1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የፍሪታውን ከንቲባ ኢቮን አኪ ሶየር የጀርመን አፍሪካ ሽልማታቸውን መስከረም 26 ይቀበላሉ

Eshete Bekele
ቅዳሜ፣ መስከረም 18 2017

የሴራ ሊዮን ዋና ከተማ ፍሪታውን ከንቲባ ኢቮን አኪ ሶየር የጀርመን አፍሪካ ሽልማታቸውን መስከረም 26 ይቀበላሉ። የፍሪታውን ከተማን የቆሻሻ አወጋገድ በማዘመን፣ የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦትን በማሻሻል እና ዛፎች እንዲተከሉ በማበረታታት ኢቮን አኪ ሶየር ስኬታማ ሆነዋል።

https://p.dw.com/p/4lBBn
የሴራ ሊዮን ዋና ከተማ ፍሪታውን ከንቲባ ኢቮን አኪ ሶየር
የሴራ ሊዮን ዋና ከተማ ፍሪታውን ከንቲባ ኢቮን አኪ ሶየር የጀርመን አፍሪካ ሽልማታቸውን መስከረም 26 ይቀበላሉ። ምስል DW

የፍሪታውን ከንቲባ ኢቮን አኪ ሶየር የጀርመን አፍሪካ ሽልማታቸውን መስከረም 26 ይቀበላሉ

የሴራ ሊዮን ዋና ከተማ ፍሪታውን ከንቲባ ኢቮን አኪ ሶየር ከፍተኛ አድናቆት ያገኙ ሴት ናቸው። ከተማቸውን በበርካታ መንገዶች አሻሽለው በዘርፈ-ብዙ ጉዳዮች ግንባር ቀደም አድርገዋታል።

ፍሪታውን በአሁኑ ወቅት 160 ማጠራቀሚያዎች እና የዝናብ ውኃ መሰብሰቢያዎች የተገጠሙለት የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ ሥርዓት ባለቤት ነች። ከፍተኛ የጎርፍ መከላከያዎችም ተበጅቶላታል። ከመጸዳጃ ቤቶች የሚወጣ ቆሻሻ በፍሪታውን ወደ ብስባሽ ማዳበሪያ (compost) ባዮጋዝ እና የማብሰያ ከሰል ይቀየራል። እነዚህ ሥራዎች ለማገዶ የሚቆረጠውን ዛፍ በመቀነስ የደን ሽፋንን ለመጠበቅ ዕገዛ ያደርጋሉ።

የሴራ ሊዮን ዋና ከተማ የውኃ አቅርቦት ዘላቂ ማሻሻያ ተደርጎለታል። ከጸሀይ በሚመነጭ ኃይል የማጣሪያ ሥርዓት ባለቤት የሆኑ የውኃ መቸርቸሪያ መደብሮች በአሁኑ ወቅት ለበርካታ ማኅበረሰቦች ንጹህ የመጠጥ ውኃ እያቀረቡ ነው። ይህ በመደብሮቹ አማካኝነት የራሳቸውን ቢዝነስ እንዲያካሒዱ በመፍቀድ ወጣት ሴቶችን ማበርታት ብቻ ሳይሆን ውኃ በሚቀዱበት ወቅት የወሲባዊ ጥቃት ሰለባ የመሆን ዕድላቸውን ይቀንሳል።

የጀርመን አፍሪካ ፋውንዴሽን (DAS) በፍሪታውን የተከናወነውን ሥራ አስደናቂ፣ አስገራሚ እና መሸለም የሚገባው በማለት ገልጾታል። በዚህም ምክንያት ኢቮን አኪ ሶየር ለዘላቂ የከተማ ልማት እና አካባቢያዊ ተሳትፎ የጎርጎሮሳዊው 2024 የጀርመን አፍሪካ ሽልማትን ሰጥቷቸዋል።

