1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ያለሕግ አግባብ የቀጠለዉ የኦነግ አመራሮች እስር

ሐሙስ፣ ግንቦት 18 2014

በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ስፍራዎች ታስረው ይገኛሉ የተባሉት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አመራር አባላት አሁንም ከሕግ አግባብ ውጭ ታስረው እንደሚገኙ ፓርቲው እና የሕግ ጠበቆቻቸው አመለከቱ። ጠበቃ ቱሊ ከእስረኞቹ የመታከም መብት ተከልክለው በጸና ታመው የሚገኙም ስለመኖራቸው አብራርተዋል።

https://p.dw.com/p/4Btoj
 Logo Oromo Liberation Front

በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ስፍራዎች ታስረው ይገኛሉ የተባሉት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አመራር አባላት አሁንም ከሕግ አግባብ ውጭ ታስረው እንደሚገኙ ፓርቲው እና የሕግ ጠበቆቻቸው አመለከቱ። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባለፈው ሳምንት ይፋ ባደረገው ጥናቱ በስም የጠቀሳቸው የኦነግ አመራር አባላት ለተራዘመ ጊዜ ከሕግ አግባብ ውጭ ታስረው የሚገኙ በመሆኑ በአፋጣኝ ከእስር ሊለቀቁ እና ለደረሰባችው ጉዳት ሊካሱ ይገባል ብሎ ነበር። የእስረኞቹ ጠበቃ ግን እስካሁን ለብቻቸው ሲከሰሱ የነበሩት ኮሎኔል ገመቹ አያና ትናንት ከመለቀቃቸው ውጭ የኢሰመኮ ማሳሰቢያንም ተከትሎ አንዳች የተፈጸመ ነገር የለም ብለዋል። ጠበቃ ቱሊ ከእስረኞቹ የመታከም መብት ተከልክለው በጸና ታመው የሚገኙም ስለመኖራቸው አብራርተዋል። 

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በተለያዩ ፖሊስ መምሪያዎች በእስር ላይ ያሉ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አመራሮች እና አባላት የእስር ሁኔታን በተመለከተ ባለፈው ሳምንት ባወጣው የጥናቱ ዝርዝር ሁኔታ መግለጫ፤ በርካታ የድርጅቱ አባላትና አመራሮች ህጋዊ ባልሆነ እስራት ላይ መሆናቸውን አሳውቆ ነበር፡፡

በቡራዩ ፖሊስ መምሪያ በእስር ላይ የነበሩ አቶ ሚካኤል ቦረን፣ አቶ ኬኔሳ አያና፣ ዶ/ር ገዳ ኦልጅራ፣ አቶ ዳዊት አብደታ፣ አቶ ለሚ ቤኛ እና አቶ ገዳ ገቢሳ የተባሉ ስድስት እስረኞች የፓርቲው አመራር መሆናቸውን የገለፀው ኢሰመኮ፤ በወቅቱ ኮሎኔል ገመቹ አያና በፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ማዕከል፣ እንዲሁም አቶ አብዲ ረጋሳ ገላን ከተማ በሚገኘው የኦሮሚያ ክልል ልዩ ፖሊስ ካምፕ ውስጥ በእስር ላይ የሚገኙ መሆኑን ከቤተሰብ እና ጠበቆቻቸው መረዳት መቸቻሉንም እንዲሁ አረጋግጧል፡፡

Daniel Bekele | Leiter der äthiopischen Menschenrechtskommission
ምስል EDUARDO SOTERAS/AFP/Getty Images

ከዚሁ በመነሳትም የኢ.ሰ.መ.ኮ. ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “የኦነግ ፓርቲ አመራር ለተራዘመ ጊዜ ከሕግ አግባብ ውጭ ታስረው የሚገኙ በመሆኑ በአፋጣኝ ከእስር ሊለቀቁ እና ለደረሰባችው ጉዳት ሊካሱ» ይገባል ነበር ያሉት፡፡

በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ቃል አቀባይ አቶ ለሚ ገመቹ ግን፤ የኢሰመኮ መግለጫን ተከትሎ የተለወጠ አንዳችም ነገር አለመኖሩና፤ በፌዴራል ሶሦስተኛ ሰበር ሰሚ ችሎት ክርክር ላይ የነበሩት ኮሎኔል ገመቹ አያና ብቻ የሚከሰሱበት መረጃ ባለመኖሩ ትናንት ከእስር ተለቀዋል ብለዋል፡፡

ኢሰመኮ የፍርድ ቤትና የዐቃቤ ሕግ ውሳኔዎች በተደጋጋሚ ስለመጣሳቸው፣ እስረኞች ከሕግ ውጪ ለተራዘመ እስር መዳረጋቸው ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም ስለሆነ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት አፋጣኝ ማጣራት አካሂዶ ተገቢውን ርምጃ እንዲወስድም ጠይቆ ነበር፡፡ የእስረኞቹ ጠበቃ ቱሊ ባሳ በፊናቸው እንደሚሉት ክስ አንኳ ሳይመሰረትባቸው የሚገኙ መኖራቸውንና የፍርድ ቤትም ትዕዛዛት በተደጋጋሚ መጣሳቸውን አመልክተዋል፡፡ 

ጠበቃ ቱሊ ያለአግባብ ታስረው ቆይተዋል ያሉትን ደንበኞቻቸውን ለማስለቀቅ ከመታገል በተጨማሪ ካሳ እንደሚጠይቁበትም አብራርተዋል።

እስረኞቹ በተለያዩ ማቆያ እና እስርቤት የታሰሩት በኦሮሚያ በተለያዩ ጊዜያት ኹከት ለማስነሳት ተንቀሳቅሰዋል በሚል እና በኦሮሚያ ክልል ታጥቀው ከሚንቀሳቀሱ ኃይላት ጋር ትስስር እንዳላቸው መጠርጠራቸውን የኦሮሚያ ፖሊስ ከዚህ ቀደም በሰጠው ምላሽ አብራርቷል፡፡ ኢሰመኮ ይህ በፍርድ ቤት በማስረጃ ባለመረጋገጡ እስረኞቹ በነጻ ሊለቀቁ ይገባል ማለቱን ተከትሎ ከኮሚሽኑ ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ግን አልተሳካም፡፡ ታሳሪዎቹ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር እንደመሆናቸው በሕዝባዊ አገልግሎት ሥራቸው ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንዳይጋለጡ ጥበቃ ሊደረግ ሲገባ፤ በተግባር የተገላቢጦሽ መሆኑ አሳዛኝ ነው ያለው ኢሰመኮ ግን ጉዳዩ አፋጣኝ እልባት እንዲያገኝ” በባለፈው ሳምንት መግለጫው አሳስቧል።

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