1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ድህነት በጀርመን እና ኢትዮጵያ እንዴት ይገለፃል?

ልደት አበበ
ዓርብ፣ ጥር 9 2017

እዚህ ጀርመን ውስጥ አንድ አራተኛ የሚሆነው ወጣት ለድህነት የተጋለጠ መሆኑን በቅርቡ የወጣ አንድ ጥናት ያመለክታል። በተለይ ተማሪ ወጣቶችን ለድህነት የዳረገው ዋነኛ ምክንያት ለቤት ኪራይ የሚያወጡት ወጪ እንደሆነ ተጠቅሷል። ኢትዮጵያ ያሉ ወጣቶችስ ስለ ወጣቶች የኑሮ ሁኔታ ምን ይላሉ? በርካቶች በፁሁፍ እና በድምፅ አስተያየታቸውን አጋርተውናል።

https://p.dw.com/p/4pGJl
Äthiopien Armut l Arbeitslosigkeit l Junge arbeitslose suchen nach Arbeitsangeboten
ስራ ፈላጊዎች በኢትዮጵያምስል Thomas Imo/photothek.net/picture alliance

ድህነት በጀርመን እና ኢትዮጵያ እንዴት ይገለፃል?

 ጀርመን ሀብታም ሀገር ብትሆንም በቅርቡ ይፋ የሆነ ጥናት እንደሚጠቁመው አንድ አራተኛ ያህሉ ወጣት ለድህነት ተጋልጧል። ይህንን የሰማው ኢትዮጵያዊ ወጣት አበራ፤ «እንዴ ድህነትን የተጎናፀፍነው እኛ ኢትዮጵያውያን ብቻ መስሎኝ ነበር። ለካ አውሮፓም አለ።   ሲል አስተያየቱን አጋርቶናል።  ስሙ እንዲገለፅ ያልፈለገው የዮንቨርሲቲ ተማሪ ደግሞ ከወላይታ  ሶዶ፣ ጀርመን ሀገር ላይ ይህን ያህል ወጣት በድህነት መኖሩ አስገርሞታል። «እውነት የማይመስል ዜና ነው። ምክንያቱም እኛ ምዕራባዊያንን የምናስባቸው በሁሉም ነገር ከፍ ያሉ ያደጉ ሀገራት ስለሆኑ ወጣቶች እንዲህ በድህነት ይኖራሉ ብለን አንጠብቅም።»

ድህነት እንዴት ይገለፃል?  

በዚህ በምዕራቡ ዓለም ጥናት መሠረት እጎአ በ2023 ዓም  12 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ጀርመን ውስጥ ድሀ ወይም ለድህነት የተጋለጡ  ነበሩ። በዝርዝር ስናየው፤ አንድ ብቻውን የሚኖር ሰው ግብር ከከበፈ በኋላ በወር 1310 ዮሮ ወይም ከዚያ በታች ገቢ ያለው ከሆነ የድህነት ጫፍ ላይ ይገኛል።  እድሜያቸው ከ 18 እስከ 24 ዓመት የሆኑ ወጣቶች 25 በመቶ ያህሉ በዚህ መስፈርት መሠረት ድህነት ያጠቃቸዋል። በተለይ ከፍተኛ ወጪ የሚያስወጣቸው የቤት ኪራይ ሲሆን ለዚህም ካላቸው የወር ገቢ 40 በመቶ ወይም ከዚያ በላይ ለቤት ኪራይ ያወጣሉ፤ ይህ ኢትዮጵያ ለሚኖሩ አዲስ ነገር አይደለም። «እዚህ የዕለት ጉርስ ለማግኘት ነው ወጣቶች የሚቸገሩት። እኛ የዮንቨርሲቲ ተማሪዎች ነን። ግን ዮንቨርሲቲዎች ተማሪዎችን የመመገብ አቅም የላቸውም።»
የዕለት ጉርስን ለመሙላት ስራ ያስፈልጋል። በወላይታ ሶዶ የመጨረሻ ዓመት የዩንቨርስቲ ተማሪ የሆነው እና ስሙ እንዳይገለፅ የፈለገው ይህ ወጣት ወደፊት በተማረው መስክ ስራ የማግኘት እድሉ የተመናመነ እንደሆነ ያውቃል። ይሁንና አለመማርም መፍትሔ ሊሆን አይችልም። «በአፍሪቃም ሆነ በኢትዮጵያ ስራ የማግኘት እድሉ በጣም ዝቅተኛ ነው። ሙስና አለ። አለመረጋጋት አለ። ሰው በተማረበት አይደለም ስራ የሚያገኘው። ያን ያንን ስናስብ ተስፋ አስቆራጭ ነው።»


