1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፕሬስ ነፃነት በአፍሪቃ እና የቡሩንዲ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ጥቃት በሶማሊያ

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 29 2014

መረጃዎች እንደሚያሳዩት የፕሬስ ነፃነት በአፍሪቃ መልከ ብዙ ፈተናዎች የተጋረጡበት ነው። ከነዚህም መካከል ሳንሱር ፣መገናኛ ብዙሃንን መዝጋት፣ መረጃዎችን ማፈን፣እንዲሁም የጋዜጠኞች እስራት እና ጥቃት ይገኙበታል።

https://p.dw.com/p/4AxxW
Radiohörer in Afrika
ምስል ALEXIS HUGUET/AFP/Getty Images

ትኩረት በአፍሪቃ

 በዛሬው የትኩረት በአፍሪቃ ዝግጅት የፕሬስ ነፃነት በአፍሪቃ እንዲሁም  አልሸባብ  ሰሞኑን በቡሩንዲ የሰላም አስከባሪ ወታደሮች ላይ በሶማሊያ የፈፀመውን ጥቃት ይቃኛል።
የዘንድሮዉን የ2022 የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን አስመልክቶ የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የፕሬስ ነፃነት በአፍሪቃ መልከ ብዙ ፈተናዎች የተጋረጡበት ነው። ከነዚህም መካከል  ሳንሱር ፣መገናኛ ብዙሃንን መዝጋት፣ መረጃዎችን ማፈን፣እንዲሁም  የጋዜጠኞች እስራት እና ጥቃት ይገኙበታል።
በአህጉሪቱ የዚህ ጥቃት ሰለባ ከሆኑት በርካታ ጋዜጠኞች መካከል በካሜሩን የአባክዋ ኤፍ ኤም  ማንቾ ቢቢክሲ አንዱ ነው።
ጋዜጠኛ ማንቾ ቢቢክሲ  ጥር  17 ቀን 2017 ዓ/ም በባሜንዳ ካሜሩን ከሚገኘው የስራ  ቦታው የካሜሩን ጦር  ኮማንዶዎች  ወስደው ካሰሩት ዓመታት ተቆጥረዋል።
የአባካዋ አፍኤም ፈርጡ ማንቾ ቢቢክሲ አሁን በያውንዴ  የኮንደንጊ ማእከላዊ እስር ቤት ከተፈረደበት የ17 ዓመት ዕስር 5ተኛ አመቱን አገባዷል።  ጋዜጠኛውን ለዕስር የዳረገው በሬዲዮ ጣቢያው  በሰራቸው ዘገባዎች ነው። የጣቢያው ዋና አዘጋጅ ንዲጋና ሬይመንድ እንደሚሉት ጋዜጠኛው ተፅዕኖ ፈጣሪ ዝግጅቶች ነበሩት። 
 «ማቾ ቢቢክሲ በዚህ ሬዲዮ  ጠንካራ አሻራ ነበረው። በአካባቢው ማህበረሰብ ላይ ተጽእኖ የሚፈጥሩ በጣም አስደሳች ዝግጅቶች ነበሩት። ለዚህም ነው "ፍርሀት አልባው ማንቾ ቢቢክሲ" ተብሎ ይጠራ የነበረው.»
አባክዋ ኤፍ ኤም በሀገሪቱ  የፖለቲካ እና የማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ጠንክር ያሉ ዘገባዎችን የሚሰራ ጣቢያ ሲሆን፤ ዋና አዘጋጁ እንደሚሉት የጋዜጠኛው መታሰር ሬዲዮ ጣቢያውን ጎድቶታል።  
«በአስቂኝ ዝግጅቶች ላይ ጠንካራ ጉዳዮችን በቀልድ መልክ አቅርቧል። የእሱ አለመኖር በሬዲዮ ጣቢያው ብዙ አጉድሏል። መሞላት ያለበት ክፍተት ነው ትቶ የሄደው።»
ከ2014 ጀምሮ ደግሞ የካሜሩን መንግስት በመገናኛ ብዙሃን ዘርፉ የሚያደርገው  ክትትል እና ቁጥጥር  በማጠናከር  እና በመገናኛ ብዙኃን ላይ ከፍተኛ ጫና የሚፈጥሩ አዳዲስ የፀረ ሽብር ሕጎችን በማውጣት ጋዜጠኞች ለደህንነታቸው የበለጠ እንዲፈሩ  አድርጓል።
ሲ ኮንራድ እንደ ማንቾ ቢቢክሲ ከፍተኛ ጥበቃ ባለበት እስር ቤት  የታሰረ ጋዜጠኛ ነው። ይህ   ጋዜጠኛ በፀረ-መንግስት  ክስ  የ15 ዓመታት ዕስር በ2018 ዓ/ም ነበር የተፈረደበት። ከጋዜጠኛው ጋር በቅርበት የሰሩት ታምፉ ክሪስቶፈር እንዳሉት የዕስሩ ዓላማ  በፀረ-ሽብር  ህጉ ሌሎችን ለማስፈራርት ነው።
