ወደ አብሮ የመስራት ዘይቤ ስለተጨመረበት፤ በእዉነቱ ለኢትዮጵያችን ጠቃሚ የሆነ የጥናት ክፍል ፤ በዓለም እንዲታወቅ አድርገዉ፤ በጎርጎረሳዉያን አቆጣጠር 1655 ዓ.ም   በጀርመንዋ ላይፕዚግ ከተማ የኢትዮጵያ ጥናት ተጀመረ። በዝያን ወቅት የጀርመን ጥናት የሚል ክፍል አልነበረም። »  

ዶ/ር ሳሙኤል ኪዳነ ኃይሌ - የታሪክ ተመራማሪ
ጀርመናዊዉ ሂዮብ ሉዶልፍ፤ የኢትዮጵያን ጥናት አባት 400 ኛ ዓመት ታሰበምስል Azeb Tadesse Hahn/DW

ልዑል ዶ/ር አስፋ ወሰን አስራተከ 23 ዓመት በፊት የኢትዮጵያን ባህል እና ጥበባት ለመጠበቅ እና ለአዲስ ትዉልድ ለማስተላለፍ «ዉርስ አትዮጵያ»  „Orbis Aethiopicus“  በሚል ያቋቋሙት ድርጅት በኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ የዓመቱ ጉባዔ ለሦስት ቀናት ይቀመጣል። ዉርሰ ኢትዮጵያ ማኅበር ዘንድሮ የኢትዮጵያ ጥናት አባት የተባሉትን የጀርመናዊ የሂዮብ ሉዶልፍን ፤ 400ኛ የትዉልድ ዓመት በማስመልከት፤ ይኖሩበት እና ያስተምሩበት በነበረበት ጎታ በምትባል ቴሪንገን ግዛት ዉስጥ ዉስጥ በምትገኝ ከተማ ላይ ነበር ጉባኤዉን ያካሄደዉ። ጉባኤዉ በተካሄደበት በአነስተኛዉ ከተማ በኢትዮጵያ ስም የተሰየመ መንገድም አለ ፤ የኢትዮጵያ መንገድ ይባላል። ከዚህ ሌላ ጎታ ከተማ የኢትዮጵያዋ የአድዋ ከተማ እህት ከተማ ነች።  

ዉርስ አትዮጵያ  በጀርመንዋ ጎታ ከተማ ላይ ባዘጋጀዉ የኢትዮጵያ ጥናት አባት የሂዮብ ሩዶልፍ 400ኛ ዓመት ማስታወሻ ጉባዔ ላይ በአዲስ አበባ የሚገኙ ሁለት ከፍተና ምሁራንን ጨምሮ ከንጉሰ ነገስቱ ጀምሮ በኢትዮጵያ በተለያዩ ሥራዎች ላይ ተሰማርተዉ የነበሩ ጀርመናዉያን ምሁራን፤ በአሁኑ ጊዜም በኢትዮጵያ በስራ ላይ የሚገኙ ጀርመናዉያን ምሁራን በጎታ ዩንቨርስቲ በተለያዩ የኢትዮጵያ ጥናት ላይ የዶክትሪት ትምህርታቸዉን በመከታተል ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን እና የጎታ ዩንቨርስቲ ፕሮፌሰሮች የጉባኤዉ ተካፍይ ነበሩ። በአዲስ አበባ ከሚገኘዉ የጀርመን የባህል ማዕከል በጎተ ተቋም ከፍተኛ ትብብር በሦስት ቀናቱ ጉባኤ ላይ ለመገኘት ከአዲስ አበባ የመጡት እና በጉባኤዉ ላይ ጥናታቸዉን ካቀረቡት መካከል ፕሮፌሰር ሽፈራዉ በቀለ ይገኙበታል።