አብዱ መሀመድ ግን ተስፋ መቁረጥ አይፈልግም። በሚኖርባት አፋር ክልል ሰመራ ከተማ ከወንድሙ ጋር እየሰራ ይገኛል። «ወተው ካልፈለጉ ስራ አይገኝም። ጥረት እና ትግል ይፈልጋል። እቤት ተቀምጦ ስራ የለኝም ማለት አይቻልም። በሀገራችን ስራ መፍጠር የሚችሉበት መንገድ እየተፈጠሩ ነው። እኛ ህትመት ቤት ከፍተናል።ሁሉም በራሱ ስራ ቢፈጥር ጥሩ ደረጃ ላይ ይደርሳል።» አብዱ ስለ ጀርመን ወጣቶች እና የቤት ወጪ ጉዳይ ሲሰማ እንደተገረመም ገልፆልናል። « ያልጠበኩትን ነገር ነው የሰማሁት። በእኛ ሀገር የተሻለነው ማለት ይቻላል። አብዝሀኛው ከቤተሰብ ጋር ነው የሚኖረው»
በርግጥ ወላጅ ቤት እስከ ተኖረ ድረስ በጀርመንም ሆነ ኢትዮጵያ ወጪን መቀነስ ይቻላል። ግን ሁሌ ወላጅ ቤት አይኖርም። በርካታ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ተሞክሯቸውን እንዳካፈሉን ከሆነ  የቤት ኪራይ ወጪያቸው ከገቢያቸው ጋር ሲነፃፀር ከጀርመን የባሰ ነው። 
ኤሊያስ፤ በ Master of science  የዩኒቨርስቲ መምህር ነኝ ይላል፤ «ከደሞዜ ተቆርጦ ከሚደርሰኝ 10,700 ብር ለቤት ኪራይ 6,450 ብር  እከፍላለሁ ። ውኃ እና መብራትን ጨምሮ ለባለ አንድ መኝታ ኮንደሚኒየም ቤት። ይህ ከ 60% በመቶ የተጣራ ገቢዬ በላይ ነው ያሳዝናል። አንድ የህክምና ዶ/ር 10,600 ብር የሚቀጠርባት ሀገር ላይ ነው ያለነው።  ይህ እኮ ወደ ሱዳንም ያሰድዳል» ብሎናል።

በጀርመን የጎዳና ተዳዳሪ መሬት ላይ ቁጭ ብለው
በጀርመን የጎዳና ተዳዳሪምስል Peter Kneffel/picture alliance

በደሞዙ በቀን ሶስት ጊዜ መመገብ የከበደው ሀኪም

ተመሳሳይ ተሞክሮውን ያካፈለን ዶክተር ምትኩ ይባላል።  «የ27 አመት ወጣት ኢትዮጵያዊ ጠቅላላ ሀኪም ነኝ» ያለን ምትኩ « በአሁን ሰዓት እዚህ ሀገር ላይ፤ አይደለም ስራ የሌለው እኔ በደመወዜ በቀን ሶስት ጊዜ መብላት አልችልም። ሀገራችን ለተማሩ ሰዎች ሲዖል ከሆነች ሰነበተች። ብችል ወደተሻሉ ሀገሮች ካልሆነ ደቡብ ሱዳን መሄድ ብቻ ነው ሀሳቤ። በሀገሩ እንደኔ ያዘነና ተስፋ የቆረጠ ያለ አይመስለኝም።» ብሎናል። 
እንደ ሀኪም ምትኩ ተስፋ የቆረጡ ሌሎች ወጣቶችም ስለ የኑሮ ሁኔታቸው ገልፀውልናል።