«በእውነቱ ኮንራድ አሁንም በእስር ላይ ይገኛል ብዬ ማሰብ አልችልም። መንግስት ሽብርተኝነትን የገለፀበት መንገድ በጣም ጥቅል ነው።ሁሉም ሰው ዝም እንዲል እና ምንም ነገር እንዳይዘግብ ይፈልጋሉ። በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ኮንራድን በእስር ቤት እንዲቆይ በማድረግ እውነት ከመነገር እንዲቆም አደረጉ?»
በዛምቢያም  ፕሬዝዳንት ሃካይንዴ ሂቺሌማ በነሀሴ 2021 በሀገሪቱ በተካሄደው ምርጫ ሲያሸንፉ፣ የመገናኛ ብዙሃን  ነፃነትን እንደሚያጎለብቱ ቃል ቢገቡም ፤የሉሳካው ጋዜጠኛ ሉኪ ሲቹላ እንደሚለው እስካሁን በተግባር የታዬ ነገር የለም።ጋዜጠኞችን ከእሳቸው እና ከሌሎች የመንግስት ባለስልጣናት እና ተቋማት ጋር  በቀላሉ እንዲገናኙ እና የአገሪቱን የመረጃ ተደራሽነት ህግ የማውጣት ስራም አለመከናወኑን ገልጿል።
አንዳንዶች ደግሞ ከዚህ ቀደም በዛምቢያ ጋዜጠኞች መንግሥትን በመተቸታቸው ይንገላቱ ወይም ይታሰሩ እንደነበር በመጥቀስ፤ የጋዜጠኞችን ደህንነት በመጠበቅ  ረገድ ለሂቸሌማ መንግስት እውቅና ሰጥተዋል። ኤሚሊ ሉክዌሳ የተባለች የስፖርት ጋዜጠኛ በበኩሏ በዛምቢያ የፕሬስ ነፃነትን ለመተቸት ጊዜው በጣም አጭር መሆኑን ገልጻለች። 
በሌላ በኩል የአለም አቀፍ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን እንደገለፀው በማሊም ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እየታፈኑ ነው።ባለፈው በመጋቢት ወር በማሊ  ራዲዮ ፍራንስ ኢንተርናሽናል (RFI) እና ፍራንስ 24 የተባሉ ሁለት የፈረንሳይ የህዝብ ማሰራጫዎችን በማሊ  ወታደራዊ መንግስት  እና በሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮች ተፈጽሟል የተባለውን  የሰብዓዊ መብት ጥሰት አስመልክቶ ባወጡት ዘገባ መታገዳቸውን ገልጿል።
በጊኒ-ቢሳውም የመገናኛ ብዙሃን  በጥብቅ ቁጥጥር  ስር መሆናቸው ይነገራል።የሀገሪቱ መንግስት ከፈቃድ ክፍያ ጋር በተያያዘ በሚያዝያ ወር በመላ ሀገሪቱ 79 የሬዲዮ ጣቢያዎችን  ዘግቷል።
የጋዜጠኞች እና የቴክኒሻኖች ህብረት ዋና ፀሀፊ ዲያማንቲኖ ዶሚንጎስ ሎፕስ እንደሚሉት በጊኒ ቢሳው የመረጃ ነፃነት በክር የተንጠለጠለ ነው።በመሆኑም የሬዲዮ ጣቢያዎቹ መዘጋት መንግስትን በሚተቹ ጣቢያዎች ላይ ከዚህ ቀደም ይደረጉ ከነበሩ  በርካታ ጥቃቶች በተጨማሪ ለፕሬስ ነፃነት በሚደረገው ትግል ሌላ ጥቃት  እየደረሰብን ነው ።ብለዋል።
በደቡብ አፍሪቃ በሌሴቶ እና ዚምባብዌ ደግሞ ጋዜጠኞች የበይነመረብ መዘጋት እና የመንግስት ክትትል ያጋጥማቸዋል።
በሌላዋ አፍሪቃዊት ሀገር ሩዋንዳም የመንግስት ጥብቅ  ክትትል ጋዜጠኞችን በፍርሃት ቆፈን እንዲሸበቡ የሚያደርግ ነው። የሩዋንዳ ዋና ዋና የመገናኛ ብዙሃን በመንግስት የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግላቸው የመንግስት ሞገስ ናቸው።,ዩቲዩብን እንደ መድረክ የሚጠቀሙ ገለልተኛ ጋዜጠኞችም ታስረዋል ወይም ዝም እንዲሉ ተደርገዋል ።በዚህ የተነሳ ብዙዎች መንግሥትን ላለማስቀየም ዝምታን ይመርጣሉ።ይላል። አንድ ስሙን መግለፅ ያልፈለገ የአካባቢው ጋዜጠኛ። 
«በሩዋንዳ የፕሬስ ነፃነት ከቀን ወደ ቀን እየጠበበ ነው።ነፃ ፕሬስ ማለት ምንም አይነት መዘዝ ሳይኖር እውነትን በድፍረት መናገር ማለት ነው። ነገር ግን በሩዋንዳ እንደዛ አይደለም ። እዚህ ደህንነትህን ለመጠበቅ ፀጥ ማለት ወይም ለመንግስት ጆሮ  መልካም የሆነ ነገር መናገር አለብህ ።»