ቁርጠኝነታቸው የማይናወጥ ተብሎ ተወድሷል። ሸላሚው እንደሚለው ደረጃ በደረጃ “ፍትኃዊ፣ ዘላቂ እና ሊኖርባት የሚገባ ከተማ የመመሥረት ርዕያቸውን” ተግባራዊ አድርገዋል።  የከንቲባዋ ጥረት እስካሁን ቢሯቸው ከሚፈልገው የላቀ እንደሆነ ሸላሚው ድርጅት ገልጿል።

አኪ ሶየር የተወለዱት በሴራ ሊዮን ቢሆንም ጋናን ጨምሮ በተለያዩ ሀገሮች ኖረዋል። ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ የ56 ዓመቷ ወይዘሮ በለንደን ለ25 ዓመታት የፋይናንስ ባለሙያ እና ኦዲተር ሆነው ሰርተዋል። በሴራ ሊዮን መንግሥት ውስጥ ተሳትፎ ማድረግ የጀመሩት በጎርጎሮሳዊው 2014-2015 የኢቦላ ወረርሽኝ በተቀሰቀሰበት ወቅት ነው። በጎርጎሮሳዊው 2023 ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኙት ፖለቲከኛ ለሁለተኛ የሥልጣን ዘመድ ድጋሚ ተመርጠዋል።

Deutscher Afrika-Preis 2024 an Yvonne Aki-Sawyerr
የጀርመን አፍሪካ ፋውንዴሽን እንደሚለው በአፍሪካ ላሉ የፖለቲካ መሪዎች በተለይ በውሳኔ አሰጣጥ እና በአተገባበር ረገድ ነዋሪዎችን ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲሳተፉ ለማድረግ አኪ ሶየር አርዓያ ናቸው።ምስል DW

“በፕሮጀክቶቻቸው አኪ ሶየር ቱሪዝም፣ የቆሻሻ አወጋገድ፣ መሠረተ-ልማት እና የአረንጓዴ ኤኮኖሚ ልማት የሥራ ዕድል እና መዋዕለ-ንዋይ ፈጥረዋል” በማለት የጀርመን አፍሪካ ፋውንዴሽን ስኬታቸውን አብራርቷል።

አኪ ሶየር በፈጠራ ሐሳቦቻቸው ተሽከርካሪዎች በሀገራቸው ጎዳናዎች በሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንዲሻሻል ያበረታታሉ። የትራፊክ መጨናነቅ እና የከባቢ አየር ብክለትን ለመቀነስ የሚረዳ ተንጠልጣይ የገመድ መጓጓዣ በፍሪታውን ለመዘርጋት የአዋጪነት ጥናት እንዲካሔድ ማድረጋቸው በምሳሌነት ይጠቀሳል።

ዕቅዱ ተግባራዊ ከሆነ በቂ መጓጓዣ የሌላቸው የፍሪታውን መንደሮች ነዋሪዎች በፍጥነት ወደ ማዕከላዊ የከተማዋ ክፍሎች መድረስ እንዲችሉ ይጠቅማል። የመጓጓዣው ተጠቃሚዎች አረንጓዴውን ተፈጥሮ በመንገዳቸው ላይ እንዲመለከቱም ዕድል ይፈጥራል።

ፍሪታውን የዛፎች ከተማ (#FreetownTheTreeTown) በሚል በጀመሩት ዘመቻ የከባቢ አየር ለውጥ ተጽዕኖን ለመግታት እና በከተማዋ ዙሪያ የሚገኘውን ደን ይዞታ ለመጠበቅ 977,000 ዛፎች ተተክለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ዘመቻው ዛፎቹን ለተከሉ እና ለሚንከባከቡ ነዋሪዎች የገቢ ማግኛ ዕድል የፈጠረ ነው። በዚህም ምክንያት ፍሪታውን ለሌሎች ከተሞች በአርዓያነት የምትታይ ሆናለች። የደቡብ አፍሪካ አስተዳደራዊ ዋና ከተማ ፕሪቶሪያ ከፍሪታውን ምክር ከሚሹ መካከል ነች።