ሲሳይ በአማራ ክልል የሚኖር ወጣት ነው። የቴክኒክ እና ሙያ ተማሪ ቢሆንም በተማረበት ሙያ ስራ አላገኘው። «አይደለም በሙያዬ በአሁኑ ሰዓት የቀን ስራ ለመስራት በጣም ከባድ ነው።» አለምሰገድም በአማራ ክልል ነዋሪ ነው። በባህር ዳር ከተማ ፤« እኛ አካባቢ ስራ የለም አፈሳ ነው። አብዛኛው ሰው ወደ ጫካ ለመግባት ነው የሚያስበው። ሀገራችን ላይ ተስፋ ሰጪ ነገር የለም። የመንግሥትም ችግር አለ። የማህበረሰቡም ችግር አለ። ችግሮቹ በድርድር ቢፈቱ የሀገራችን ሀብት ለሁሉም በቂ ነው።»

ስምረተዓብስ ምን ይላል?

«ኢትዮጵያውያን ወጣቶች እየተጋፈጡ የሚገኙት የኑሮ ጫና እየተባባሰ የመጣና መፍትሔ ያልተገኘለት ነው። አሁን እኔ እንደ አንድ ወጣት በደቡብ ኢትዮጵያ ዲላ ከተማ በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ተቀጥሬ የምሰራ ስሆን ወርሃዊ ደሞዜ በአዲሱ ደሞዝ ስኬል መሠረት 7424 ብር ነው። ይሁንና ከዚህው ደሞዜ ላይ በሆነው ባልሆነው ተቆራርጦ በእጄ 5 ሺህ ቢደርስም የኑሮ ውድነት ጫናውን መቋቋም ካለመቻሌ ባለፈ በስራ ላይ በቆየውባቸው ሶስት ዓመታት የራሴ የምለው ነገር የሌለኝና የኑሮው ሁኔታ እየተባባሰ የመጣ መቋጫ የሌለው መሆኑ አስፈሪ ያደርገዋል። ይበልጥኑ ደግሞ በአከባቢዬ የሚገኙ ወጣቶች እውቀትና ጉልበት እያላቸው በሥራ ማጣት ሲሰቃዩና በተስፋ መቁረጥ ሲባዝኑ ስመለከት ይበልጥ ሃዘን ይሰማኛል። በሃገሬም ተስፋ ወደ መቁረጥ እጓዛለሁ። አሁን ላይም እኔን ጨምሮ በርካታ ወጣቶች ተስፋ በመቁረጥ የጥቁር መዝገብ ጅማሮ የሆነውን ህገወጥ ስደትን መርጠን በጉጉት በመጠበቅ ላይ እንገኛለን።» ብሎናል።

አሌክ ነኝ ያለን ደግሞ « በሀገረ ጀርመን የሚኖሩ ወጣቶች የሚያገኙት ገቢ ለቤት ኪራይ ክፍያ የሚዉል በመሆኑ በወጣቶቹ ህይወት ላይ ለዉጥ እንደማይመጣና የወጣቶች ሰርቶ የመለዎጥ እጣ ፈንታ አደጋ ላይ መዉደቁን ያመላክታል ።በተመሳሳይ በኢትዮጵያም የሚስተዋለዉ ይሄ ነዉ፡፡ምንም እንኳን ሀሳቤ በጥናት ያልተደገፈ ቢሆንም እኔ ከመቀሌ ዩንቨርሲቲ በ2009 ዓ.ም በመጀመሪያ ድግሪ ተመርቄ በአንድ የመንግስት መስሪያ ቤት ዉስጥ በሚዲያ ሞኒተሪንግና አናሊስስ ባለሞያነት ተቀጥሬ ላለፉት 5 እና 6 ዓመታት የሰራዉ ሲሆን በሞያዬ ሰርቼ የማገኘዉ ገቢ ከቤት ኪራይ ወጪ የዘለለ ምንም ለዉጥ የማያመጣና በዚህ ወጣትነት ዘመኔ አሁን ባለዉ የኑሮ ሁኔታ ሰርቶ መለወጠ ቀርቶ በልቶ ማደር በራሱ ሌላ ፈተና እየሆነ መምጣቱ የአደባባይ ሚስጥር ነዉ፡፡» ሲል ተሞክሮውን አካፍሎናል። 

