1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዩክሬን ከአፍሪቃ ሃገራት ጋር ለመተሳሰር የጀመረችው ጥረት

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 27 2015

የዩክሬን ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ በመጪው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2023 አዳዲስ ኤምባሲዎችን በአፍሪቃ ሃገራት ለመክፈት መዘጋጀታቸውን ይፋ አድርገዋል። ለመሆኑ አፍሪቃ የዩክሬንን የዲፕሎማሲ ተነሳሽነት እንዴት ይመለከተዋል?

https://p.dw.com/p/4LYBk
Ukraine Weizen l Erster internationaler Gipfel zur Ernährungssicherheit in Kiew l Präsident Selenskyi
ምስል Ukrainian Presidency via ABACA/picture alliance

የዩክሬን የአዲሱ ዓመት ዕቅድ

የዩክሬን ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ከሳምንታት በፊት ባደረጉት ንግግር ሀገራቸው ከአፍሪቃ ሃገራት ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደ አዲስ እንደምትጀምር ተናግረዋል። በአዲሱ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2023 ዩክሬን ኤምባሲ ልትከፍትባቸው የምትፈልጋቸውን አስር ሃገራት መምረጧንም አመልክተዋል። ይኽ የኪየቭ እርምጃ ጥያቄ ከፈጠረባቸው አንዱ በጋና ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ ማዕከል ከፍተኛ ተመራማሪ እና የአፍሪቃ ጉዳይ ተንታኝ ዶክተር ቦኖ ያኦ ጌቤ ናቸው።

«ወሳኙ ጥያቄ አሁን ለምን? የሚለው ነው። ዩክሬን ትኩረት የሰጠችው በመሆኑ ነው ወይስ አሁን ባለው የፖለቲካ ውጥረት ምክንያት? እንዲሁም አካፋን አካፋ ማለትም ሊያስፈልግ ይችላል፤ ወይስ ከሩሲያ ጋር በምታደርገው ውጊያ ምክንያት ይሆን?»

ባለፈው ጥቅምት ወር የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደሚትሮ ኩልባ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱን ለማጠናከር በርካታ የአፍሪቃ ሃገራትን ጎብኝተዋል፤ በመሀሉ የሩሲያ የሚሳኤል ጥቃት ዩክሬን ላይ ሲጠና ጉብኝታቸውን ለማቋረጥ ቢገደዱም። ሩሲያ ዩክሬን ላይ ጦርነት ከከፈተች ጀምሮ ኪየቭ የአፍሪቃ ሃገራትን ድጋፍ ለማግኘት በመሞከር ላይ ናት። ምንም እንኳን ዘለንስኪ ሀገራቸው በየትኞቹ ሃገራት ኤምባሲ ለመክፈት እንዳቀደች በስም ባይጠቅሱም በመካከለኛው ምሥራቅ እና አፍሪቃ የዩክሬን ተጠሪ ማክሲም ሱብኪህ ትኩረቷን የሩሲያ ጠንካራ ይዞታ እንደሆነ በሚታመነው ከሰሃራ በስተደቡብ ባለው አካባቢ እንደምታደርግ ጠቁመዋል። እንደእሳቸው ገለጻ ከሆነም በቀጣይ ወራት ጋና ላይ ኤምባሲዋን ትከፍታለች። በጉዳዩ ላይ ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው የቀድሞው የዩክሬን ዲፕሎማት እና የውጭ ጉዳይ ተንታኝ ኦሌህ ቤሎኮሎስ እንደውም ዩክሬን አፍሪቃ ውስጥ ሊኖራት የሚገባው ተሳትፎ ዘግይቷል ባይ ናቸው።

Ukraine Getreideexport l UN gecharterter Frachter, Humanitarian Food Aid
ዩክሬን ለአፍሪቃ ሃገራት የላከችው የእርዳታ እህልምስል Str/NurPhoto/picture alliance

« የክፍለ ዓለሙን ጠቃሚነት እንረዳለን። ከአፍሪቃ ሃገራት ጋር ያለንን ትብብር ማስፋፋት የምንችልበት አቅም መኖሩንም እናውቃለን፤ እናም የአፍሪቃ ሃገራት ከዩክሬን ጋር ትስስር እንዲፈጥሩም ማበረታታት እንፈልጋለን። ሆኖም ግን  አሁን ካለው ሁኔታ እና ከጦሩርነቱ ጋር ያለውን ሂደቱት ማስተዋልም ያስፈልጋል።»

ፕሬዝደንት ዘለንስኪ እንደሚተናገሩት ከሆነ ዩክሬን ኤምባሲዎች መክፈት ብቻ ሳይሆን አፍሪቃ ውስጥ ጠለቅ ያለ የንግድ ትስስር እንዲኖራት ትፈልጋለች። ዩክሬናዊው ዲፕሎማትም በተለይ በሩሲያ ወረራ ምክንያት አንዳንድ የአፍሪቃ ሃገራት ያሳዩዋት መቆርቆር ሀገራቸው በግብርናም ሆነ በምግብ አቅርቦት በኩል ትብብር የማድረግን መንገዶች ከፍቷል ባይ ናቸው። ይኽን ደግሞ እንደ እሳቸው ወደ ማኅበራዊና ኤኮኖሚያዊ ትብብር የሚያድግ ነው። በርካታ ሃገራት ከዩክሬን ጋር የንግድ ትስስር እንዳላቸው ያመለከቱት ዶክተር ያኦ ጌቤ ግን የኪየቭ የአሁኑ ተነሳሽነት አንድምታው ሌላ ነው ይላሉ።

UN-Generalversammlung stimmt über Reparationsantrag für die Ukraine ab
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ኒውዮርክምስል Michael M. Santiago/Getty Images

«በርካታ የአፍሪቃ ሃገራት ከሩሲያ ጋር እንደሚያደርጉት ከዩክሬንም ጋር የንግድ ግንኙነት አላቸው። እንደሚመስለኝ የአሁኑ መነሻ ዩክሬን በተመድ መድረክ የአፍሪቃ ሃገራት እንዲደግፏት ለማድረግ ነው፤ በዚህ ደግሞ ከሩሲያ ይልቅ ከአፍሪቃ ጋር ትርጉም ያለው ግንኙነት እንዲኖራቸው ያስችላቸዋል። ይህ ደግሞ ማራኪ ሳይሆን በግጭት የታጀበ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።»

ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው በመካከለኛው ምሥራቅ እና አፍሪቃ የዩክሬን ተጠሪ ማክሲም ሱብኪህም ይህንኑ ነው ያረጋገጡት። በመንግሥታቱ ድርጅት ውስጥ ሩሲያ ላይ ጫና ለማሳደር ዩክሬን ለምታደርገው እንቅስቃሴ የአፍሪቃ ሃገራትን ድምጽ እንደሚፈልጉም አልሸሸጉም። ጋናዊው የፖለቲካ ተንታኝ ዶክተር ያኦ ጌቤ ጦርነቱን በተመለከተ ሳይሆን በጥቅሉ ከዩክሬን ጋር ትብብር መፍጠሩ ባይጠላም የአፍሪቃ ሃገራት ከምዕራባውያን ሃገራት በሚያደርጉት ግንኙነት በተናጠል መደራደራቸው ለክፍለ ዓለሙ እንደማይጠቅም አጽንኦት ሰጥተዋል።

 ሸዋዬ ለገሠ/አይዛክ ሙጋቤ

እሸቴ በቀለ