«ጀርመናዉያን በሂዮብ ሉዶልፍ ይኮሩበታል፤ በጣም ትልቅ ምሁራቸዉ ነዉ። መታወቅ አለበት ይላሉ ። ጀርመናዉያን ሂዮብ ከአፍሪቃዉያን ጋር ትልቅ የትብብር ስራ  የፈፀመ፤ ነጮችም ጥቁሮችም፤ ተባብረዉ ይሰራሉ ለሚለዉ ተምሳሌት ነዉ ይላሉ።  ጀርመናዉያን ከኢትዮጵያዊዉ አባ ጎርጎርዮስ ጋር መስራቱ iመታወቅ አለበት ብለዉ ያምናሉ።» ከኢትዮጵያ ለዚሁ ጉባዔ በጎተ የባህል ማዕከል በኩል ተጋብዘዉ የመጡት በኢትዮጵያ የካቶሊክ ቤተክርስትያን በአዲስ አበባ አገረስብከት ካህን እና በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ሥነ-ልሳን እና ፊሎሎጂ ትምህርት እና መምህር አባ ዶ/ር ዳንኤል አሰፋ ስለጀርመናዊዉና ኢትዮጵያዊዉ ምሁር አበርክቶት ይህን ብለዉናል።

ፍሰሃ በርኸ - የታሪክ ተመራማሪ
ጀርመናዊዉ ሂዮብ ሉዶልፍ፤ የኢትዮጵያን ጥናት አባት 400 ኛ ዓመት ታሰበምስል Azeb Tadesse Hahn/DW

«ሂዮብ ሉዶልፍ ራሱ የፃፈዉ የግዕዝ ሰዋስዉ እና የግዕዝ መዝገበ ቃላትን ስናይ፤ ሂዮብ ከአባ ጎርጎርዮስ የቀሰመዉን እንዳለ አይደለም፤ ያስቀመጠዉ። ትልቅ ተነሳሽነት እንደነበረዉም እንማራለን፤ በተጨማሪ ግን ለምዕራቡ ዓለም እንደሚስማማ አድርጎ፤ ተርጉሞታል። እና ከዚህ የምንማረዉ፤ እዉቀቱን ወደ አገሩ ሰዎች የማድረሱ እና በኛም በኩል አንዳንድ ነገሮች ወደ አገራችን ስናስገባ፤ በመጀመርያ ከማህበረሰቡ ባህል አስተሳሰብ እና የኑሮ ዘይቤ ይጣጣማል ብለን መዝነን መሆኑን የምንማርበት ነዉ።»

ዶ/ር ሳሙኤል ኪዳነ ኃይሌ በጀርመን በኤርፉርት ዩንቨርስቲ የታሪክ እና የባህል ጥናት ማዕከል  የዶክትሬት ዲግሪያቸዉን አጠናቀዋል። በጎታ ጉባኤ ላይ አንዱ የጥናት ፁሁፍ አቅራቢም ነበሩ። ከወራቶች በኋላ የዶክትሬት ማዕረጋቸዉን ከዚሁ ከኤርፉርት ዩንቨርስቲ የሚቀበሉት የከፋዉ ጎልማሳ ዘገየ ወልደማርያም አምቦ ፤ በተለይ በከፋ ህዝብ ባህል ቋንቋ ጥናት ላይ ለዓመታት እየሰሩ ነዉ። ሌላዉ የታሪክ ተመራማሪ ጎልማሳ ፍሰሃ በርኸ  በኤርፉርት ዩንቨርስቲ የታሪክ እና የባህል ጥናት ማዕከል በኢትዮጵያ ዶባ ስለሚባሉ ህዝቦች እያጠኑ ናቸዉ።

ወልበርት ሽሚድት - ፕሮፌሰር - የታሪክ ተመራማሪ
ጀርመናዊዉ ሂዮብ ሉዶልፍ፤ የኢትዮጵያን ጥናት አባት 400 ኛ ዓመት ታሰበምስል Azeb Tadesse Hahn/DW

ጉባኤዉን ያዘጋጀዉ ዉርሰ ኢትዮጵያ ከተመሰረተ ከጥቂት ዓመታት ጀምሮ የማኅበሩ አባል የሆኑት እና በጀርመን ኑረንበርግ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሳምሶን በቀለ ተሰማ ማኅበሩ ስለሚያካሂደዉ ተግባር ደስተኛ ናቸዉ። በጉባዔዉ ላይ የጥናት ፅሑፋቸዉን ያቀረቡትን ሦስቱንም ኢትዮጵያዉያን የታሪክ ተመራማሪዎች ሰፋ ያለ ቃለ መጠይቅ ሰጥተዉናል። በሚቀጥሉት ሳምንታቶች ይዘናቸዉ እንመለሳለን።  

አዜብ ታደሰ