ደቡብ አፍሪቃ፤ ስራ አጥ ሰዎች ቆመው
ደቡብ አፍሪቃ፤ ስራ የሚጠብቁ ሰዎች ቆመውምስል Nic Bothma/EPA-EFE

ሀብታሙ ወንድሙ ደግሞ «የቤት ክራይ ከኑሮ ውድነት ጋር ተዳምሮ በጣም አስጊ ሁኗል። 3x4 ክፍል ቤት እኔ በምኖርበት መቱ ከተማ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማግኘት አዳጋች ነው ይለናል። «በተሻሻለው ደሞዝ አንድ ሰራተኛ ዝቅተኛው ደሞዝ 4800 ገደማ ነው። ቤት ኪራይ ደግሞ 3x4 የሆነ ቤት 2000 ብር ገደማ ነው። ልጅ ያለው  ወጣት ከሆነ ደግሞ ቤተሰብ ማስተዳደር በጣም ይከብዳል።»

ስም ያልገለፀ አንድ ወጣት፤ « በሀገራችን ለወንዶች ያለው የስራ እድል በትንሽ ደሞዝ ወይ ለቀለብ ብቻ መከላከያን ወይም አማፂ ቡድኖችን መቀላቀል ሲሆን ለሴት ታዳጊዎች ደሞ አረብ አገር ተሰዶ የመንግስት ኤጀንሲዎችን እና የኢትዮጵያ አየር መንገድን ገቢ ማሳደግ ነው። ብሎናል።

«ተስፋዬ ጋሹ፤ ከምዕራብ ጎጃም ፍኖተ ሰላም። ኢትዮጵያ ላይ አሁን መኖር ከባድ ነው። በተለይ ለወጣቱ። ወጣቶቹ ለሁሉም ስራ ተፈላጊ ናቸው። ዕርስ በዕርስ ጦርነት ውስጥ ያለች ሀገር ላይ ወጣቶቹ ለውትድርና ተፈላጊ ናቸው። ተምረው ወተውም አደጋ ውስጥ ናቸው ያሉት። »

ማዕድን ድንጋይ
ማዕድን ድንጋይ ምስል Johannes Meier/streetsfilm

ጥቂትም ቢሆኑ ቀደም ሲል እንደሰማችሁት የአፋር ክልል ነዋሪ አብዱ እና በቤንሻንጉል ጉሙዝ አሶሳ ከተማ ነዋሪ የሆነው፣ ቴድሮስ አይነት ተስፋ ያልቆረጡ ወጣቶች ገጥመውናል። ራሴን ለማስተዳደር አላንስም ይላል ቴድሮስ፤ « ባለፉት አመታት ውስጥ ትንሽ ለወጣቱ ጫና ነበር። አሁን ባለው መረጋጋት ግን ኑሮ ላይ ያለው ፋይናንስ እየተሻሻለ ይገኛል። በተለይ እኔ ባለሁበት በቤንሻንጉል ጉሙዝ ወጣቶች የማዕደን ስራ እየሰሩ ራሳቸውን እየለወጡ የተሻለ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።» ብሎናል።


ልደት አበበ

አዜብ ታደሰ