የጀርመን አፍሪካ ፋውንዴሽን እንደሚለው በአፍሪካ ላሉ የፖለቲካ መሪዎች በተለይ በውሳኔ አሰጣጥ እና በአተገባበር ረገድ ነዋሪዎችን ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲሳተፉ ለማድረግ አኪ ሶየር አርዓያ ናቸው። ለከተማዋ የተዘጋጀው የረዥም ጊዜ የልማት ዕቅድም የከንቲባዋ ሐሳብ ነው። ከፖለቲከኞች በተጨማሪ የንግዱን እና የሲቪል ማኅበረሰቦች ተወካዮችን በዕቅዱ ዝግጅት አሳትፈዋል።

“በአረንጓዴ እና አምራች ዘርፎች በሥራ ፈጠራ ላይ በማተኮር በከተማችን ለሚመጣው ትውልድ ኤኮኖሚያዊ ዕድገትን እና ብልጽግናን እንፈጥራለን” ብለዋል አኪ ሶየር።

የፍሪታውን ከንቲባ ኢቮን አኪ ሶየር የጀርመን አፍሪካ ሽልማት አሸናፊ
የጀርመን አፍሪካ ፋውንዴሽን የዓመቱ ተሸላሚ አድርጎ እንደመረጣቸው ይፋ ሲያደርግ አኪ ሶየር “ደስታ እና ታላቅ ክብር ይሰማኛል” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።ምስል DW

የጀርመን አፍሪካ ፋውንዴሽን የዓመቱ ተሸላሚ አድርጎ እንደመረጣቸው ይፋ ሲያደርግ አኪ ሶየር “ደስታ እና ታላቅ ክብር ይሰማኛል” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። “ይሁንና ሽልማቱን ለመላ ሀገሪቱ የተሰጠ እንጂ የግል እውቅና አድርጌ አልመለከተውም” ያሉት ከንቲባዋ “ከተማችንን ለመለወጥ የያዝንውን ዕቅድ ለማሳካት በሚተጉ የሥራ ባልደረቦቼ እና በፍሪታውን ነዋሪዎች ሥም ሽልማቱን እቀበላለሁ” ሲሉ ተናግረዋል። 

“ይኸ ጉዞ ከፈተናዎች ነጻ አልነበረም። ነገር ግን የሠራንው ሥራ በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና በማግኘቱ እጅግ በጣም አመሰግናለሁ” ብለዋል።

የሽልማት አሰጣጡ በበርሊን በመጪው ጥቅምት 16 ይካሔዳል። የጀርመን የታችኛው ምክር ቤት ወይም ቡንደስታግ ፕሬዝደንት ባርብል ባስ ከ20 በላይ ከሚሆኑ ዕጩዎች መካከል በዳኞች ተመርጠው አሸናፊ ለሆኑት አኪ ሲየር ሽልማታቸውን ይሰጣሉ።

ከጎርጎሮሳዊው 1993 ጀምሮ የጀርመን አፍሪካ ፋውንዴሽን ለዴሞክራሲ፣ ለሰላም፣ ለሰብአዊ መብቶች፣ ለዘላቂ ልማት፣ ለጥበብ፣ ለባሕል፣ ለጥናት እና ምርምር እንዲሁም ሌሎች ማኅበራዊ ጉዳዮች በአፍሪካ ከፍ ያለ አስተዋጽዖ ላበረከቱ ሽልማቱን ሲሰጥ ቆይቷል።

የጀርመን አፍሪካ ፋውንዴሽን በተለያዩ የፖለቲካ ክበቦች እና በአጠቃላይ በጀርመን ሕዝብ ዘንድ ስለ አፍሪካ የተለየ ግንዛቤ እንዲኖር የሚያበረታታ ወገንተኛ ያልሆነ ድርጅት ነው።

ኒኮላስ ፊሸር/እሸቴ በቀለ

ታምራት ዲንሳ