በሌላ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአፍሪቃ እውነታውን ለማጣራት የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።ያም ሆኖ  ግን ስራው ቀላል አለመሆኑ ይነገራል።የመረጃ አረጋጋጮች ያለ ምንም እንቅፋት መስራት ይችሉ እንደሆነ ዶቼ ቬለ የጠየቃቸው የጋና ፋክት ማኔጂንግ ኤዲተር ራቢዩ አልሀሰንን እንደሚሉት በዚህ የስራ ሂደት ውስጥ የሚሰሩ ሰዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እንግልት እና ያልተገባ በደል እየደረሰባቸው ነው። በእኛ ስራ የህዝብ የሚያገኘውን ጥቅም በሚገባ እናውቃለን የሚሉት ሀላፊው ጥቃቶች ቢደርሱም ራሳቸውን  ሳንሱር  ሳያደርጉ ትክክለኛ መረጃን ለህዝብ ለማቅረብ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልፀዋል።
የቡሩንዲ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ጥቃት በሶማሊያ 
ያለፈው ማክሰኞ በማዕከላዊ ሶማሊያ በሚገኘው የአፍሪቃ ህብረት ጦር ሰፈር ላይ በተፈፀመ ጥቃት 10 የብሩንዲ ወታደሮች ሲገደሉ 25 ያህል ቆስለዋል። ሌሎች 5ቱ ደግሞ የደረሱበት አለመታወቁን የብሩንዲ ጦር አስታዉቋል። የአውሮጳ ህብረት  ይፋ ባደረገዉ መግለጫ  ደግሞ በርካታ የሶማሊያ ዜጎችም የጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል። 
አልሸባብ ለጥቃቱ ሃላፊነቱን ወስዶ ካምፑን መቆጣጠሩን እና 173 ወታደሮች መሞታቸውን ገልጿል።ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚነገርለት ይህ እስላማዊ ታጣቂ ቡድን የሶማሊያን ማዕከላዊ መንግስት ለማዳከም ከዚህ ቀደምም በሀገሪቱ የተለያዩ  የሽብር ጥቃቶችን  ሲፈፅም  ቆይቷል።
የአሁኑ ጥቃት ግን  ከመስከረም 2015 ዓ/ም ወዲህ አስከፊው ነው ተብሏል።የሆርን ኢንተርናሽናል የተባለው ስትራቴጂክ ጥናቶች ተቋም ዳይሬክተር  ዶክተር ሀሰን ካኔንጄ ለሰሞኑ የአልሸባብ ጥቃት የተለያዩ ምክንያቶችን ያቀርባሉ።
«አልሸባብ ቀጣይነቱን እና ተፈላጊነቱን ማሳየት ይፈልጋል።ምክንያቱም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፣ የአፍሪቃ ህብረት ተልዕኮ በሶማሊያ /አሚሶም/ እና መንግስት  እንደምታውቁት የአልሸባብ ስጋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል። የሚል ስሜት እየፈጠሩ ነበር።» 
ዶክተር ሀሰን እንደሚሉት  በሶማሊያ የሚሰማሩ የውጭ ሀይሎችን ማስፈራት ለጥቃቱ ሌላው እና ሁለተኛው ምክንያት ነው።
«ሁለተኛው ለወደፊቱ የሚሰማሩ  የውጭ ኃይሎችን  የማስፈራራት ሙከራ ነው። በተጨማሪ ደግሞ ሌሎችን መመልመል እንዲችሉ መንገድ ያመቻቻል። በተለይ የቡሩንዲን ወታደራዊ ሀይሎች በማጥቃት ብሄራዊ ስሜት ያላቸው በመምሰል  በሶማሊያ ተወዳጅነት ለማግኘት ሊሞክሩ ይችላሉ። ከዚህ በተጨማሪ በተለይ ለዓለም አቀፍ ፅንፈኛ ደጋፊዎቻቸው አንዳች ነገር እየሰራን ስለሆነ ወደ እኛ ተቀላቀሉ። የሚለውንም ማሳየት ይፈልጋሉ።»
የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የሶማሊያ መንግስት  የአፍሪቃ ህብረት ተልዕኮ እና የሶማሊያ ኃይሎች  ሽብርተኝነትን በብቃት መዋጋት እንዲችሉ የበለጠ ድጋፍ  እንዲደረግ ተማጽኗል።
በምርጫ መራዘም ሳቢያ  ከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ እንደገጠማት  የሚነገርላት ሶማሊያ፤ በቀጠናው በረዥም ጊዜ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት የረሃብ ስጋት ውስጥ  ትገኛለች። የሰሞኑ ጥቃት  ደግሞ የሀገሪቱን የፀጥታ ችግሮች  አጉልቶ የሚያሳይ ነው ተብሏል። ዶክተር ሀሰን እንደሚሉት የፖለቲካ ሽግግሩ መዘግየትም ለችግሩ መባባስ አስተዋፅኦ አድርጓል።
«በሶማሊያ የፖለቲካ ሽግግር መዘግየቱ ጠንካራ ውሳኔዎችን የማሳለፍ አቅም ገድቧል። በመሆኑም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ የመጣውን የጸጥታ ዘርፍ ዘመናዊ እና ሙያዊ ለማድረግ  እና ብዙ ሶማሊያውያን የሚፈልጉትን ያህል  የኃይል እርምጃ አማራጭ አድርጎ ማቅረብ አልተቻለም።» 
በሌላ በኩል ጥቃቱ የተከሰተው የቀድሞው የአፍሪቃ ህብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ በሶማሊያ በአፍሪቃ ህብረት ተልዕኮ ለሶማሊያ ሽግግር  ከተተካ ከወር በኋላ በመሆኑ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት በሶማሊያ ደካማ የፀጥታ እና ደህንነት ሁኔታ መኖሩን ያሳያል። 
ተመራማሪው ዶክተር ሀሰን ደግሞ ጉዳዩ በሶማሊያም ይሁን በአፍሪቃ ቀንድ ትልቅ  የደህንነት ተግዳሮት መደቀኑን ያሳያል  ይላሉ። በተለይ ዓለም ትኩረቱን በዩክሬን ጦርነት ላይ  በማድረጉ  ችግሩ ይበረታል የሚል ስጋት አለቸው።በመሆኑም የሶማሊያን ቀውስ ለመፍታት በቅድሚያ  በሀገሪቱ ተቀባይነት ያለው መንግስት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
«በሶማሊያ ያለውን ሽግግር ሂደት ማጠናቀቅ ያስፈልጋል።በተቻለ ፍጥነት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫውም መከናወን አለበት።ያ አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ  አብሮት ሊሰራ የሚችል  ታዓማኒነት ያለው መንግስት ስለሚያስፈልግ  ነው።ይህ ባልሆነበት ሁኔታ የፀጥታ አገልግሎቱን በሚፈለገው መንገድ ዘመናዊ እና ሙያዊ አድርጎ መገንባት አስቸጋሪ ይሆናል።»
የአፍሪቃ ህብረት ፣ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የአውሮፓ ህብረት ፣ ብሪታንያ እና የቀጣናው ኅብረት  (ኢጋድ) ጥቃቱን አውግዘዋል። በሀገሪቱ ሰላምን ለማስፈን   ከአፍሪቃ ህብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ እና ከሶማሊያ የጸጥታ ሃይሎች ጎን እንደሚቆሙ ገልፀዋል። 
የአፍሪቃ ህብረት ተልዕኮ በሶማሊያ  ከቡሩንዲ፣ ከጅቡቲ፣ከኢትዮጵያ፣ ከኬንያ እና ከዩጋንዳ የተውጣጡ  22,000 የሚጠጉ  ወታደሮች  ያሉት ሲሆን ።ከጎርጎሪያኑ 1991 ዓ.ም ጀምሮ  ቀውስ ውስጥ የምትገኜውን የሶማሊያን  የፀጥታ ኃይሎች የማገዝ  ኃላፊነት የተጣለበትበት ነው። 

Somalia | Anschlag in Mogadischu
ምስል Feisal Omar/REUTERS
AMISOM Soldaten aus Burundi in Mogadischu
ምስል Ilyas A. Abubakar/AU UN IST Photo/AFP
Symbolbild Whistleblower Afrika
ምስል Andrey Popov/Panthermedia/imago images
Guinea Bissau Bewaffneter Angriff auf "Radio Capital" in Bissau
ምስል Privat


ፀሐይ ጫኔ
ነጋሽ መሀመድ